መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብኪን/ጥበብ‹ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር›

‹ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር›

‹ለዚህ ያደረስከን ተመስገን፣ ደግሞ ለከርሞ በሰላም አድርሰን› በለሆሳስም በድምጽ ማጉያም አውጥተው የሚናገሩት ቃል ነው። እንደየ ሃይማኖቱ ፈጣሪውን ማመስገን የብዙ ኢትዮጵያዊ ደንቡ ነውና ይህን ምን አዲስ አደረገው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል። ‹‹አምና በዚህ ጊዜ የነበርንበትን የምናስታውስ እኛ ነን›› ነው መልሳቸው።

የዛሬ ዓመት ደብረታቦር ከተማ ሰላም አልነበረም። የአንድ ቤተሰብ አባላት ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ጥቂት የማይባሉ የከተማ ነዋሪዎችም በከባድ ሁኔታ ውስጥ ለማለፍ ተገድደዋል። ይህ የሆነው አሁንም እንደ አዲስ እየተቀሰቀሰ ባለውና ኹለት ዓመት ሊሞላው ኹለት ወር በቀረው የሰሜኑ ጦርነት የተነሳ ነው።

‹‹ስንት መሣሪያ ስቶኝ መሰለሽ ዛሬ እዚህ የተገኘሁት!› አለ፤ አንድ ከተማዋን በወፍ በረር ሲያስቃኘን የነበረ ወጣት አሽከርካሪ ‹‹በሕይወት መኖሬ ራሱ ይደንቀኛል።›› አከለበት።

በእርግጥ ደብረ ታቦር ከተማ ልክ የዛሬ ዓመት በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ነበረች። የቦታው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥም ወሳኝ በመሆኑ፣ እጅን አሳልፎ ላለመስጠት የተደረገው ትንቅንቅ ቀላል እንዳልነበር መገመት አያዳግትም። ደግሞም የሆነው እንደዛ ነው፤ ደብረ ታቦር የደረሰባት ችግር ቢኖርም ተላልፋ አልተሰጠችም። በብርታትና በወኔ ተዋግተው ነጻ አድርገው ሊያቆይዋት ችለዋል።

ይህን ፈተና ወዳሳለፈችው ወደ ደብረ ታቦር ተጉዘናል። የጉዟችን ተቀዳሚ ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በድምቀት የሚከበረው የቡሄ ወይም ደብረታቦር በዓል ነው። በዓሉ ሀይማኖታዊ መነሻ ያለው ይሁን እንጂ ባህላዊ እሴቱም በዛው ልክ ከፍ ያለ ነው። እናም ሀይማኖታዊ ክዋኔውን ብቻ ሳይሆን የልጆችን የቡሄ ጭፈራ፣ የሴቶች አሸንድዬ ውዝዋዜ እና ዜማ ለማድመጥ ብሎም ደብረ ታቦርን ለመጎብኘት ጓግተን ነበር።

ዋናው የጉዟችን ምክንያት ይህ ሆነ እንጂ ሌላም ነበር። ይህም በሐሳብ ወደ 1832 የሚወስድ ነው። የዛሬ 182 ዓመት ገደማ እንዲህ የሚል የትልቅ ታሪክ መግቢያ ተጽፏል። ‹‹በቀድሞው በጌምድር አውራጃ፣ የዛሬው የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ደብረ ታቦር ከተማ ነሐሴ 12 ቀን 1832 ተወለዱ።››

ይህ የታሪክ መግቢያ የማን ነው የተባለ እንደሆነ ‹ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ› የተባሉት የእቴጌ ጣይቱ ነው። እናም በእቴጌይቱ የትውልድ አካባቢ፣ እንዲሁም በእርሳቸውና በአፄ ምኒልክ የልደት ቀን በዛ አካባቢ መገኘት ልዩ ስሜትን ይፈጥራል። በደብረ ታቦር ዋዜማም እለቱን ለማሰብ ይህ ሌላ ተጨማሪና ትልቅ ምክንያት ሆኖ አልፏል።

ደብረታቦር ከዚህም በተጓዳኝ በርካታ ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደች ከተማ ስትሆን፣ ታሪካዊ ቅርሶቿ እጅግ በርካታ ናቸው’ ሰባት መቶ ዓመት የተሻገረ እድሜ ያላት ደብረ ታቦር፣ የተክሌ አቋቋም አብነት ቤት አላት’ ይህም ማስመስከሪያ ወይም በለመድነው አገላለጽ ማስመረቂያ ትምህርት ቤት ነው። ይህ ማስመስከሪያ ከታላቁ ደብረ ታቦር ኢየሱስ ከሚገኝበት ተራራ ወደታች ወደ መሃል ከተማዋ ሲወርዱ በመካከል ይገኛል።

ጋፋትም ያለው በደብረ ታቦር ነው። አፄ ቴዎድሮስ ለአገራቸው የተመኙት ዘመናዊነትና የሞከሩት ሙከራ፣ በስፍራው በታሪክ የሚነገር ሲሆን፣ በትውልዱ ግን ወደ ተግባር ሊቀየር የተቀመጠ ግብ ሆኗል። ይህንንም የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ርዕዩ አድርጎ እየሠራ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ፒኤችዴ) ይናገራሉ።

ዩኒቨርሲቲውም ራሱን ሲያስተዋውቅ፤ ‹‹በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ አማካይነት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንዱስትሪ ጥማት ተጸንሶ በተወለደበት የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር አቅራቢያ የተቋቋመ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነው።›› ብሎ ነው። መሪ ቃሉም ‹የቴዎድሮስን የእውቀት ጥያቄ የመመለስ ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን!› የሚል ነው።

እድሜው ዐስር ዓመት የተጠጋው ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የሚቀበላቸው ተማሪዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ ሄዷል። በዚህ መሠረትም አሁን ላይ ከ16 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ለእነዚህ ተማሪዎቹም በጤና ሳይንስ፣ በግብርና፣ በማኅበራዊ ሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎችም ላይ ትምህርት ይሰጣል።

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢን ባህልና እሴት እንዲጠበቅ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸው የሆነ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ያምናል። ተልዕኮውም ላይ ሳይንሳዊ ምርምርን ከአገር በቀል እውቀት በማጣመር የማኅበረሰብን ችግር በመፍታት የአገርን ሁለንተናዊ እድገት ለመወጣት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተጠቅሷል።

በደብረ ታቦር መሆን

ወደነገሬ ልመለስ። ገናን በላሊበላ፣ መስቀልን በጉራጌ እንዲሁም ጥምቀትን በጎንደር ማክበር የሚናፍቀውን ያህል፤ የቡሄ ደብረታቦር በዓልንም በደብረታቦር ከተማ ተናፋቂ ለማድረግ ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ባለው አቅም እየሠራ ይገኛል።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው ይህ በዓል፣ የደብረ ታቦር ከተማን ሥም ይዞ የሚገኝ ቦታ ስለሆነ በተለየ ሁኔታ በከተማዋ መከበር አለበት በሚል ነው፤ ‹ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር› በሚል መጠሪያ በድምቀት ይከበር የጀመረው። ከአምስት ዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲው ይህን ሐሳብ ሲያመጣ፣ የአካባቢው ትውፊት፣ ባህልና ታሪክ ከፍ እንዲል፣ እንዲመዘገብና አንዲሰነድ ብሎም ለትውልድ እንዲተላለፍ ከማድረግ አንጻር የያዘውን እቅድ ለማሳካት አልሟል።

በበዓሉ ዋዜማ በዩኒቨርሲቲው በሚገኘው ተክሌ አዳራሽ ግማሽ ቀን የቆየ፣ ሐሳብ የተንሸራሸረበት መድረክ ነበር። ከዛም ማምሻውን በ2010 ተገንብቶ የተጠናቀቀው የአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት ያለበት አደባባይ ጋር ‹ቡሄ በሉ› የወንዶች እና የሴቶች ‹አሸንድዬ› ጭፈራ ትርዒት ቀረበ። ልዩ ነበር።

- ይከተሉን -Social Media

‹‹ዋዜማው እንዲህ የደመቀ ዋናው እንዴት ሊሆን ነው?›› ያሰኝም ነበር። ይህን ጉዳይ ለማየት በከተማዋ የተገኘነው ሰዎች ብቻ ሳንሆን የሰማይዋ ላይ ፀሐይም የጓጓች መስሎባታል። ለምን ቢሉ፣ ወቅቱ የክረምት ቢሆንም እርሷ ግን ቁልቁል እያየች፣ አንዳች እንኳ በደመና ልትጋረድ ሳትፈቅድ እንደ በራች ውላ አምሽታለች።

እርግጥ ደግሞ ዋናው እለትም ከዋዜማው የሚልቅ ልዩ ቀን ነበር። የደብረ ታቦር እለት በዓሉን የሚያከብረው የክርስትና እምነት ተከታይ ምዕመንን ጨምሮ በዓሉን ለመታደም ከተለያየ አካባቢ የተገኙ ዜጎችና በርካታ መገናኛ ብዙኀን በከፍታው ላይ ከሚገኘው የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስትያን የተገኙት ማልደው ነው። የምዕራብ ጎንደር አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሰላማ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መላኩ አከበልን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ታድመዋል።

በዓሉን ለማክበር ምክንያት የሆነውና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሶ እንደሚገኘው ታሪክና ቃል፤ ‹በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው።›› የሚያሰኝ ቆይታ በተራራው ላይ አልፏል’ የተክሌ አቋቋምን ሊቃውንቱ እያዜሙና ዘመም መለስ እያሉ አሳዩ፣ አስደመጡ።

ሃይማኖታዊ የሆኑ የተለያዩ ክዋኔዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ ከዛ ባለፈ የሴቶች የአሸንዳ ጭፈራና የጅራፍ ትርዒት ዐይን ከሚስቡ በአካባቢው ከነበሩ ክስተቶች መካከል ናቸው። ከዛም ባልተናነሰ እየወረደ አካባቢውን የሚሸፍነው ጉም፣ በበዓሉ ዋዜማ ደምቃ እንደዋለችው ፀሐይ ፍጹም የበዓሉ ተሳታፊ ነበር።

መልክዓ ምድሩ ልዩ ነው። በዓሉን የተመለከቱ ትርዒቶችና ክዋኔዎችን አለፍ ብሎ ዙሪያውን ለቃኘ፤ ደብረ ታቦር ከተማ ቁልቁል ቁልጭ ብላ ትታየዋለች። ክዋኔውንም ቢሆን ከፍ ብሎ ቆሞ ለማየት የሚያስችል ተጀምሮ ያልተቋጨ ሕንጻ በበርካታ ታዳሚዎች ተሞልቶ ይታያል’ በእርግጥ ደብረ ታቦር ይህን ብቻ ብታስጎበኝ፣ ተመልካች ከሚያገኘው ደስታ በተጓዳኝ የአካባቢውንም ሆነ የአገርን ቱሪዝም በብዙ ሊታደግ የሚችል መሆኑን በዛ ስፍራ የተገኘ ሰው ልብ ማለቱ አይቀርም።

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አነጋግረኝም ይህን በተመለከተ ሲናገሩ፣ ትልቁ የአገር ሀብት ቱሪዝም መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን እየተጠቀምንበት አይደለም ብለዋል። ከሀብቶች መካከል አንደኛው ትውፊታችን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ በዛ መሠረት ደብረታቦርን ዓመት ተጠብቆ ከተለያየ አቅጣጫ ሰዎች ወደ ከተማዋ የሚመጡበት ‹ፌስቲቫል› ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በእርግጥ ደግሞ ከተማዋ ሊጎበኝ የሚችልና ለቱሪዝም የሚያግዝ ብዙ ሀብት አላት። የእድሜዋ መጠን እንዳለ ሆኖ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እንዲሁም ትውፊትን መሠረት ያደረጉ በርካታ ሀብቶች ባለቤት ናት።

በዛ ስፍራ የተገኘንም፣ ‹እውነትም ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር› ብለን ነው ከተራራው የወረድነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የደብረ ታቦር ኹነት ላይ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ ሐዋርያት እንዲሁም ከቀደሙት ሙሴ እና ኤልያስ በተገኙበት ብርሃኑን ገልጦ ነበር። ይህን ጊዜም በስፍራው ከተገኙት ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ‹በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው።› ሲል አንድ ለኢየሱስ ክርስቶስ፣ አንድ ለሙሴ እንዲሁም አንድ ለኤልያስ ቤት እንሥራ ሲል ጠይቋል።

- ይከተሉን -Social Media

ሐዋርያው ምንም እንኳ የኹነቱን ውበትና መልካምነት አድንቆ፣ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው ቢልም፤ በዛ ስፍራ አልቆዩም። ሁሉም ባለጉዳይ መንገዶች የነበሩ፣ ክስተቱም ወደፊት ለሚሆነው የሚያደርስና ከኋላ የነበረውን የሚያጠራ መተላለፊያ ነበረና፤ ከተራራው ወረዱ።

እኛም በደብረ ታቦር ኢየሱስ የተካሄደው የደብረ ታቦር በዓል አከባበር ሲጠናቀቅ ቁልቁል ወርደን ወደ መሃል ከተማዋ አቀናን። በከሰዓት መሰናዶ በዋልታ ቴሌቭዥን በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፈውንና በዓሉን ምክንያት ያደረገውን ዝግጅት ለመታደም አቀናን። ምርቃትና ቡራኬን ያካተተው የጠዋቱ ክዋኔም ‹የከርሞ ሰው ይበለን!› ተብሎ ለዓመት ቀጠሮ ተይዞ ተቋጨ።

ቁልቁል ስንወርድ የኢትዮጵያን ከፍታ እያሰብን፣ አገራችንን በከፍታ ላይ ብትሆን መልካም ነውና እንደ ሰው፣ እንደ ሕዝብ እና እንደ አገር ከፍታ ላይ ያድርሰን የሚል ምኞትና ጸሎት በየልባችን እየደገምን ነበር።

ቆይታችን ግን በዛ አላበቃም። ‹‹ሕይወቱ አልፎ ስጋው የተቀበረ ሰውን ከዓመት በኋላ መጥታችሁ ቆፍራችሁ ብትፈልጉት ሥጋውንም ሆነ አጥንቱን አታገኙትም› የሚባልበት አንድ ጥንታዊና ታሪካዊ ቦታ እንዳለ ተነገረን’ በማግስቱ ያቀናነው ወደዚያ ታሪካዊ ስፍራ ነው። የት ነው ካላችሁ፣ ሳምንት እንገናኝና እነግራችሁ አለሁ። ሰላም!


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች