በደብረብርሃን ከተማ ወይንሸት ካምፕ ለ3 መቶ ተፈናቃዮች የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም ተካሂዶ 1 መቶ 17ቱ መታመማቸውን ተገለጸ

0
967

የተከሰተውን ችግር መቆጣጠር መቻሉን የደብረ ብርሃን ከተማ ጤና መምሪያ አስታውቋል

ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በደብረብርሃን ከተማ ወይንሸት ካምፕ ለሚገኙ ለ3 መቶ ተፈናቃዮች የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም ተካሂዶ ከተመገቡት ውስጥ 1 መቶ 17ቱ መታመማቸው ተገልጿል።

የከተማዋ ጤና መምሪያ ኃላፊ በቀለ ገብሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ትናንት ነሐሴ 15 ቀን 2014 በወይንሸት መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ ለ3 መቶ ተፈናቃዮች የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም መካሄዱን ገልጸው፤ ከተመገቡት ውስጥ 1 መቶ 17ቱ መታመማቸውን አስረድተዋል፡፡

ችግሩ እንደተከሰተም የከተማው አመራሮች፣ የጸጥታ መዋቅር አካላትና የጤና ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ የታመሙትን ወገኖች በፍጥነት ደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል፣ 04 ጤና ጣቢያ፣ አየር ጤና፣ እና ጠባሴ ጤና ጣቢያዎች በመውሰድ እንዲታከሙ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

በተደረገው ፈጣን ጥረትና ርብርብ ታመው ከነበሩት ውስጥ 1 መቶ 16ቱ ወደ መጠለያ ጣቢያቸው መመለሳቸውን አረጋግጠው፤ አንድ ሰው ግን አሁንም ህክምናውን እየተከታተለ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡

ከምግቡ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ችግር መንስዔው ምን እንደሆነ ለማወቅ ለደብረብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል ናሙናው ተሰጥቶ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት በቀለ ውጤቱ እንደደረሳቸው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አሳውቀዋል፡፡

የችግሩን መንስዔ ውጤት እንደደረሰ ትክክለኛውን መረጃ በድጋሚ ይፋ እስከሚደረግ ድረስ ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ ኃላፊው ማሳሰባቸውን ከከተማው አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here