የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በ2009 አድርጎት በነበረው ጥናት በኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤተሰብ ቤት ይፈልጋል፤ ሚኒስቴሩ እንደሚለው በየዓመቱ ተጨማሪ 100 ሺህ ቤት ፈላጊዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ይህም አንድ ዓመት በጨመረ ቁጥር የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱ ላይ ተጨማሪ መቶ ሺህ ፍላጎት እተደመረ ነው ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ በተለየ የቤት ችግር ሰለባ ስትሆን ከ2009 ጀምሮ የአዳዲስ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታን አቋርጣለች፤ ቀድመው የተጀመሩ 132 ሺህ ገደማ ቤቶችንም እስካሁን ገንብታ ማጠናቀቅ አልቻለችም፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ 30 ሺህ የመኖሪያ ቤቶችን በዕጣ ሐምሌ 2008 ካስተላለፈች በኋላ እስካሁን የተላለፈ ቤት የለም፡፡ አስተዳደሩ ጥቅምት 30/2011 አስተላልፋቸዋለሁ በሚል ቃል ገብቶ የነበሩ 42 ሺህ ቤቶችንም ለማይታወቅ ጊዜ አራዝሟል፡፡ ይህም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጥያቄዎችን እንደአዲስ ማስነሳት ጀምሯል፡፡
አዲስ አበባና የቤት ጥያቄ
ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከተጋረጡ ፈተናዎች መካከል ትልቁ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ነው፡፡ የነዋሪው በቤተሰብ ደረጃ የነፍስ ወከፍ ቤት ባለቤትነት እንደማይሳካ መንግሥት በቅርቡ ያሳወቀ ሲሆን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ቢያንስ የቤት ኪራይን በተመለከተ ሕጋዊ ማዕቀፍ አዘጋጃለሁ ያለውንም ቃል ሳይፈፀም ዓመታት ነጉደዋል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር ላለፉት 14 ዓመታት የጋራ መኖሪያ ቤት ልማት በማካሄድ የቤት ችግርን ለመፍታት ሞክሯል፡፡ ይሁንና ከ1997 ጀምሮ ተገንብተው የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች 183 ሺህ 221 ገደማ ናቸው፡፡ በየወሩ ከዕለት ኑሯቸው ቀንሰው እየከፈሉ ለሚቆጥቡትና ቤታቸውን ለሚያስገነቡት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተመዝጋቢዎች በዕጣ የተላለፉት ቤቶች ቁጥር ከ167 ሺህ 605 መብለጥ አልቻለም፡፡
ቀሪዎቹ ከ15 ሺህ 616 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግን ለልማት ተነሺዎች፣ ለመንግሥት ሹመኞች፣ ለመከላከያ ሠራዊት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጨረታ፣ በአነስተኛ ኪራይና በሽያጭ ተላልፈዋል፡፡ የንግድ ቤቶችም ይገኛሉ። በተመዝጋቢው ቁጠባ በሚገነቡ ቤቶች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍና መመሪያ በማውጣት ላልተመዘገቡ ሰዎች ቤት የመስጠቱ ሂደት ሕጋዊነት ጥያቄ የሚነሳበት አስተዳደሩ እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ይሁንና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግሥት ሠራተኞችና ነዋሪዎቹ የሚሆኑ አንድ ሺህ 718 የኪራይ ቤቶችን እየገነባ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
አሁን አዲስ አበባ ላይ ተመዝግበው ቤት ከደረሳቸው ይልቅ ገና በመጠባበቅ ላይ ያሉት ከአምስት እጥፍ በላይ ናቸው፡፡ አስተዳደሩም ቢሆን ተመዝጋዎቹ በጉጉት እየጠበቁኝ እንደሆነ አውቃለሁ ይላል፡፡
በቤቶች ግንባታ ላይ ምን ሲካሄድ ነበር?
አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) የከተማ ልማትና ቤቶች ሚንስትር በነበሩበት ወቅት እየተገነቡ ያሉ ቤቶችን ጎብኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ምዝገባው ቀድሞውኑ ችግር የነበረበት መሆኑን አንስተው መንግሥት አንድ ሚሊዮን ለሚሆን ተመዝጋቢ ቤት ገንብቶ የመስጠት ዕቅድም አቅምም እንደሌለው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ አዲሱ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም በዚህ ሐሳብ ይስማማል። ኅዳር 4/2011 ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ቤቶችን በግል የቤት አልሚዎችና በመንግሥት ትብብር በፍጥነትና ብዛት ገንብቶ ለነዋሪዎች ለማስረከብ በሚያስችሉ አሠራሮች ዙሪያ ከቤት አልሚዎች ጋር መክሯል፡፡ ይሁንና በዚህ ዘርፍ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች መነሻ ካፒታላቸው 50 ሚሊዮን ዶላር ይሁን መባሉ በባለሃብቶቸ በኩል ቅሬታን አሰነስቶ ነበር፡፡
ቤት መገንባቱ ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራሉን መንግሥት ሳይሆን እኔን ነው ሲል የነበረው የአዲስ አበባ አስተዳደር ግን ለሁሉም ተመዝጋቢዎች ቤት እገነባለሁ የሚል ተስፋን ሲሰጥ ነበር፡፡ ድሪባ ኩማ ከንቲባ በነበሩ ጊዜም በየዓመቱ እስከ 50 ሺህ አዳዲስ ቤቶችን ግንባታ መጀመር የሚል ዕቅድ አስቀምጠው ነበር፤ አልተሳካም፡፡ የበጀት እጥረት አላሰራ አለኝ ላለው አስተዳደር ለቤት ግንባታ እንዲውል በ2009 ዓ.ም 16 ቢሊዮን በ2010 ደግሞ 20 ቢሊዮን ብር ተበጅቶለትም ግንባታዎችን አልጀመረም፤ የጀመራቸውንም አልጨረሰም። በ2010 እጀምራቸዋለሁ ያለውን 25 ሺህ ቤቶች መጀመሩ ቀርቶ እስከ 2009 ሰኔ ወር በግንባታ ላይ ያሉ ቤቶችን አፈፃፀም 80 በመቶ ለማድረስ ያለመው አስተዳደሩ አንድ ዓመት ዘግይቶም 80 በመቶ አለማድረሱን የቢሮው የዕቅድ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ቤቶች ገና ወደፊት 80 በመቶ ደርሰው ይተላለፋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ሌላው ችግር የተላለፉ ቤቶች ላይ የመሠረተ ልማት አለመሟላት ነው፤ የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ያስጠናው ጥናት በቤት ዕድለኝነታቸው የተደሰቱ ሰዎች ቤታቸው ሲገቡ ባጧቸው የመብራትና ውሃ እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማት አቅርቦቶች እየተማረሩ እንዳሉ የሚያሳይ ነው፡፡
ጥቅምት 30 ዕጣ ይወጣባቸዋል ተብሎ ላልታወቀ ጊዜ ከተራዘሙት 42 ሺህ ቤቶች ውስጥም ከታህሳስ እስከ ሰኔ 2011 መሠረተ ልማታቸው የሚሟላላቸው ሲኖሩ ኮዬ ፈቼ ላይ ዕጣ የሚወጣባቸው ቤቶች ላይ ግን መሠረተ ልማት ማሟላቱ እስከ ዛሬ ሁለት ዓመት ድረስ ሊቆይ እንደሚችል የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጀማል ሃጂ ይገልጻሉ፡፡
ቤት የሚጠባበቁት አዲስ አበቤዎች እጣ ፈንታና መፍትሔ
ባለፉት ሦስት ዓመታት አዳዲስ ግንባታዎች አለመጀመራቸውን ተከትሎ ተመዝጋቢዎች ዕጣ ፈንታ ምንድነው የሚል ጥያቄ ከአዲስ ማለዳ የቀረበላቸው የአዲስ አበባ ቤቶቸ ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሌላኛው ምክትል ኃላፊ ዘሪሁን አምደማሪያም ‹‹አዳዲስ ግንባታዎች መጀመራቸው አይቀርም›› ብለዋል፤ መቼ ለሚለው ግን ቁርጥ ያለ ምላሽ አልሰጡም፡፡
ችግሮች የበዙበት የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ መጨረሻ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር መንግሥት ፕሮግራሙን የጀመረው ለሥራ ዕድል ፈጠራና ግንባታ ዘርፉ እድገትም ጭምር በመሆኑ አይቋረጥም ብሏል። ጎንደር ለይ ለተካሄደው የከተሞቸ ፎረም አዘጋጅቶት የነበረው ሰነድ ግን በመንግሥት በጀት የጋራ መኖሪያ ቤትን ማስቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ያትታል፡፡ ቤት ገንብቶ ሊያስረክብ ነዋሪዎችን መዝግቦ የሚያስቆጥበው የአዲስ አበባ አስተዳደርም አይቋረጥም ሲል ኖሮ ዛሬ ላይ ለተመዝጋቢዎች ቤት ለማዳረስ የሚስችለኝን ሌላ ስልት ከሚኒስቴሩ ጋር እያማተርኩ ነው ብሏል። እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ዘሪሁን ገለጻ ስልቶቹ ቀድሞ ቤት ሊደርሳቸው የሚችሉ ሰዎችን እየለዩ በግንባታው እንዲሳተፉ ማድረግንም ይጨምራል፡፡ በሌላ በኩል በማኅበራት እየተደራጁ ቤት የመገንባትን ሥራ መስከረም 2010 ላይ በሚጀመሩ 20 ሺህ የመንግሥት ሠራተኞች የማኅበራት ቤት አሟሻለሁ ብሎ የነበረው አስተዳደሩ መርሃ ግብሩን ሳይጀምረው አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ አሁንም ግን ይህ የቤት ልማት አማራጭ እንዳለ መሆኑን የሚናገረው ቢሮው መቼና እንዴት ያስጀምረዋል የሚለውን ግልጽ ማድረግ አልቻለም፡፡ መርሃ ግብሩ መቼ እንደሚጀመር ባይታወቅም የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎችም እየተደራጁ የራሳቸውን ቤት እንዲገነቡ ያለመ ነው፡፡
አሁን ባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች አዝጋሚ ግንባታ አካሄድ ሲሰላ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ቤት እየጠበቀ ያለውን ተመዝጋቢ የቤት ባለቤት ለማድረግ 50 ዓመታትም አይበቁም፡፡ በምሳሌ ካየነው በ14 ዓመት 168 ሺህ ቤት ገደማ ብቻ ያስተላለፈ አስተዳደር 974 ሺህ ተመዝጋቢን የቤት ባለቤት ለማድረግ 81 ዓመት ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ በ2005 ምዝገባ ወቅት አንድ ተመዝጋቢ ቢያንስ 18 ዓመት መሆን ይጠበቅበት ነበር፤ ስለዚህ በወቅቱ የተመዘገበ የ18 ዓመት ወጣት አሁን 24 ዓመት ሞልቶታል፡፡ በዚህ ስሌት የመጨረሻው በእድሜ ትንሹ ተመዝጋቢ ቤት የሚያገኘው የ105 ዓመት አዛውንት ሆኖ ነው ማለት ነው፡፡
የዜጎቼ በሕይወት የመኖር የእድሜ ጣሪያ 65 ዓመት ደርሷል የሚለውን የመንግሥት መረጃ ስንመለከት ደግሞ የተለየ ስልት ተፈልጎ የቤት ግንባታው ካልፈጠነ በስተቀር አብዛኛው ተመዝጋቢ ቤቱ ሳይደርሰው ሕይወቱ ያልፋል እንደማለት ነው።