መነሻ ገጽዜናወፍ በረር ዜናበኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚፈጸም ክፍያ በሳምንት 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተነገረ

በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚፈጸም ክፍያ በሳምንት 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተነገረ

የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚፈጽሙት ክፍያ በሳምንት 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ማስታወቁ ተነግሯል።

ይህን ማወቅ የተቻለው የገንዘብ ሚኒስቴር ከፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ጋር በኤሌክትሮኒክ ክፍያ አፈጻጸም ላይ ባደረገው ውይይት ነው ተብሏል።

በኢንተርኔት ባንኪንግ የተከናወኑ ክፍያዎች በጥቅምት 2014 መጀመሪያ በሳምንት 900 የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሳምንት ከ12 ሺሕ በላይ ክፍያዎች በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ስልት እየተፈጸሙ እንደሆነ ተመላክቷል።

በውይይቱ ከጥቂት መሥሪያ ቤቶች በስተቀር ሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ስርዓቱን በሥራ ላይ እንዳዋሉና አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ክፍያዎችን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ማከናወን ደረጃ ላይ መድረሳቸው ተገልጿል። በርካታ መሥሪያ ቤቶችም 50 በመቶ ክፍያዎችን በኤሌክትሮኒክ ክፍያ በማከናወን ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክ ክፍያውን መጠቀም ከጀመሩ በኋላ ጥቅሙን እና አስተማማኝነቱን በመረዳት ክፍያዎቻቸውን በቼክ፤ በጥሬ ገንዘብ እና በደብዳቤ ከማከናወን ይልቅ ወደ ኤሌክትሮኒክ ክፍያዎች ዘዴ እያዘነበሉ መሆናቸውም ተዘግቧል።

በሌላ በኩል ወደ ስርዓቱ አለመግባት፤ የሂሣብ ሪፖርትና የመንግሥት ሌተር ኦፍ ክሬዲት (L/C) የአፈጻጸም ሪፖርት በወቅቱ አለማቅረብ፣ ለመንግሥት ገቢ መደረግ ያለበትን ገንዘብ በወቅቱ ያለማስገባት፤ ዓመታዊ የጥሬ ገንዘብ ዕቅድን በአግባቡ ያለማቀድና ከተደገፈው የጥሬ ገንዘብ ዕቅድ በላይ የመጠየቅ ችግሮች መኖራቸው ተስተውሏል።

በአጠቃላይ የመንግሥት የደመወዝ፤ የግዢና የአገልግሎት ክፍያዎችን በኤሌክትሮኒክ ክፍያ መፈጸም ቀልጣፋ፤ ግልጽና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት ከመስጠቱም ባሻገር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያሻሻል መሆኑ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

የፌዴራል መንግሥት የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 71/2013 አምና የወጣ ሲሆን ከ2014 በጀት ዓመት ጥቅምት ወር ጀምሮ የክፍያ ስርዓቱ ትግበራ መጀመሩ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች