የእኛን እናጥና!

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ትግል መች ተጀመረ የሚለው በጥናት መሠረት የተቀመጠ አይመስለኝም፤ ወይም መረጃው የለኝም። ነገር ግን እንቅስቃሴዎች የተጀመሩት ከደርግ ዘመነ መንግሥት በኋላ ወይም የሴቶች ቀን መከበር ከጀመረ ወዲህ እንዳልሆነ እሙን ነው።

በቀደመው ዘመን የሴቶች የእኩል መብት ትግል ተሳታፊዎችን ባናወሳ እንኳ፣ ዛሬ ላይ ሆነን ከሴቶች መብት አንጻር ‹ነበር› ብለን በግምት ዝቅ በምናደርገው ዘመን የነበሩ ሴት መሪዎችን ታሪክ እንኳ አንዘክርም። ሴት ንግሥት በኢትዮጵያ ምድር ነበረች። በአድዋም ሆነ በኹለተኛው የኢትዮጵያና ጣልያን ጦርነት ተሳትፈው ታሪክ የሠሩና የተጋደሉ ሴቶችንም አናወሳም።

በተለያዩ ከተሞች ታላላቅ ታሪክ የሠሩ ወንዶቹ መሪዎች ሐውልት ሲቆምላቸው፤ በሴቶች አንጻር የተሠሩ ሀውልቶች በአብዛኛው በጠቅላላው ሴቶችን የሚወክሉ ናቸው። አደባባይ እንደሚሰየም ሁሉ ለምን በጀግንነት የሚታወቁ ሴቶች ሀውልት እንደማይቆምላቸው ገብቶኝ አያውቅም።

‹ሴቶች ፖለቲካን አይደፍሩም› ሲባል ‹‹ትክክል ነው›› ብዬ ልስማማ የሚቃጣኝ ጊዜ አለ። ፖለቲከኛ የሆኑ ብርቱ ሴቶች እንዳሉ አውቃለሁ። ነገር ግን የእቴጌ ጣይቱ ሀውልት እንዳልተሠራና ሊሠራ የተደረገው ጥረትም በፖለቲካ ሰበብ ተድበስብሶ መቅረቱን ሳስብ ፤ ሴቶች ለምን ዝም አልን ብዬ እጠይቃለሁ።

የጣይቱ አይሆንም ቢባል እንኳ፣ በቃቄ ውርድወት ወይም በንግሥት ዘውዲቱ አልያም በአበበች ጎበና እና ካትሪን ሐምሊን ወይም ከብዙ ሴት ብርቱዎች መካከል በአረአያነት የምትነሳ የአንዲት ሴት ሀውልት እንኳ እንዴት አይሠራም? እሺ ሐውልት ይቅር፣ ባለፉት 30 ዓመታት በአንጋፋ ሴቶች ሥም የተከፈቱ ትምህርት ቤቶች ስንት ናቸው?

መቼም በቁጥር እየበረከቱ የመጡ ባንኮች የተለያዩ ቅርንጫፎቻቸውን ከአገር ጀግኖች ጋር አያይዘው የሚጠሩ መሆኑ በጀ፡፡ ባይሆን ኖሮ የታሪክ መዛግብትን ካልገለጥን በቀር በጀግንነትና ለአገር ትልቅ ሥራ በመሥራት ያለፉትን ሴቶች በምን ማውሳት እንችል ነበር?

የአደባባዩስ ይቅር፣ እነዚህን ሴቶች ምን ያህል እንደተጠቀምንባቸው ራሳችንን እንታዘብ። በእነዚህ ሴቶች ሥም ምን ሠራን፣ ታሪካቸውንና የሠሩትን ሥራ እንዴት አወጣንና ለዛሬ ሥራችን መንገድ እንዲመራን አደረግን? እንደ አዲስ መንገድ ከመጥረግ ይልቅ አስቀድሞ በተጀመረው ላይ ለመሥራት ምን ጥረት አደረግን? በሴቶች ጉዳይ የሚሠሩ አዳዲስ ማኅበራት ከቀደምቱ ጋር ምን ልምድ ወሰዱ?

ይህን ጥያቄ መጠየቅ ተገቢ ነው። የራሳችንን ታሪክ ካላጠናን በቀር የዛሬ እንቅስቃሴያችን ለነገ እንደማያድር እርግጠኛ መሆን አለብን። እኛ ካለፈው ያልተቀበልነውን ዱላ፣ ነገ ከእኛ እጅ ማንም ተቀብሎ ሊያስቀጥልልን አይችልም። ለውጥ ደግሞ የሚመጣው በአንድ ጀንበር ሳይሆን በተከታታይና ቀጣይ ሥራ መሆኑ አያጠራጥርም። እና እስቲ ዛሬም ልበል፤ ወደ ራሳችን እንመልከት!

መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች