መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየሸኔ ታጣቂ በአፋር ክልል በከፈተው አዲስ ጥቃት ንጹሐንን እየገደለ መሆኑ ተሰማ

የሸኔ ታጣቂ በአፋር ክልል በከፈተው አዲስ ጥቃት ንጹሐንን እየገደለ መሆኑ ተሰማ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሸኔ ታጣቂ ቡድን በአፋር ክልል ቡርቃ ከተማ አዲስ የጥቃት ዘመቻ መጀመሩንና ንጹሐን ሰዎች እየተገደሉ መሆኑን  የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች በገለጹት መሠረት፤ ሸኔ ጥቃቱን የከፈተው ባሳለፍነው ነሐሴ 18/2014 ነው። ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ የቡርቃ ከተማ ነዋሪዎች እየተገደሉ ነው ያሉት ምንጮች፤ ‹‹ድሮም ከሕወሓት ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። አሁንም ጥቃቱን በተመሳሳይ ጊዜ ከፍተዋል።›› ሲሉ ተናግረዋል።

ቡድኑ መነሻውን ባቲ አካባቢ ስለማድረጉ ተጠቅሷል። እስካሁን በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ በኦሮሚያ ያለውን ነዋሪ ጨርሶ ወደ አፋር ክልል በመዞሩ መንግሥትም አስፈላጊውን እርምጃ ሊጀምር ይገባል ብለዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ከዚህ በፊት በቡርቃ ከተማ ጥቃት ሰንዝሮ ንጹሐን ላይ ጥቃት አድርሶ እንደነበር ያስታወሱት የመረጃ ምንጮች፤ አሁን ጥቃት የከፈተው ሲዘጋጅ ቆይቶ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገልጻሉ።

እስካሁን የሟቾች ቁጥር በትክክል አልታወቀም የተባለ ሲሆን፤ ታጣቂ ቡድኑ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መጠነ ሰፊ ጥቃት እያደረሰ እንደሚገኝ ማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል፣ ታጣቂ ቡድኑ ከቀናት በፊት በምዕራብ ወለጋ ዳሪሙ ወረዳ በመግባት በአራት አቅጣጫ ጥቃት የመክፈት ሙከራ አድርጎ እንደሰነበተም የተጠቆመ ሲሆን፤ በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስ ባደረገው መከላከል ወደ ደንቢ ደሎ ያፈገፈገ ቢሆንም በድጋሚ ለመግባት ዳር ዳሩን ይዞ እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በሸኔ ተከፈተ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ወደ አፋር ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አሕመድ ካሎይታ የተደረገው ሙከራ ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም።

በሌላ በኩል፣ ሽብርተኛ የተባለው የሕወሓት ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ በከፈተው ጦርነት፣ በአማራ እና በአፋር ክልል ንጽሐን ላይ ጉዳት ማድረሱን የስፍራው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው ነሐሴ 18/2014 ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ የትግራይ ክልል ሥፍራዎችን አልፎ ተኩለሽ እና ዞብል በሚባሉ ቦታዎች ጦርነት መክፈቱ የተነገረለት ሕወሓት፤ በነበረው የአጭር ጊዜ ጥቃት ገና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንጹሐንን ስለመግደሉ የዐይን እማኞች ገልጸዋል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማችን አይጠቀስ ያሉ የራያ አላማጣ ነዋሪዎች፣ ታጣቂ ቡድኑ መተኮስ የማያውቁ ሰዎችን በማስገደድ ወደ ጦርነት እንዲገቡ ትእዛዝ ማውረዱንና፤ ትእዛዙን አንቀበልም ብለው የሞገቱን ንጹሐን የግድያ ጥቃት እንደፈጸመባቸው ጠቁመዋል።

አላማጣ ከተማ የትግራይና አማራ ክልል ወሰን አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ፤ የአማራና የትግራይ ተወላጆች በጋራ የሚኖሩበት ከተማ መሆኑ ይታወቃል። ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት ያደረሰው በቦታው የሚገኙ አንዳንድ የአማራ ተወላጆችን ከጎኑ ሆነው እንዲታኮሱ ሲያስገድድ ‹‹ወገናችንን አንዋጋም›› ብለው በመሞገታቸው ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባደረገው የተኩስ አጸፋ የተኩለሽና ዞብል እንዲሁም የዋግ አካባቢዎችን ለቆ ወደ ኋላ አፈግፍጓል ነው ያሉት።

ሕወሓት በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን፤ በአፋር ክልልም ዞን አራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰሞኑን ትንኮሳ አድርሶ እንደነበር የአዲስ ማለዳ ምንጮ ሳይናገሩ አላለፉም።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች