ከ65 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከሳዑዲ አረቢያ ተመልሰዋል ተባለ

0
765

ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ከ65 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው መመለሳቸው ተገለጸ።

ይህ የተነገረው በሰው መነገድ፣ በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ለሥራ ወደ ሀገር ውጭ መላክ ወንጀሎች መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የ2014 በጀት ዓመት የብሔራዊ ምክር ቤቱ ዓመታዊ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ተብሏል።

በዚህም ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው ለተመለሱ ዜጎች የተደረገውን ድጋፍ በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ለተመላሾቹ ዐስር የመቀበያ ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል።

ከመጋቢት 21 ቀን 2014 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 9 ቀን ድረስ 65 ሺሕ 446 ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፣ 62 ሺሕ 978 ዜጎች ደግሞ ወደ ቀያቸው ተጓጉዘዋል ተብሏል።

ከሳዑዲ አረቢያ ተመላሾች መካከል 3 ሺሕ 119 የሚሆኑ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ባሉበት የመቀበያ ጣቢያ አስፈላጊው የሎጂስቲክስ፣ የሕክምና እንዲሁም የሥነልቦና ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑም ተገልጿል።

በሪፖርቱ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ተዘግተው የነበሩ የውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሳይከፈቱ መቅረት ሕገውጥ ስደቱን እያባበሰው መምጣቱም ተነስቷል።

በስብሰባው በክልሎች መካከል ስላለው የተመላሾች ቅብብሎሽ ስርዓትን በተመለከተ በተዘጋጀው የመግባቢያ ስምምነት ላይ ማብራሪያ መቅረቡም ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here