“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
የሴቶች ትግል ከባህር ማዶ ሲመጣ ከአገር ባህል፣ ከእምነትና ከስርዓት የተቀዳ ባለመሆኑ ብዙ ሙግት በዛበት እንጂ፣ አገር ውስጥ ያሉና ለእኩል መብት ጥያቄ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ እድሎች አሉ። ግን አብዛኛውን ስንጠቀምበት አንታይም።
ለምሳሌ ደጋግሜ በተለያዩ ጽሑፎች ላይ የማነሳት ውርድወት አንዷ ናት። የቃቄ ውርድወት የሚለውን ቴአትር የተመለከተ አልያም በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጉዳዮችን ከመጻሕፍት ያገላበጠ ሰው በደንብ ያውቃታል። ይህቺ ሴት በምትኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ እንዲለወጥና የሴቶች እኩል መብት እንዲከበር ለማድረግ በብዙ የደከመች ሴት ናት።
ውርድወትን የትግል መነሻ ማድረግ፣ የእርሷን ጥያቄዎች መነሻ የሚያደርጉ ትግሎችን መፍጠር ይቻል ነበር። እንደውም ከዚህ አልፎ ባህር ማዶዎች ሳይዋሱት ይቀራሉ ብላችሁ ነው!
ብዙ ጊዜ አሜሪካዊቷ ሮዛ ፓርክስ ትነሳለች። ይህቺ ሴት በአንድ በተሳፈረችበት አውቶብስ ውስጥ በቆዳ ቀለሜ የተነሳ የሚደርስብኝን መድሎ አልቀበልም በማለት ከወንበሯ ለመነሳት ፈቃደኛ አለመሆኗ ትልቅ ንቅናቄ አስነስቶ ነበር። ይህች ሴት ዛሬም ትወሳለች፤ ጥቁር አሜሪካውያን የትግላቸው ግብዓት ያደርጓታል፤ አልረሷትም።
የእኛዋን ውርድወት እንደ ማሳያ አነሳኋት እንጂ፣ ጥቂት የማይባሉ በተመሳሳይ የትግል መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሴቶች አሉ። ግን በሚገባው አልተጠቀምንባቸውም። የትኛውም የዓለም አገር ሴቶችን በመሪነት ሳይሰይም በፊት ኢትዮጵያ ሴት ንግሥቶች ነበሯት፣ እነዚህን ሴቶች ጠቅሰን ግን ሞግተን አናውቅም። ‹ማርች ኤይት› ብለን ከባህር ማዶ የተሰጠንን ቀን እንደግስበታለን፣ ነገር ግን ሻደይና አሸንዳ እንዲሁም ሶለል የተባሉ አገር በቀል የሆኑ የሴቶች የነጻነት ቀን የሆኑ እለታትን በተገቢው መንገድ አንጠቀምባቸውም።
ነገሩ በሚገኘው ፈንድ ምክንያት ይሁን ወይም በእጅ ያለ ወርቅ ሆኖብን አላውቅም። ብዙ ‹ፌሚኒስቶች› ኢትዮጵያዊ የሆነ ‹ፌሚኒዝም› ሲባል አይዋጥላቸውም። ለዛም ነው ትግላቸው ሁሌም አንጻራዊ ገፊ ኃይል የሚኖረውና እንደውም በሴቶች ላይ የበለጠውን ጫና እያሳደረ ያለው።
በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በመጀመሪያ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ማኅበረሰቡ ሲያውቅ፣ ከዛ ደግሞ በሚገባውና በተገቢው መንገድ ሲነገረው ነው። ከባህር ማዶ በሚመጡ ስልቶችና አካሄዶች ከተቀጠልን ግን፤ በዘርፉ ከተሰማሩ ‹ባለሞያዎች› ኑሮ ውጪ የሚቀየር ነገር አይኖርም።
በአንጻሩ ግን ማኅበረሰቡ በሚያውቀው፣ የራሱ መልክ በሆነው እውነት ውስጥ ነገሮችን ማስረዳት ያሻል። እኛ እንደ አገር ያለንን ባህል፣ እምነት፣ ስርዓት፣ አስተሳሰብና የልቦና ውቅር መናቅም ሆነ ቸል ማለት አይገባም፤ ደግሞም አያዋጣም። ወደድንም ጠላንም ገና የትምህርት ተደራሽነት፣ የሴቶች ጠለፋና ግርዛት የመሳሰሉት ገና ያላለቁ የቤት ሥራዎች ናቸው። ኧረ እስቲ ኢትዮጵያዊ የሆነ የሴቶች የእኩል መብት ትግልን እንፍጠር!
መቅደስ ቹቹ
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014


