ከጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ወጣቶችም እየታሰሩ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጣለች።
የክልልነት ጥያቄ አንስታችኋል፣ አስተባብራችኋል፣ ደግፋችኋል እንዲሁም የመንግሥትን ክላስተሪንግ አደረጃጀት ተቃውማችኋል የተባሉ አካላት እየተለቀሙ እየታሰሩ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
እስካሁንም ስምንት የዞን መምሪያ ኃላፊዎች ታስረዋል የተባለ ሲሆን፣ የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ የክልልነት ጥያቄውን ትደግፋለህ በሚል ታስረዋል ነው የተባለው።
እንዲሁም ወጣቶችን አሳልፈው እንዲሰጡ የተጠየቁት የጸጥታ መምሪያ ኃላፊው፣ ‹‹ወጣቶች ድንጋይ ባልወረወሩበትና ረብሻ ባልፈጠሩበት ሁኔታ ምን ስላደረጉ አሳልፌ እሰጣለሁ።›› በማለታቸው ለእስር መዳረጋቸው ተሰምቷል።
በተጨማሪም፣ የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ፣ የሙያና ቴክኒክ መምሪያ ምክትል ኃላፊ እንዲሁም ሌሎች በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚሠሩ አካላት መታሰራቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው።
የመረጃ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ብዙዎች የታሰሩት ቅዳሜ እለት ሲሆን፣ ሐሙስ ነሐሴ 19/2014 ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
በዞኑ ምክር ቤት ክላስተሪንግ አደረጃጀትን ውድቅ ያደረጉትን ጨምሮ 52 ሰዎችም ለቀጣይ እስር ማዘዣ እንደወጣባቸው ተመላክቷል። ለዚህም የክልሉ ምክር ቤት ያለመከሰስ መብት ያላቸው የምክር ቤት አባላትን መብት ለማንሳት በቅርቡ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚጠራ ይጠበቃል ነው የተባለው።
በዚህም ሐሙስ ነሐሴ 19/2014 ጀምሮ ለኹለት ቀን የሚቆይ የቤት መዋል አድማ በዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤ እንደተደረገ እና ይህን ተከትሎ የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሙሉ ተዘግተው መዋላቸው ተሰምቷል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከዋዜማው ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት በድምጽ ማጉያ በየቤቱ እየዞሩ ማንም ሰው ከግልም ይሁን ከመንግሥት ሥራ እንዳይቀር ያስፈራሩ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ግን ቤቱ ቁጭ ብሎ ማሳለፉ ነው የተነገረው።
የቤት ውስጥ መዋል አድማ ሲደረግ ይህ ለኹለተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከአስራ ሰባት ቀን በፊትም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በጉራጌ ዞን መቀመጫ ወልቂጤ ከተማ አሁኑ ሰዓት ከሰብአዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውጪ ያሉ የንግድ ድርጅቶች፣ ባንኮች፣ የተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መሉ ለሙሉ እንቅስቃሴያቸውን በማቋረጥ የአንድ ቀን የሥራ ማቆም አድማ መመታቱ ይታወሳል።
የሥራ ማቆም አድማው ዋነኛ ዓላማ የዞኑ ምክር ቤት የወሰነው ውሳኔ እንዲከበር ስለመጠየቅ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል። እንዲሁም፣ እንወያይ በሚል ለስብሰባ ተጠርተው የታሰሩ ወጣቶች በመኖራቸውም ይፈቱልን ለማለት ጭምር ነው ተብሏል።
በዞኑ ከነሐሴ 12/2014 ጀምሮ ማንኛውንም ስብሰባ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ የሚከለክል አስቸኳይ ትዕዛዝ መተላለፉን እና በዚህም የንግድ ሱቆችና ተቋማትን ያለምንም ምክንያት መዝጋትና ማንኛውም ሰልፍና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የተከለከለ መሆኑ፣ ትዕዛዝ በሚተላለፉ አካላት ላይም እርምጃ እንደሚወስድ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ማስታወቁ አይዘነጋም።
ሕዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብቱን እንዲያገኝ እንዲሁም ወንጀል ሳይሠሩ የታሰሩ ወጣቶችና አመራሮች እንዲፈቱ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በማቅረብ በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነና ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጡን አስረድተውናል ሲሉም አንድ ማንነታቸው እንዲገለፅ ያልፈቀዱ የመረጃ ምንጭ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014



