ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች ያቃልላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን አገራዊ ምክክር ለማድረግ ምክክሩን የሚመራ ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል። ምክክሩን እንዲመራ ከተሠየመው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በተጨማሪ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አገራዊ ምክክሩ እውን እንዲሆን የየራሳቸውን አበርክቶ ለማዋጣት ጥረት እያደረጉ ነው።
በአገራዊ ምክከሩ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው ከሚታሰቡት ባለድርሻ አካላት መካከል ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ጉልህ አበርክቶ የሚጠበቅባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተደራጀ መልኩ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ፈጽመው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ኹለቱ ባለድርሻ አካላት በአገራዊ ምክክሩ የድርሻቸውን ሚና ለመጫወት በወኪሎቻቸው ማለትም ሲቪል ማኅበራት በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ምክር ቤት እና ፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል ስምምነት ፈጽመው በጋራ እየሠሩ ነው።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች እና በአገራዊ ምክክሩ ጉዳይ በጋራ ለመሥራት፣ ሰኔ/2014 የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው በጋራ መሥራት ጀምረዋል።
የምክር ቤቶቹ አመራሮች ከዚህ ቀደም ባደረጉት ውይይት በተለያዩ ዘርፎች የሚታዩ ልዩነቶችን የሚያሰፉ እንቅፋቶችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ጎን በመተው፣ የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት የሚሠራበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ተስማምተዋል። ይህን ተከትሎ በሲቪል ማኅበራት እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የመጀመሪያው የምክክር መድረክ ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 17/2014 ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የሲቪል ማኅበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጪው አገራዊ የምክክር ሂደት ላይ ሊጫወቱት የሚችሉት ሚና ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራትና የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት በጋራ ሊሠሩባቸው የሚችሉ ጉዳዮች እና አጠቃላይ ስለ አገራዊ ምክክር ሂደቱ ክፍተቶችና ፈተናዎች ተነስቷል። ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስብስብ ችግር ያቃልላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አገራዊ ምክክር፣ ያለፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማኅበራት ጉልህ ተሳትፎ እውን ሊሆን እንደማይችልም ተመላክቷል።
የኹለቱ ዘርፍ ምክር ቤቶች በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን ተከትሎ ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት የሚኖራቸውን ሚና በየፊናቸው በተወካዮቻቸው በኩል ለውይይት አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገራዊ ምክክሩ ያላቸው ሚና ጉልህ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ አገራዊ ምክክር በራሱ ፖለቲካዊ ስለሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ለስኬቱ ወሳኝ ነው ብሏል። ምክር ቤቱ ለውይይት ባቀረበው ሐሳብ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክሩ የዜጎችን የፖለቲካ ፍላጎት የመወከል ሚና መወጣት እንደሚችሉ ጠቁሟል።
አገራዊ ምክክሩ የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት የሚችለው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ፖለቲካዊ መተማመን ሲፈጠር መሆኑን የሚያትተው የጋራ ምክር ቤቱ ሐሳብ፣ ለምክክሩ የሚቀርቡ ፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገንቢ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ያመላክታል። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አገራዊ ምክክሩን የሚከታተል ቋሚ ኮሚቴ ከማዋቀር ጀምሮ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የምክክር መድረክ እስከ መፍጠር የሚደርሱ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ይገልጻል።
የጋራ ምክር ቤቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎቸ የውስጥ ለውስጥ ምክክር በተጨማሪ ከዓለም ዐቀፍ ተቋማትና እንደ ሰላም ሚኒስቴር ካሉ ባለድርሻ አካላት በቅርበት እየሠራ መሆኑን በውይይቱ ላይ ለተሳታፊዎች አስረድቷል። እንዲሁም በአገራዊ ምክክሩ ሂደት ላይ ቅሬታ ካላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ችግሮች የሚታረሙበትና ሂደቱን ያልተቀበሉ ፓርቲዎችን ሐሳብ የሚሰማበት ሁኔታ መፍጠሩንም አብራርቷል።
አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት አዋጅ፣ ኮሚሽኖች እስከተሰየሙበትና ከዚያም በኋለ የቀጠሉ የዝግጅት ሂደቶች ላይ ተቃውሞ ያላቸው ፓርቲዎች መኖራቸው የሚታወቅ ነው። እስካሁን በተከናወኑት ሂደቶች ላይ በፖለቲካ ፓርቲዎች የተነሱት ጥያቄዎች የግልጽነት እና የገለልተኝነት ችግር ጥያቄዎች ቀዳሚዎቹ ናቸው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በምክክር ሂደቱ ላይ የግልጽነት፣ ነጻነት እና ገለልተኝነት ጥያቄ እንዳለው የዝግጅት ሂደቱን አስመልክቶ የካቲት 19/2014 ባወጣው መግለጫ መግለጹ የሚታወስ ነው።
ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የካቲት 3/2014 ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የምክክር ኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የእጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ እና ምልመላ እንዲሁም ከሂደቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ተያያዥ ጉዳዮችን በስፋት ተመልክቻለሁ ብሏል። ከኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እስከ እጩ ኮሚሽነሮች ምልመላ መንግሥት እየሄደበት ያለው መንገድ ከፍተኛ የገለልተኝነት እና ተአማኒነት ችግር ያለበት ነው ብሏል።
ከምክር ቤቱ በተጨማሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በየግላቸው ቅሬታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አንዳንድ ፓርቲዎች ራሳቸውን ወደ ፊት ከሚካሄደው ምክክር ማግለላቸውን ገና ከጅምሩ ሲገልጹ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ቅሬታ የቀረበበት እስካሁን የነበረው ሂደት እና የተነሳው የግልጽነት ጥያቄ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሠረተ ቢስ መሆኑን የሚገልጽ ግብረ መልስ ከማግኘቱ ባለፈ በተግባር የተቀየረ ነገር አልታየም።
እስካሁን ባለው ሂደት ቅሬታውን የገለጸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሲሆን፣ የአገራዊ ምክክር አካሔዱ የገለልተኝነት ጥያቄ ያለበት ነው ብሏል። ኦፌኮ በምክክሩ ላይ ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች ተሳታፊ ካልሆኑ የምክክሩ አካል እንደማይሆን መግለጹ የሚታወስ ነው። የፓሪቲው መሪ መረራ ጉዲና (ፕ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር ከዚህ በፊት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ አገራዊ ምክክሩ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ አካላትን ካላካተተ የሚታሰበውን ውጤት እንደማያመጣና ፓርቲያቸውም ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆኑን ጠቁመው ነበር።
ሌላኛው ሂደቱን ከተቃወሙት ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ በሂደቱ የታዩ ግድፈቶች እርምት ተወስዶባቸው በሚቀጥሉት ሥራዎች እና ምዕራፎች ላይ የማይሻሻሉ ከሆነ፣ ምክክሩ እንዲያሳካልን የፈለግነውን ዓላማ አያሳካም ሲል ስጋቱን ገልጿል። አዋጁን ከማስጽደቅ ጀምሮ እስከ ኮሚሽን የማቋቋም ሂደቱ በተለያዩ ወገኖች የግልጽነት ችግር የተነሳበት ‹የአደባባይ ምስጢር ነው› ያለው ኢዜማ፣ ከፍተኛ የሆነ የግልጽነት ችግር ተመልክቻለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው።
በአገራዊ የምክክር ሂደቱ ላይ ቅሬታ የታየባቸው ክፍተቶች መታረምና እየታረሙ መሄድ መቀጠል እንዳለባቸው በውይይት መድረኩ የገለጸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት፣ የታጠቁ ኃይሎች የአገራዊ ምክክሩ አካል ሆነው መሳተፍ አለባቸው ብሎ እንደሚያምን በውይይቱ ላይ ሐሳብ አቅርቧል። ይሁን እንጂ፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሸኑም ይሁን የፌዴራል መንግሥት እስካሁን የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ እስካልፈቱ ድረስ በምክክሩ ተሳታፊ እንደማይሆኑ ከመግለጽ የዘለለ የተለየ ነገር አላንጸባረቁም።
በጋራ መሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር ስምምነት የፈጸመው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ በአገራዊ ምክክሩ ጉዳይ ገለልተኝነቱን ጠብቆ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል። ምክር ቤቱ በአገራዊ ምክክሩ ላይ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች የሚያስተባብር አስተባባሪ ቡድን አቋቁሞ ሲቪል ማኅበራት ለምክክሩ የሚጠበቅባቸውን አበርክቶ እንዲወጡ እየሠራ መሆኑን በውይይቱ ላይ አንስቷል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የኅብረተሰቡን ጉዳይ በቅርብ በመከታተል እና የሚመለከታቸው ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን በመወትወት ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ሚና እንዳላቸው በውይይቱ ላይ አንስተዋል። ዋና ዳይሬክተሩ ግልጽና ሁሉንም አካታች ያደረጉ የውይይት ባህሎችን ማዳበሩ ሰላምን ለማስፈን የምናደርገውን ጥረት በሰፊው የሚደግፉ በመሆናቸው፣ ሁላችንም ይህን ልምድ እንድናዳብር በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በተናጠል ተሠርቶ ከሚገኘው ውጤት በተጨማሪ በጋራ ቢሠራ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ጠቁመዋል። ኹለት ምክር ቤቶች አብረው ለመሥራት አቅደው የማያውቁ ተቋማት በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ታሪካዊ መሆኑን የጠቆሙት ራሔል፣ ምክር ቤታቸው ለጋራ መፍትሄ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የሲቪል ማኅበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጪው አገራዊ ምክክር ሂደት ላይ ሊጫወቱት የሚችሉት ሚና ላይ እየመከሩ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በጋራ በተዘጋጀው የመጀመሪያ የውይይት መድረክ ተሳታፊዎች ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበራት ብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማነቱ እንዲረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ኹለቱ ምክር ቤቶች በቅንጅት ለመሥራት ስምምነት ፈጥረው ወደ ሥራ መግባታቸው የሚበረታታ በጎ ጅማሮ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014



