አርብ ነሐሴ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ መንግስት ስኳር ኢንተርፕራይዞችን ወደግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ላይ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ ማቅረቡን አስታውቋል።
መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በዚህም የግሉ ዘርፍ በስኳር ኢንዱስትሪው የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ በዘርፉ ማሻሻያዎች ማድረጉ ነው በመግለጫው የተገለጸው።
ከዚህ አንጻርም የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ባለሐብቶች የስኳር ፋብሪካዎችን ወደግሉ ዘርፍ ለማዛወር በወጣው ጨረታ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪውን አቅርቧል።
ለጨረታ የቀረቡት የስኳር ፋብሪካዎችም ኦሞ ኩራዝ 1፣ ኦሞ ኩራዝ 2፣ ኦሞ ኩራዝ 3 ፣ ኦሞ ኩራዝ 5፣ አርጆ ደዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ተንዳሆ የስኳር ፋብሪካዎች ናቸው።
ጨረታው ተወዳዳሪነትን እና የስኳር ምርታማነትን በማሳደግ የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ያለመ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ይህም ኢትዮጵያ ለስኳር ግዢ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት፥ ገቢን ለማሳደግ ብሎም የሸንኮራ አገዳ አምራቾችን ህይዎት ለማሻሻል እንደሚረዳም ታምኖበታል ተብሏል።
በተጨማሪም ጥሬ እና ያለቀለት የሸንኮራ አገዳ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት እንደሚረዳም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመላክቷል።



