ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘንድሮ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
ኩባንያው ያገኘው ገቢ ከአምናው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 44 በመቶ ጭማሪ ማድረጉም ተገልጿል።
የወጠነውን ገቢ ከማሳካት አልፎ 8 በመቶ ተጨማሪ እንዳሳካ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ለሸገር ሬዲዮ ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ኦፕሬሹኑን በማሳደግ የመንገደኛ ቁጥርና የሚያጓጉዘውንም እቃ በመጨመር ዘንድሮ 5 ቢሊየን ዶላር አግኝቷል።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን፤ ውጤቱ ሊገኝ የቻለው ብቁ አመራር በመስጠትና በሠራተኞቹ ሌት ተቀን በመስራት የመጣ ውጤት ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ ከጭነት ገበያ ጥሩ ገቢ ለማግኘት የሚበሩትን አውሮፕላን ቁጥራቸውን ወደ 38 አሳድጎ ሲሰራ መቆየቱ ተነግሯል።
አሁን የጭነት ገበያው ቀዝቀዝ ሲል ደግሞ የመንገደኛ ኦፕሬሽን ሲበዛ 13 ቱን ወደ ነበሩበት መልሰናል ብለዋል ዋና ሥራ አስፈፃሚው።

አየር መንገዱ በአሁን ወቅት 138 አውሮፕላኖችን የሚያበር ሲሆን፤ 36 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ማዘዙም ተገልጿል።
ሐምሌ 1 በጀመረው 2015 በጀት ዓመትም ከ 36ቱ 13ቱን አውሮፕላኖች ለማስገባት አቅዷል።
ከ13 አውሮፕላኖች አስሩ ቦይንግ 737 ማክስ የሚባሉት ሲሆኑ፤ 3ቱ ባለፈው ሐምሌ ወር መግባታቸውም ተነግሯል።
የሚቀሩት 7 ደግሞ በቅርቡ እንደሚገቡ አየር መንገዱ ተናግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ 2 ኤር ባስ ኤ 350 የሚባሉ አውሮፕላኖች እንደሚመጡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በእድሜ የገፉት ጥቂት የሚከራዩ አውሮፕላኖች እንደሚወጡም ተነግሯል።



