የኢትዮጵያ እግር ኳስ – በደኅንነቱ ዋዜማ

0
872

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከወትሮው በተለየ አዲስ ስርዓት ይዞ እንደሚካሔድ ከተሰማ ቀናት አልፈዋል። ይህም ክለቦች ራሳቸውን ማስተዳደራቸውና ይህንንም በተመለከተ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር መፋታታቸው ነው። ታድያ ባለሙያዎችና እግር ኳስ ጉዳይ ተንታኞች ሲናገሩ፤ ለውጡን በአግባቡ መምራት የሚችል አቅምና የክለቦች እርስ በእርስ መግባባት ካለ፤ እስከ ዛሬ የእግር ኳስ አፍቃሪውንና ተመልካቹን ያሰለቹ የእግር ኳስ ጣጣዎች ይቀረፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከቢሮ እስከ ስታድየም
የኢትዮጵያ እግር ኳስ በመጫወቻ ስታድየሞች እስከ አስተዳዳሪዎቹ ቢሮ ድረስ ውዝግብ አጥቶት አያውቅም። በዛውም ላይ ውጤት ማጣት፣ የፖለቲካና ጽንፈኝነት ጣልቃ መግባትና መሰል ሁኔታዎች ነገሩን አባብሰውታል። በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጓዳ ያሉ ጥቃቅን የሚመስሉ ችግሮች፤ በአደባባይ በደጋፊዎች መካከል በጉልህ ይታያሉ። ይህን ችግር ለመቅረፍ የሚችለው ማን እንደሆነና ወደማን አቤት እንደሚባል ግራ የገባበት ጊዜም ነበር።

የክልልና የብሔር ጽንፍኛ አስተሳሰብ ጸንቶ እግር ኳሱን ከመበከሉ አልፎ፤ ደጋፊዎች የሚደግፉትን ቡድን ለማበረታታት የትም መሔድ የማይችሉበት፣ አልፎም ባለሜዳው ቀድሞ ውጤቱን የሚወስንና የሚያውቅበት፤ ዳኞችም ቢሆን ስለደኅንነታቸው ሲሉ እንዲያደሉ የሚገደዱበት ነበር። ‹‹ኅብረ ስድብ›› የሚደመጥባቸው ስታድየሞችና የተለያዩ ክለቦች ደጋፊዎችም ለመገዳደል የሚፈላለጉባቸው ሁኔታዎች መበራከታቸው አሳሳቢ ደረጃ ደርሶ ቆይቷል።

ይህ ተመልካች በየሜዳው የሚያየው ትዕይንት ሆኖ በዜና አውታሮች የሚሰሙ የፌዴሬሽኑ ውስጣዊ ውዝግቦችም ቀላል አልነበሩም። የ2012 ጨዋታዎች ሳይጀምሩ እንኳ፣ ተሳታፊ ቡድኖችን 24 እናደርሳለን የሚል ውሳኔ ተሰጥቷል። ‹‹የቸገረው…›› የሆነበት ፌዴሬሽኑ በክለቦች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመቅረፍም ጸበኛ ክለቦች በግጥሚያ እንዳይገናኙ ማድረግን መፍትሔ አድርጎ አስቀምጧል። የጸብ ምንጭ ነው ብሎ በማመንም አንዳንድ ክለቦች ስማቸውን እንዲቀይሩም ትዕዛዝ አስተላልፏል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 15 በስፖርት አምድ ‹‹አወዛጋቢው መዋቅር በተሻረበት ዝግ ስብሰባ ምን ተባለ?›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ዘገባ፣ ይኸው ጉዳይ ተነስቷል። በዛውም ላይ የእግር ኳስ ክለቦቹ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ አልዋጥ ብሏቸው ነገሩን ወደ መንግሥት በመውሰዳቸው፣ ሸምጋይ ሆኖ የገባው የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ተሳታፊ ቡድኖች 16 ሆነው እንዲቆዩና ያልተጠና መዋቅር ተግባራዊ እንዳይሆን ብሏል። ይህ እንግዲህ ገና ጨዋታዎች ሳይጀመሩ የሆነ ነው። እናም በድምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በሜዳም ሆነ በቢሮ ‹‹ጭር ሲል አልወድም›› ጸባይ አለበት።

በደኅንነት ዋዜማ
የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካበቃ በኋላ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይቀርብ የነበረው ሃሳብ፣ ሁሉም ክለቦች ጨዋታዎችን በያሉበት እንዲካሒዱ የሚል ነበር፤ በአዲስ አበባ ያሉ ክለቦችም በአዲስ አበባ ተወስነው እንዲጫወቱ።

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ፕሪምር ሊግ ክለቦች ውድድር አመራር ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ (ሼንቶ)፤ ይህን ነገር አስረድተዋል። ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሲናገሩም፤ አስቀድሞ በውድድሩ ለሚከሰቱና ለተከሰቱ ችግሮች በአግባቡ መፍትሔ አልተሰጠም የሚል የግል አቋም አለኝ ብለዋል። ሜዳው ላይ ከሚታየው ችግር ባለፈ በክለቦች ውስጥ ያሉ በርካታ ችግሮች ለዚህ መነሻ ሆነዋል። ‹‹በተለይ 2012 የምርጫ ዘመን ስለሆነና ፖለቲካ ገብቶ ኳሱ ጭራሽ ደም እንዳያፋስስ በየክልል እናድርገው ብለን ነበር።›› ሲሉም መቶ አለቃ ፈቃደ ገልጸዋል።

በፌዴሬሽኑ በኩል ግን ለአንድ ዓመት መለያየትም ጥሩ አይደለም የሚል መልስ ተሰጠ። አንደኛ ዲሲፕሊንን በተመለከተ በሚወሰዱ እርምጃዎች ቆፍጠን ማለት ይሻላል፤ ከዛም አልፎ እንደውም ክለቦች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ሲል ተዋቸው።

በዚህ የፌዴሬሽን ሀሳብ መሠረት ታድያ ጨዋታው እንደነበር እንዲቀጥል፣ እያንዳንዱ የክልል ርዕሰ ብሔር ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ተባለ፤ ይህም ከደኅንነት ጋር የተያያዘ ነው። ተጫዋቾች ተዘዋውረው ሲጫወቱ፣ ደጋፊዎችም አብረው ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ሕግና ደንብን እንዲያከብሩና በደረሱበትም ከሕግና ስርዓት እስካልወጡ ድረስ እንዳይከለከሉ። ስታድየም ሲገቡም ቦታ ተሰጥቶአቸው በአግባቡ እንዲደግፉ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፤ ከዚህ አልፎ ዳኞች ደኅንታቸው ተጠብቆ ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲሠሩ ለማስቻል ክልሎች ኃላፊነት እንዲወስዱ ያደርጋል፤ ደብዳቤው። ይህን የማያደርጉ ከሆነ የክልሉ ቡድኖች በሊጉ ተሳታፊ አይሆኑም።

መቶ አለቃ ፈቃደ ቀጥለው ሲገልጹ፤ ክለቦችም በሃይማኖት፣ በጎጥና በፖለቲካ እንዳይረብሹ የፊፋ ሕግ፣ የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ያስገድዳቸዋል። ይህን አሻፈረኝ ብለው የጸብ ምንጭ ከሆኑ ግን ከሊጉ ይሰናበታሉ። ይህ ዓይነቱ ውሳኔ ክለቦች ራሳቸውን በሚያስተዳድሩበት መዋቅር ስር ለድርድር የማይቀመጥ መሆኑንም ነው መቶ አለቃ ፈቃደ የጠቀሱት። ‹‹የሕግ ችግር የለም፤ ችግሩ ማፈጸም ላይ ነው። ሙስናም ነበር›› ሲሉ፤ በአዲሱ አወቃቀር ግን ይህን ለመቅረፍ እንደሚሠራ ጠቅሰዋል።

የስፖርት ጋዜጠኛውና ተንታኙ ዐቢይ ወንድይፍራው በበኩሉ፣ ባደጉ አገራት የሊግ ውድድሮችን የክለብ ባለቤቶች እንደሚያስተዳድሩት ይናገራል። ‹‹የራሳቸው ድግስ ስለሆነ ከድግሱ የሚገኘውን ለመካፈልና ወደፊት ለመቀጠል የሚያስፈልገውን ለማድረግ ዋናው ባለድርሻ ስለሆኑ እድሉን ይሰጣቸዋል። ይህም ከውድድሩና ውድድሩ ከሚካሔድበት መንገድ ጋር የሚገናኝ ነው።›› ሲል ይገልጻል።

የዛሬ 4/5 ዓመት ቡድኖች ይህን ጥያቄ አቅርበው እንደነበርና ፌዴሬሽኑ በድንገት ‹‹እሺ ውሰዱልኝ›› ብሎ እንደነበር ያስታወሰው ዐቢይ፣ አሁን ላይ ውሳኔውን ተቀብለው ወደ ተግባር የገቡት ከቀድሞው በተለየ ምን ያህል ዝግጁ ቢሆኑ ነው የሚል ጥያቄ አያይዞ ያነሳል።

የለውጡ ጥቅሞች
ቡድኖች ራሳቸውን ማስተዳደራቸው ለቡድኖች ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ ይታመናል። ክፍያን በተመለከተ ገቢውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በመስማማት ክለቦች መከፋፈል መቻላቸው የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። ይህ ዓይነቱ እድል ለአገራችን የእግር ኳስ ክለቦች እንዳልነበረ የሚያወሳው ዐቢይ፣ ሁሉን በባለቤትነት የያዘውና ተጠቃሚም የነበረው ፌዴሬሸኑ ነበር ይላል።

‹‹አሁን ክለቦች የራሳቸውን ድግስ ራሳቸው እንዲያዘጋጁ ነው የተደረገው›› ሲል የገለጸው ዐቢይ፣ ከተዘጋጁበትና በትክክል በባለቤትነት መምራት ከቻሉ፣ እስከአሁን ገንዘብ ሲበላ የነበረው ሊግ ገንዘብ አምጪ ይሆናል ብሏል። ለምሳሌ ይህን አነሳ፤ በአንድ ቡድን የሚጫወት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ተጫዋች እስከ 250 ሺሕ ብር ደሞዝ ይከፈለዋል። በውድድር ዓመቱም ቡድኖች ብዙና የተለያየ ወጪ ያወጣሉ። ታድያ አሸናፊው ቡድንም በተመሳሳይ በብዙ ድካም፣ ብዙ ወጪ አውጥቶና ለፍቶ አሸናፊ ሲሆን የመጨረሻ ሽልማቱ 150 ሺሕ ብር ገደማ ነው። ይህ ማለት የአንድ ከፍተኛ ተጫዋችን ደሞዝ እንኳ መክፈል የሚያስችል አይደለም።

ይህ የሆነው ፌዴሬሽኑ በተለያየ ምክንያት በሥራ ማስኬጃም መልክ ብዙ ገንዘብ ወጪ ስለሚያደርግ ነው። ክለቦችም እንደዛው ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ገንዘብ ያወጣሉ። ይህም ሁሉ ታድያ ቡድኖች ራሳቸውን ሲመሩ ያስቀሩታል ሊባል የሚችቸል ችግር ነው። ከዚህ በተረፈ እንደ ዐቢይ ገለጻ፣ በቡድኖች መካከል ያለው ህብረት ሊጨምር ይችላል። እኩል የሚያተርፉበትና የሚከስሩበት ሊግ ከመጣ፣ ይህን ህብረት ሊያመጣላቸው የሚችል ነው።

ከዛ ውጪ ፌዴሬሽን ይህ ሥራ ሲነሳለት ትልቁ ሥራውን አዲስ ትውልድ በማውጣት፣ አቅም በማየት ላይ ያደርጋል። ምንአልባት በሊጉ ሊያገኘው የሚችለውን ብዙ ገንዘብ ማጣቱ ላያስደስተው ቢችልም፣ ወደ ትክክለኛ ሥራው የሚመልሰው እርምጃ ነው፤ እንደ ዐቢይ ገለጻ።

ለውጡ ነውጥ እንዳያመጣ
ይህ ሁሉ ጥቅም በለውጡ እንዲገኝ ግን የቡድኖች ዝግጅት ወሳኝ ነው። ዐቢይ እንዳለው ከዚህ ቀደም በጋራ በመጣባቸው ጉዳይ ካልሆነ ቡድኖች እርስ በእርስ ሲስማሙ አይታዩም። አሁን ግን መስማማትና በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በቡድን መሪዎች በኩል ራስን ማስተዳደር ምን ማለት እንደሆነ እኩል መረዳት ላይ መድረስ መቻል አስፈላጊ ሲሆን፤ በአንጻሩ በጋራ አስተዳደሩ የተወሰኑ ቡድኖች ተጽእኖ ፈጣሪ ሆነው ጎልተው ሊወጡ እንደሚችሉም ያነሳል። ይህ ሁሉ ታድያ በአግባቡ ካልተያዘ መዘዙ ብዙና ከቀደመው የባሰ መሆኑ አይቀርም። ‹‹የበለጠ ሊያስቸግርና ፈተና ላይ ሊጥል ይችላል፤ ጉዳቱ ይብሳል።›› ዐቢይ ሲናገር።

‹‹ውጤት ያመጣ ከሆነ እንሞክረው ነው። በራስ መተዳደር ለሊጉ አዲስ ነገር ነው።›› ያሉት መቶ አለቃ ፈቃደ በበኩላቸው፣ ሒደቱ ቀላል እንደማይሆን ይናገራሉ። ነጻነት ሲሰጥ ጠያቂው ስለሚበዛ በደንብና አሠራር ላይ ሕጉ ለማንም ወደኋላ ሳይል እንዲተገበር በማድረግ ይሠራል ሲሉ ይናገራሉ። ከዛም አልፎ የእግር ኳስ ሜዳዎችን ባለሜዳዎች እንዲያስተካክሉ፣ ስሜታዊ ለሆነ ደጋፊ የተነጠፉ የሚመስሉ ሜዳዎችን የከበቡ ድንጋዮች እንዲነሱና እንዲጸዱ፣ አጥሮች እንዲበጁ፣ መታጠቢያ ክፍሎች እንዲስተካከሉ ለማድረግ አዲሱ መዋቅር የፍተሻ ሥራውን እያከናወነ ነው ብለዋል። መስተካከልም ሆነ ማስተካከል ያልቻሉ ሜዳዎች እገዳ ይጣልባቸዋል፣ በሜዳቸው ጨዋታ አይደረግም።

ከዛም ውጪ የብሔራዊ ቡድን ግጥሚዎች ሲኖሩ፣ የጊዜ ሰሌዳው ቀድሞ በፊፋ የሚታወቅ በመሆኑና በዛ መሠረት ከሳምንት ያልዘለለ ቀን ይሰጣል። ያለ አግባብ ተጫዋጮች ከ20 ቀናት በላይ በሆቴል እንዲቀመጡ ይደረግ የነበረውም ይቀራል ብለዋል። ‹‹ከፊፋ ሕግና ደንብ ውጪ ግማሽ ቀን እንኳ ብትሆን አንሰጥም። ውድድሩ በተከታታይ የሚደረግ ይሆናል።›› ሲሉ የተናገሩት መቶ አለቃ ፈቃደ፣ አንድ ተጫዋች ጥሩ የሚሆነው ብዙ ጊዜውን ሜዳ ላይ ሲያሳልፍ ነውና መጠጥና ጭፈራ ቤት ለማንም አያዋጣም ብለዋል።

ሁሉም ክለቦች ታድያ ለዚህ ዝግጁ መሆናቸውንና መቶ በመቶ መስማማታቸውን መቶ አለቃ ፈቃደ ገልጸዋል። ታድያ ግን ቡድኖች ንቁ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። ‹‹እንዳለፉት ዓመታት የመብት ጥያቄ ብቻ ይዞ መምራት አይቻልም፤ ግዴታም አለ፤ አንዱና ትልቁ ደግሞ ዲሲፕሊን ነው።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ቀንደኛ ደጋፊ የሆነው ሳሙኤል ባጫ በበኩሉ፤ እግር ኳሱ ከዘርና ከፖለቲካ እንዲሁም ከራሱ ከመንግሥት ነጻ ቢሆን ይመኝ ነበር። እናም ቡድኖች ራሳቸውን ማስተዳደራቸው ኳስን ያሳድጋል ብለው ከሚያምኑት ጎራ ነው። በዚህ ውስጥ ተጫዋች በዘመድ መቀጠሩ ቀርቶ ብቃት ያላቸው ጥሩ ተጫዋቾች እንዲወጡ ያስችላል ሲልም ያምናል።

ክለቦች በዲሲፕሊን
የክለቦች ደጋፊዎች እግር ኳስ ሊፈጥር ከሚችለው ስሜታዊነት ላይ ሌላ አጀንዳ አክለው ሜዳዎችን ጦር ሜዳ ሲያደርጓቸው ይስተዋላል። ሳሙኤል እንደሚለው ከሆነ ደጋፊዎች ላይም መሠራት አለበት። ሁሉም ደጋፊዎች ጥሩ ናቸው ማለት አይቻልም፤ በተቻለ መጠን ደግሞ በማህበራዊ ገጾች የሚለቀቁ ሃሳቦችን መቀበል የለባቸውም። ‹‹ደጋፊ በሰማው ሳይሆን ያየውን ነው ማመን ያለበት›› ያለው ሳሙኤል፣ ከዛ ውጪ ጠጥተው ነው ወደ ሜዳ የሚገቡ ላይ ጨዋታ ባለ ቀን መጠጥ ቤቶች አካባቢ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ነው።

ዐቢይ በበኩሉ ዲሲፕሊንን በሚመለከተ አሁን ቡድኖች ድግሱ የራሳቸው ስለሆነ፣ ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ ቀጥታ የሚያገኘው እነርሱን ስለሆነ እንዲረበሽ አይፈልጉም ይላል። ‹‹በፊት ሌላ ዳኘን የሚሉት አካል አለ፤ አሁን ግን ተስማምተው የሚያቆሙትና ውክልና ያለበት ነው የሚሆነውና አንዱ ረባሽ አንዱ አስታራቂ አይሆኑም።›› ሲል ገልጾታል።

በአዲሱ መዋቅር ሕግና ደንቡን በተመለከተ ሁሉም ነገር ለውድድር እንዲመች ይሆናል እንጂ ቡድኖች መሠረታዊ ከሆኑ ሕጎችና ደንቦች ያፈነገጠ ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። ተስማምተው የሚያወጡት በመሆኑም ከዲሲፕሊን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ስርዓት ይኖራል።

የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስፖርት ጋዜጠኛ ብርሃን ፈይሳ በበኩሏ፤ ቡድኖች አሁን ላይ በተለይ ከዲሲፕሊን እና ቅጣት ጋር በተያያዘ ቅሬታ ለማሰማት አይመቻቸውም ባይ ናት። ቡድኖች በፌዴሬሽን ስር በሚተዳደሩበት ጊዜ አንዴ የተጣለ ቅጣት ሲሻርና ሲለወጥ፣ በገንዘብ የሚደረግ ቅጣት በመሆኑም ቡድኖች በቀላል ሲያልፉት ይስተዋል ነበር ትላለች። አሁን ግን ለራሳቸው ሲሉ ይሠራሉ።

ከዛ ባለፈ ብዙውን ጊዜ ደጋፊን የሚያነሳሱትና ለብጥብጥ የሚጋብዙት ራሳቸው ተጫዋቾች መሆናቸውን ትጠቅሳለች። ይህን በተመለከተም እንደ መከላከያ ያሉ ቡድኖች ራሱ ተጫዋቹን በመቅጣት እንዲሁም ቡድኑም በዲሲፕሊን እንዲቀጣው የሚደረግበትን አሠራር ታወሳለች። ፌዴሬሽኑም በየዓመቱ ከቅጣት የሚያገኘው ብር ከፍ ያለ መሆኑ ቅጣቱ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ ብቻ ለመሆኑ ምስክር ነው። ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ይንቀሳቀስ የነበረው ይህ ገንዘብ ታድያ ቡድኖች ለቅጣት ሲከፍሉም ብዙ የሚሰማቸው አልነበረም። አሁን ግን የራሳቸው ኃላፊነት ስለሚሆን ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የኮሚቴው ሊቀመንበር መቶ አለቃ ፈቃደ፣ ‹‹ተጫዋቾች መጫወት ሲያቅታቸው ነው ረብሻ የሚያስነሱት።›› ይላሉ፤ ለዛም ነው ሜዳ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመጨመርና ጨዋታዎችንም በተከታታይ የማድረግ እቅድ የተያዘው። ከዲሲፕሊን ጋር በተያያዘ በሚሰጡ ውሳኔዎችና እርምጃዎች ላይ መደራደር እንደማይኖርና ሕግና ስርዓቱ በአግባቡና በትክክል ተፈጻሚ እንደሚሆንም ሊቀመንበሩ ደጋግመው ገልጸዋል።

በድምሩ
የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዚህ ለውጥ መሠረት ሊከናወን ብሔራዊ ቡድኑ ያለበትን ጨዋታ እንዲሁም የሲቲ ካፕ ጨዋታ መጠናቀቅን የሚጠብቅ ይሆናል። ይህም ጥቂት እንዲራዘም የገፋው ሲሆን ለአዲሱ ኮሚቴ ዝግጅት ጊዜ እንዲያገኝ እድል የፈጠረም ይመስላል። ያም ሆነ ይህ እንደ ዐቢይ ሁሉ ለውጡን አድንቆ ግን ደግሞ ስጋትም የሚታየው የእግር ኳስ ማህበረሰብ፣ እንደ ሳሙኤል ለውጡ ውጤት ያመጣል ብለው ተስፋ ያደረጉ ደጋፊዎች የዓመቱን ጨዋታ መጀመር እየጠበቁ ይገኛሉ።

መቶ አለቃ ፈቃደ በበኩላቸው በአዲሱ የውድድር ዓመት ለደጋፊና ኳስ ተመልካች እግር ኳስን እንደ አንድ መዝናኛ ዘርፍ እንዲያየው አደራ ብለዋል። ‹‹ኳስ ከሌሎች መዝናኛዎች በተለየ ለመጮኽ፣ ለመዝፈን፣ ለመጨፈር ያስችላል። መሳደብ፣ ዘረኝነት እና ነውጠኝነት ግን አይደረግን፤ ለማንምም አይጠቅምም። እግር ኳስ ሜዳን የወንድማማቾች፣ ሕዝብ የሚፋቀርበት ቦታ አድርገን እንየው።›› ሲሉ ለእግር ኳስ አፍቃርያን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here