ልማታዊ መንግሥት ከየት ወዴት

0
1374

ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን ባለፉት 15 ዓመታት ተግባራዊ አድርጋ ስትከተል ነበር። ፖሊሲው በተለያዩ የዓለም አገራት በአንድ በኩል ለኪሳራ ሲዳርግ፤ አንዳንድ አገራት ደግሞ ኢኮኖሚያቸውን በእጅጉ እንዲያሳድጉ እድል ፈጥሮላቸዋል። በዚህ ልዩነት ምክንያት ልማታዊ መንግሥት-መር የሆነ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ከማምጣት፣ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም ሥራ ፈጠራን ከማበረታታት አኳያ ያለው ሚና ሲያከራክር ቆይቷል።

በኢትዮጵያም የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን በተመለከተ ታድያ ባለሙያዎች መርኹና ትግበራው ለየቅል ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ። መንግሥት የልማታዊ መንግሥትን ምንነት በሚገባ አልተረዳም የሚሉም አሉ። ይህንን እና ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያን እንዴት ይቀጥላል፣ ኢትዮጵያንስ ወዴት ያደርሳታል፣ አሁንስ ያለበት ሁኔታ ምንድን ነው የሚሉ ተያያዥ ነጥቦችን በተመለከተ፣ የአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሃኔ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን በመጠየቅ፣ የሚመለከታቸውን በማናገርና መጻሕፍት በማጣቀስ ጉዳዮን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ልክ የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ በዓለም አገራት ዘንድ በደካማ ምጣኔ ሃብቷ፣ በጦርነት፣ ረሃብ እና ድህነት ከሚታወቁ አገራተ ተርታ ትመደብ ነበር። ይባስ ብሎ፤ የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት ከማደግ ይልቅ ወደ ባሰ ውድቀት እያዘመመ ነበረ። ለዚህ ማሳያ፤ በ1995 የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት በኔጋቲቭ 3 ነጥብ 3 ወደ ታች እድገት ማሳየቱ ነበር። በወቅቱም፤ ከግማሽ በላይ የነበረው ሕዝብ በድህነት ውስጥ ይማቅቅ የነበረ ሲሆን የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ40 ዶላር በታች ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያን በድህነት ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚ አድርጓታል ቆይቷል።

ነገር ግን ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የታየው ሰፊ እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት አገሪቷ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያላት ገፅታ እንዲቀየር ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አነሳሽነት ኢትዮጵያ መከተል የጀመረችው ‹‹የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ›› ሲሆን አገሪቷ ባለፉት አስርት ዓመታት ባለ ኹለት አሃዝ የምጣኔ ሃብት እድገት እንድታስመዘግብ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ከዚህም ባሻገር፤ በድህነትና ረሃብ የምትታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ፈርጥ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከዓለም ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ አገራት ተርታ ልትሰለፍ ችላለች። ምን ይሄ ብቻ፣ አገሪቷ የምትከተለው ‹‹የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ›› የአፍሪካ አንበሳ የሚል ስያሜ እንድታገኝ አስችሏታል።

ፖሊሲው ትላልቅ የሚባሉ ስኬቶችን ቢያመጣም ከትችት አላመለጠም። በአንድ ጎን ከመነሻው መንግሥት የልማታዊ መንግሥት መርህ እከተላለሁ ቢልም፣ ባለሙያዎች ትግበራውና የመርኹ ምንነት ለየቅል ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ። በተጓዳኝ ጥቂት የማይባሉ በልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መርኹን ለመተግበር ሲያስቡ ፅንሰ ሃሳቡን የተረዱበት መንገድ እና አተረጓጎማቸው ላይ ችግር አለበት ሲሉ ያነሳሉ።
በእርግጥ መለስ የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲያቸውን ለፓርቲያቸውም ሆነ ለሕዝብ ይፋ ሲያደርጉ ሊበራል (ነፃ) የመንግሥት አመራር ዘይቤ ሞቷል፤ እንደውም ተቀብሯል ሲሉ ተደምጠው ነበር። ታዲያ ለእርሳቸው ለኢትዮጵያ ህልውና ፈተና የሆነው ድህነትን ማጥፋት የሚቻለው አገሪቷ መንግሥት-መር የሆነ ምጣኔ ሃብት ወይንም ልማታዊ መንግሥት ስትከተል ነው ብለው ነበር። ይሁንና ተግባር ላይ የዋለው ከፖሊሲው መርህ አንጻር ተቃራኒ ሆኖ የተመለከቱ ባለሙያዎች ደግሞ የሰላ ትችት ሲዘነዝሩ ይታያል።

የልማታዊ መንግሥት ፅንሰት
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመለካት አገራዊ አጠቃላይ ምርትን እንደ መለኪያ የሚጠቀሙ ሲሆን ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ባለፉት አራት ምዕተ ዓመታት ውስጥ ብዙ ንድፈ ሃሳቦች ተዘጋጅተዋል። ከእነዚህም በቀዳሚነት የሚነሳው የምጣኔ ሃብት አባት ተብሎ የሚጠራው አዳም ስሚዝ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ይዞት ብቅ ያለው ፅንሰ ሃሳብ ነው። አዳም ስሚዝ በ1776 በታተመው ‹‹ዌልዝ ኦፍ ኔሽን›› በሚለው ዝነኛ መጽሐፉ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ መሰረት በማድረግ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ሊመጣ የሚችልበትን መንገድ ያብራራ የመጀመሪያው ባለሙያ ነበር።

በአዳም ፅንሰ ሃሳብ መሰረት፣ አቅርቦት እና ፍላጎት የገበያን ባህርይ በመተንበይ ረገድ ትልቅ ሚና ያላቸው ሲሆን የአንድ አገር ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያም ያላቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ይህ የአንድ አገር ጥቅል ምርት በአቅርቦት እና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው እንደ ማለት ነው። የ‹ክላሲካል ኢኮኖሚ› ባለሙያዎች ዘርፍ የሚመደበው አዳም በመጽሐፉ እንደሚገልፀው፣ የአንድ አገር ገበያ ራሱን ማስተዳደር የሚችል እና ነፃ መሆን ያለበት ሲሆን በአንድ ምጣኔ ሃብት ውስጥ የሚፈጠረው አጠቃላይ ፍላጎት በቂ የሆነ አቅርቦትን መፍጠር ይችላል። ይህም ክስተት “የማይታየው እጅ” (ዘ ኢንቪዝብል ሃንድ) በመባል ይታወቃል። ይህ ፅንሰ ሃሳብ በብዙ የምጣኔ ሃብት ምሁራንና ተመራማሪዎች ከዳበረ በኋላ እነ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊ አገራት ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ቆይቷል።

ነገር ግን፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1929 እስከ 1939 ድረስ፣ መጀመሪያ በአሜሪካ ቀጥሎም በመላው ዓለም የተከሰተውን የምጣኔ ሃብት ቀውስ ተከትሎ የሊብራሊዝም ተቀባይነቱ በከፍተኛ ደረጃ ወርዶ ነበር። ከዚያም ነበር ታዋቂው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ጆን ማይናርድ ኬነስ አዲስ የኢኮኖሚ ፅንሰ ሃሳብ ይዞ የመጣው። ከአዳም ስሚዝ ዕሳቤ በተቃራኒ ፍላጎት እና አቅርቦት ሁልጊዜ ወደ ተፈጥሮአዊ ሚዛን እንደማይሸጋገሩ ያረጋገጠው ኬነስ፣ የፍላጎትን መፈጠር ተከትሎ ችግሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ፣ ተጨማሪ ማነቃቂያ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ ባይ ነው። አጠቃላይ ፍላጎት ከተፈጠረ በኋላ በቂ የሆነ አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል አስፋፊ የፋይናንስ ፖሊሲን መጠቀም የግድ ይላል ሲል ይሞግታል።

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በኢኮኖሚ ወስጥ ያለውን የመንግሥት ኢንቨስትመንት መጨመር ግድ ይላል የሚለው ኬነስ፣ በዚህ ዓይነቱ አካሔድ ምርታማነትንም ሆነ አጠቃላይ ጥቅል ምርትን መጨመር እንደሚቻል ይመክራል።

የልማታዊ መንግሥት ፅንሰ ሃሳብም ከዚህ የመነጨ ነው።
የኬነስ ንድፈ ሀሳብ ቅጥያ ተድርጎ የሚወሰደው የልማታዊ መንግሥት ፅንሰ ሃሳብ መሰረት፣ የአንድ ምጣኔ ሃብት አጠቃላይ ፍላጎትም ሆነ አቅርቦት ለመጨመር ከፍተኛ የመንግሥት ኢንቨስትመንት አስፈላጊ ሲሆን ይህንን ለማድረግ አስፋፊ የፋይናንስ ፖሊሲን (በጀትና ታክስን ማሳደግ) መከተል ግድ ይላል። ነገር ግን ይህ ዓይነቱ እሳቤም ቢሆን ከትችት አልዳነም። መንግሥት በምጣኔ ሃብት ላይ ያለው ሚና ይብዛ ወይስ ይነስ የሚለው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዓለም ዐቀፍ ባለሙያዎችንና የፖሊሲ አውጪዎችን እንዲሁም መንግሥታትን ሲያከራክር የቆየ ጉዳይ ነው።

በተለይም ከ1950ዎቹ አንስቶ በአፍሪካና እስያ የሚገኙ አገራት ሉአላዊነታቸውን ማወጃቸውን ተከትሎ የተቀበሉት ልማታዊ መንግሥት-መር የሆነ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ከማምጣት፣ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም ሥራ ፈጠራን ከማበረታታት አኳያ ያለው ሚና ሲያከራክር ቆይቷል። በዚህም የተነሳ የልማታዊ መንግሥት-መር የምጣኔ ሃብት ዘይቤ ተቀባይነቱ ከኹለት አስርት ዓመታት በላይ ሊልቅ አልቻለም።

በተለይም ይህን አይነቱን አሰራር ተከትለው ኢኮኖሚያቸውን ሲያስተዳድሩ የነበሩ አገራት ውስጥ የመንግሥት ሚና በምጣኔ ሃብት ውስጥ ከፍተኛ መሆንና ጣልቃ ገብነቱ ያለቅጥ መስፋቱ፣ ደካማ እና እጅጉን ቀልጣፋ ያልሆኑ የመንግሥት ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ እና ሙስና እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል።

ይባስ ብሎ፤ በአንዳንድ የላቲን እና የአፍሪካ አገራት ምጣኔ ሃብቱ በጥቂት ግለሰቦችና ድርጅቶች ስር እንዲወድቅና ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲባባስ እንዳደረገ ተጨባጭ ማስረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚያም የልማታዊ መንግሥት መርህ መውደቁን የተመለከቱት ፖሊሲ አውጪዎችና የፖለቲካ ምሁራን፣ ገበያ-መር የሆነ ኢኮኖሚ እንዲመለስ መወትወታቸውን ተከትሎ ተቀባይነቱ ሊወርድ ችሏል። ከ1980ዎቹ አንስቶ ታዲያ ለዚህ ምላሽ አይ ኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክ የዓለም ዐቀፉን ማህበረሰብ በማሰባሰብ የዋሽንግተን ስምምነትን ይዘው ብቅ ማለት ችለው ነበር።

የበጀት ጉድለትን መቆጣጠር፣ ድህነት ተኮር ፕሮግራሞች ላይ ማተኮር፣ የታክስ መሰረትን ማስፋት፣ ውድድርን መሰረት ያደረገ የውጭ ምንዛሬ የገበያ ስርዓት መከተል እና በመንግሥት የተያዙ ቁልፍ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ግል ይዞታ ማዘዋወር በስምምነቱ ላይ የተጠቀሱ ለምጣኔ ሃብት ዕድገት መወሰድ ያለባቸው ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው። ይህ በብዙ ምዕራብ አገራት ተቀባይነት አግኝቶ ቢቆይም በአንዳንድ አገራት በተለይም በ1990ዎቹ በእስያ ያለው ተቀባይነት መውረዱ ለልማታዊ መንግሥት ፅንሰ ሃሳብ በድጋሚ ማንሰራራት ምክንያት ሆኖ ነበር። በአንጻሩ ቀጣይ በነበሩት አስር ዓመታት ውስጥ የሊበራል ፖሊሲ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያዘግም፣ የገቢ አለመመጣጠን እንዲስፋፋ እና የፋይናንስ ዘርፍ እንዳይረጋጋ ምክንያት መሆኑ በአገራት ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎታል።

በተለይም በምስራቅ እስያ እንደ ሆንግ ኮንግ፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን ወይም ‹የእስያ ነብሮች› የሚባሉት አገራት የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን በመጠቀም ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገትና ስር-ነቀል ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ከ30 ዓመታት በላይ ለማስመዝገብ መቻላቸው ሊብራሊዝም የበለጠ ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎታል። እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ከዝቅተኛና የከፋ የግብርና ማህበረሰብ መካከል ይመደቡ የነበሩት እነዚህ አገራት ልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን በመተግበር የከፍተኛ የቴክኖሎጂ እና ውድ ሸቀጦች አምራች አገራት መካከል መሆን ችለዋል። ይህ በተለይም እ.ኤ.አ. በ2007/8 ከተከሰተው ዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተዳምሮ የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ የምጣኔ ሃብት እድገት ከማምጣትና የገበያ ውድቀት ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የታዳጊ ሀገራት የልማት ሒደት እንዲፋጠን ያለው ሚና ሊያድግ ችሏል።

የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ የሚያስገኘውን ጥቅም ከተገነዘቡ አገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ነች።
በተለይም አገሪቷን ለኹለት አስርት ዓመታት እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ የመሩት መለስ ዜናዊ፣ ሊበራሊዝም ሞቷል ወይም ላይመለስ ተቀብሯል ብለው ከሚያስቡት የአገራት መሪዎች መካከል ይመደባሉ። ጥናታቸውን በዚሁ ርዕስ ላይ የሠሩት መለስ፣ ኒዮ-ሊበራሊዝም ትርጉም ያለው ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እና ሽግግርም ሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ሊያመጣ አይችልም የሚል እሳቤ የነበራቸው ሲሆን ድህነትን ማጥፋት ለኢትዮጵያ ህልውና አማራጭ የሌለው መሠረታዊ ነገር ነው በማለት ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት-መር ኢኮኖሚ መከተል ግድ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠው ነበር። እንደ መለስ አስተሳሰብ፣ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ለማድረግና የምርት እጥረት ችግሮቿን ለመፍታት ጠንካራ፣ መንግሥት የሚመራውና የመንግሥት የበላይነት ያለበት ምጣኔ ሃብት መተግበር አለበት።

በተጨማሪ፤ በቅርቡ በሪፖርት መልክ ተሰናድቶ ይፋ በሆነውና መለስ ከ1988 እስከ 2012 ባለው ጊዜ መካከል ከአሌክስ ዲ ዋል ጋር ያደረጉት ተከታታይ ውይይቶች ላይ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ንቁ የሆነ መንግሥት ሊኖር ይገባል ብለዋል። በተጨማሪም መንግሥት በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ከማድረግም በላይ የአገሪቷን ሃብት ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ ሊመድብ ይገባል ሲሉ ተከራክረውም ነበር።
በሌላ በኩል መለስ የልማታዊ መንግሥትን ለመተግበር ሦስት አቅጣጫዎችን ገልፀው ነበር።

በመጀመሪያ፤ መንግሥት የግሉን ዘርፍ እና አንዳንድ ቁልፍ ዘርፎችን መምራት የሚችል መሆንና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር እንዲሁም ምጣኔ ሀብቱን መቆጣጠር መቻል አለበት። በኹለተኛ ደረጃ፤ ለልማት ትኩረት መስጠት እና የተፋጠነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣት ዋነኛ መርኹ ሊሆን ይገባል። በሦስተኛ ደረጃ፤ የሕብረተሰቡ ወጎች እና እሴቶች በእድገት ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው።

ታዲያ አገሪቷ ይህን ዓይነቱን ፖሊሲ በመከተል ባለ ኹለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ለአስር ዓመታት ብታስመዘግብም ባለሙያዎች፣ ኢህአዴግ ልማታዊ መንግሥትን የተረዳበት መንገድ ትክክል አይደለም ሲሉ ኮንነዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝደንት ታደለ ፈረደ መንግሥት የልማታዊ መንግሥትን ሞዴል ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አልተረዳውም፤ ይህም ከጅምሩ የመጣ ነው ከሚሉት መካከል ናቸው።

‹‹የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ መንግሥት በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ውስጥ ቁልፍ ሚና ሊኖረው ይገባል ማለት አይደለም። ይልቁንም በልማታዊ መንግሥት መርህ በሚመራ ሃገር ውስጥ መንግሥት በሁሉም ዘርፍ ውስጥ ቁልፍ ሚና ከመጫወት ይልቅ ዋና ሥራው የግሉን ዘርፍ ለማጎልበት ሕጎችን እና ደንቦችን ማውጣትና የግሉን ዘርፍ ማበረታት ነው›› ይላሉ፤ ታደለ። በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት የምጣኔ ሃብት ባለሙያውና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ዲን የሆኑት አጥላው ዓለሙ፣ የልማታዊ መንግሥት መር ኢኮኖሚ መንግሥትን የምጣኔ ሀብቱ ፈላጭ ቆራጭ ማድረግ አይደለም ይላሉ።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ልማታዊ መንግሥት ለኢትዮጵያ ትክክለኛ ፖሊሲ ነው ብለው ከሚያምኑት መካከል ይመደባሉ። ነገር ግን ባለፉት 15 ዓመታት በትክክል አለመተግበሩ አግድም የገቢ አለመመጣጠን እንዲባባስ እና ሙስና እንዲስፋፋ እንዳደረገ ያነሳሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት በመንግሥትና በግል ዘርፉ ያለው ውይይት ያነሰ መሆን፣ የግሉ ዘርፍ እንዲያድግ አለመደረጉ፣ የተጠያቂነት አለመኖር እና በፓርቲ የተመሰረቱ ድርጅቶች በምጣኔ ሃብት ላይ ያላቸው ድርሻ መብዛቱን ነው።

በሌላ በኩል፤ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ታደለ፣ መንግሥት ፍላጎትን መጨመር ላይ የሰጠውን ያህል ትኩረት አቅርቦት ላይ አለመስጠቱን እንደ ችግር ያነሳሉ። በእርግጥ፤ በባለፉት አስር ዓመታት ወደ ኢኮኖሚ እንዲገባ የተደረገው የገንዘብ መጠን በ987 በመቶ አድጎ 741 ቢሊዮን ብር መድረሱ ከፍተኛ ፍላጎት በኢኮኖሚ እንዲፈጠር ያደረገ ቢሆንም የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።

በመለስ እና እርሳቸውን በተኩት ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን፣ ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን ስትተገብር፤ የእስያ ነብሮች ተብለው የሚጠሩ አገራትን በተለይም ደቡብ ኮሪያን መነሻ አድርጋ መውሰዷ በተደጋጋሚ ቢነገርም በመሬት ላይ የታየው ነገር ግን የተለየ ነበር።

ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ተገኘተው ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት የፖለቲካል ሳይንስ እና የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ፍራንሲስ ፉኩያማ፣ ከልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ አተገባበር አንፃር በኢትዮጵያ እና በደቡብ ኮሪያ ያለውን ልዩነት ከተመለከቱት መካከል ናቸው።

የእስያ አገራት የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን ሲተገበሩ ሁሉም በከፍተኛ ኃይል እና ሥራ ፈጠራን መሰረት በማድረግ በግሉ ዘርፍ የጀመሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ሲተገበር በጣም ደካማ ከሆነው የግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን በመንግሥት የሚመራ ነው ይላሉ፤ ፉኩያማ።

በእስያ ልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ ሲጀመር መንግሥታት ለግል ኩባንያዎች ተግሳጽ ከመስጠት ባለፈ ሚና አልነበራቸውም የሚሉት ፉክያማ፤ በእነዚህ አገራት በመንግሥት እና በግል ዘርፍ መካከል የነበረውም ግንኙነት እርስ በእርስ የመማማር እና የመረዳዳት እንጂ እንደ ኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም ነገር የተቆጣጠረበት ስርዓት አልነበረም ይላሉ። ቻይናን ለአብነት ያነሳሉ።

‹‹በመጀመሪያ በመንግሥት የተያዙ ድርጅቶች ማበረታቻዎች እየተሰጣቸው ውጤታማ ሆነው የቻይናን ምጣኔ ሃብት የሚያንቀሳቅሱት የግሉ ዘርፍ ተዋንያኖች ናቸው። በሌሎች ልማታዊ መንግሥት በሚከተሉ እንደ ኮሪያ ያሉ እስያ አገሮችም ከዚህ የተለየ አላደረጉም›› የሚሉት ፉኩያማ በኢትዮጵያ ግን የተተገበረው ከዚህ የተለየ ነበር ባይ ናቸው። ‹‹ኢትዮጵያ የተገበረችው ከልማታዊ መንግሥት ይልቅ መንግሥት-መር የሆነ ፖሊሲ ነው።›› እንደ ፉኩያማ ገለጻ።

በኢትዮጵያ እና በእስያ አገራት መካከል ያለው ሌላው ትልቁ ልዩነት የእስያ አገራት ልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን ሲተገበሩ ጠንካራ፣ ትጉህ እና የሠለጠነ የሰው ኃይል የነበራቸው መሆኑ ነው። ‹‹የእስያ አገራት ይህ ዓይነቱን ፖሊሲ በተግባር ሲያውሉ በቴክኖሎጂ ብቁ የሆኑና አቅም ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የነበራቸው ሲሆን በኢትዮጵያ የነበረው ሁኔታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነበር›› ይላሉ ፉክያማ።

ሌላው በኢትዮጵያ እና በእስያ አገራት መካከል ያለው ልዩነት ደግሞ ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዘ ነው። ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና እና በተወሰነ ደረጃ ታይዋን ልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን ከመተግበራቸው በፊት በጥሩ ሁኔታ የተቋቋሙ ግዛቶች እና በደንብ የተቋቋሙ ብሔራዊ መለያዎች ነበሯቸው ያሉት ፉክያማ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት ላይ ችግር መኖሩ አገሪቷ ፖሊሲውን በአግባቡ ተግባር ላይ እንዳታውለው ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ።

‹‹ልማታዊው የኢህአዴግ መንግሥት›› ምን ለውጥ አመጣ?
ገዥው ፓርቲ ልማታዊ መንግሥት ፖሊሲን ከተቀበለበት ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት አንስቶ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንካራና ሰፊ ዕድገት አስመዝገቧል። የአገልግሎት ዘርፍ እና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ መስፋፋት ለታየው ሰፊ እድገት ዋነኛ ምክንያት ሲሆኑ የአምራቹ ዘርፍ በምጣኔ ሃብቱ ላይ ያለው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም ቀላል የማይባል ዕደገት አሳይቷል። ከአስርት ዓመታት በፊት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር እንኳን ያልነበረው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር መድረስ የቻለ ሲሆን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሆኑ አምስት የአፍሪካ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ምክንያት ሆኗል።

የተገኘው የኢኮኖሚ ስኬት በዚህ አያበቃም።
ባለፉት 15 ዓመታት በተመዘገበው ባለ ኹለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት የነፍስ-ወከፍ ገቢ ከስድስት ዕጥፍ በላይ የሆነ ዕድገት እንዲያሳይ ምክንያት ሲሆን በድህነት አረንቋ የሚኖሩ ዜጎች በ15 ሚሊዩን ቀንሰው 23 ሚሊዮን እንደደረሱ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ ያሳያል። የኢኮኖሚ ዕድገቱ በሰው ኃይል ልማት (ትምህርትና ጤና)፤ የመጠጥ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታና ተደራሽነት መስፋፋት የታገዘ ሲሆን ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ከአምስት ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ሕጻናት ሞት ከግማሽ በላይ ለመቀነስ ተችሏል።

በተመሳሳይ የዜጎች በሕይወት የመኖር አማካይ ዕድሜ በ10 ዓመታት የጨመረ ሲሆን የመጀመሪያና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ጥቅል ተሳትፎ ምጣኔ በቅደም ተከተል 100 እና 80 በመቶ ደርሷል። የኤሌክትሪክ ኃይል፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲሁም የመንገድ ተደራሽነት በተመለከተ አሁንም ሰፊ ክፍተት ያለበት ቢሆንም በእነዚህ ዓመታት ከእጥፍ በላይ ማደጉ ተጠቃሽ ናቸው።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እድገት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።
አንደኛው ልዩ የሚያደርገው ነገር እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት በነዳጅ ወይም በሌሎች ማዕድናት እና የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ጥገኛ አለመሆኑ ሲሆን ይህ የሚያመለክተው በመሰረተ-ልማት አውታሮች ላይ በተደረገ ግዙፍ ኢንቨስትመንት የመጣ ዕድገት መሆኑ ነው።

እንደ አብዛኛዎቹ ልማታዊ መንግሥታት ሁሉ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ የእድገት አንቀሳቃሽ ሲሆን መሠረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና በሌሎች ቁልፍ ዘርፎች ትልቅ ግፊት በመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ሚና ነበረው። የፋይናንስ ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት ኢዮብ ተካልኝ ከኹለት ሳምንት በፊት በሚኒስቴሩ አዳራሽ በተዘጋጀ መድረክ ይህንን አንስተው የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት ለተገኘው የኢኮኖሚ እድገት ስኬት የመንግሥት የተለጠጠ የኢንቨስትመንት መርሀ-ግብር አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር ሲሉ ተደምጠዋል።

ለዚህም የተለያዩ ማሳያዎችን ጠቅሰው ነበር።
ከግማሽ በላይ የሚሆነው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የመነጨው ከኢንቨስትመንት መሆኑ፣ ኢንቨስትመንት ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻው ከ15 ዓመታት በፊት ከነበረው 25 በመቶ በ2009 ወደ 38 በመቶ ድርሻ ከፍ ማለቱን አንስተዋል። የብሔራዊ አካውንት መረጃዎች የመንግሥትንና የግሉን ዘርፍ መዋዕለ ንዋይ ድርሻ ለይቶ ባያመላክትም የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛው ኢንቨስትመንት መጠን ከመንግሥት እየመነጨ እንደነበር ሲሆን ባለፉት 10 ዓመታት ከኹለት ሦስተኛ በላይ የሚሆነው የመንግሥት በጀት ለልማት የኢንቨስትመንት (ካፒታል በጀት) የዋለ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

በተጨማሪ ወደ 90 ቢሊዮን ዶላር የደረሰውን የአገሪቷን አጠቃላይ ምርት 20 በመቶ የሚሆን ገንዘብ እንደ መንገዶች፣ ዩንቨርስቲዎች፣ ጤና ተቋማት፣ ባቡር ሀዲዶች፣ አየር መንገዶች፣ ውሃ ማመላለሻ፣ የመስኖ ግድቦች እና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት መንግሥት ማውጣቱ በኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ የበለጠ አግዝፎታል። ይህም የመንግሥት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት፣ የኮንስትራክሽንና የአገልግሎት ዘርፉን እንዲነቃቃ ከማድረጉም በላይ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የነበረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር።

የመንግሥት ኢንቨስትመንት በአገር ውስጥ ቁጠባና በብድር የተሸፈነ ሲሆን የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች የጡረታ መብት መዋጮ በጀት ጉድለት መሙያ በመሆን ፈሰስ መሆኑ እንዲሁም የከተማ ቤቶች ቁጠባ በመጨመሩ የአገር ውስጥ ቁጠባ ለጥቅል አገራዊ ምርት ያለው ድርሻ በ15 በመቶ በማደግ 24 በመቶ መድረሱን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል።

ይህም፤ ጥብቅ ከነበረው የአገሪቷ የፖለቲካ ከባቢ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ መንግሥት-መር የነበረው የኢህአዴግ ፖሊሲ በምጣኔ ሃብት ወጤት አምጥቶ እንደነበር ማሳያ ነው። ነገር ግን ይህ መንግሥት-መር የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ያመጣቸው ይበል የሚያሰኙ እምርታዎች ቢኖሩም ይዞት የመጣው ችግርም ቀላል የሚባል አይደለም። በመንግሥት መር ምጣኔ ሃብት የተገኘው ልማት የገቢ አለመመጣጠንን፣ ኪራይ ሰብሳቢነት እና ሙስና ሲያስፋፋ ጥቂት ሃብታሞችንና ብዙ ድሃዎችን ፈጥሯል።
እንዲሁም በክልሎችና በከተሞች መካከል ያለውን የሃብት ስርጭት ኢ-ፍትሃዊ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። ይህንን ከተገነዘቡት የኢህአዴግ አመራር መካከል የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ርዕስቱ ይርዳው አንዱ ናቸው። ‹‹ከከተማ ርቀው የሚገኙ ስፍራዎች በአገሪቷ ከነበረው ዕድገት ተጠቃሚ አልነበሩም›› ያሉት ርዕስቱ፣ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ትኩረት የሚሰጡት ለንግድ መተላለፊያ ለሆኑና ቀድሞውኑ ላደጉ ከተሞች ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ፍትሃዊ የሃብት ስርጭት በክልሎች መካከል አለመኖሩን ያወሱት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ የምጣኔ ሃብቱ ፈላጭ ቆራጭ የነበረው ፌዴራል መንግሥቱ ፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ ደካማ መሆኑን እንደ ችግር አንስተዋል።

ከኢ-ፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል በተጨማሪ መንግሥት-መር የነበረው ምጣኔ ሃብት ከነበረው ደካማ የቁጥጥር ስርዓት ጋር ተዳምሮ አገሪቷን ለብክነትና ለሙስና እንዳጋለጣት መረጃዎች ያሳያሉ። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ አካባቢ ይፋ የሆነው የኦዲተር ጄኔራል ሪፖርት ነው። መሥሪያ ቤቱ 290 የሚሆኑ እንደ ስኳር ፋብሪካ፣ መስኖ ግድብ፣ መንገድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ባደረገው የኦዲት ሥራ ከ44 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ያልተገባ ወጪ መውጣቱን አረጋግጧል። ይህም ከአዲስ አበባ ዓመታዊ በጀት ጋር የሚስተካከል ሲሆን የመንግሥት-መር ምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ጋር የመጣ ችግር ተድርጎ ይነሳል።

ሜቴክን እንደ ማሳያ
ኢህአዴግ-መር የሆነው መንግሥት በአገሪቷ ምጣኔ ሃብት ላይ መዋቅራዊ ሽግግርን ማምጣትን ግብ አድርጎ መሥራት ከጀመረ ኹለት አስርት ዓመታት አልፎታል። በተለይም የማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም ኢንዱስትሪ ዘርፎችን ለማሳደግ መንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችን አውጥቶ ቢሠራና የታየው እመርታም ቀላል ነው ባይባልም፤ አገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ያለው አስተዋፅኦ ብዙም ሊያድግ አልቻለም።

በግልፅ ሲቀመጥ፤ ከ15 ዓመታት በፊት አጠቃላይ የአምራች ዘርፉ ምርት አራት ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን በባለፈው በጀት ዓመት ወደ 125 ቢሊዮን ብር አካባቢ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ እንደሚያሳየው የአምራች ዘርፉ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ የ31 እጥፍ ዕድገት ያሳየ አሳይቷል። በአንጻሩ ለአገሪቷ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ ግን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከሰባት በመቶ ሊያልፍ አልቻለም። ታዲያ ልክ የዛሬ ዓመት በፊት ነበር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይህንን የተገነዘቡት። ለችግሩም ዋነኛ ምክንያት የሰለጠነ እና ትጉህ ሠራተኛ አለመኖሩ መሆኑን በወቅቱ የተረዱት መለስ፣ ይህንን ለመፍታት ነበር ሜቴክ ወይም የብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን እንዲመሰረት ያዘዙት። ከዚያም በኋላ ነው በመከላከያ ስር የነበሩ ዘጠኝ ድርጅቶችን በማዋሃድ ሜቴክ የተመሠረተው።

የሰለጠነ እና አምራች የሰው ኃይል መፍጠር አና ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ብቃት ለመጨመር የተመሰረተው ኮርፖሬሽኑ፣ ከምስረታው አንስቶ በመቶ ቢሊዮን ብሮች የሚያወጡ የግንባታ ፕሮጀክቶችና ግዢዎችን ያለምንም ጨረታ ቢሰጠውም በትክክል ያሳካው ነገር እጅጉን ያነሰ ነበር። ይህም ድርጅቱ ያለቅጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ፕሮጀክቶች ከመያዙ ጋር ተዳምሮ ኪሳራ ላይ እንዲወድቅ ያደረገው ሲሆን ያለበት ዕዳ በአሁኑ ወቅት ወደ 70 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ከዚህ ባሻገር፤ 11 ቢሊዮን ብር ያልተከፈለ የታክስ ውዝፍ ዕዳ ያለበት ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ስለገጠመው ይህንን በ30 ዓመታት ውስጥ ለመክፈል ጥያቄ አቅርቧል።

ታዲያ የሜቴክ ወድቀት የተመለከቱ ባለሙያዎች ችግሩ ኢህአዴግ ከሚከተለው የመንግሥት-መር ምጣኔ ሃብት ፖሊሲ የመጣ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። በተለይም ለሜቴክ ያለ ጨረታ ፕሮጀክቶችን ከመስጠት ይልቅ የግሉ ዘርፍ ተዋንያኖች ተወዳድረው እንዲወስዱ ቢደረግ መልካም ነበር የሚሉም አልጠፉም።

‹አለ በጅምላ› ሌላኛው መንግሥት የምጣኔው ሃብት ፈላጭ ቆራጭ እኔ ነኝ ከማለቱ ጋር ተያይዞ በመጣ ችግር አደጋ የወደቀ ድርጅት ነው። የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ከዛሬ ስድስት ዓመታት በፊት የተመሠረተው አለ በጅምላ ወደ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ሥራ ቢጀምርም የዋጋ ተመንን ለመቆጣጠር እና ግብይትን ለማዘመን እንዲሁም የሸቀጥ ገበያውን ኹለት ሦስተኛ ባለድርሻ ለመሆን አቅዶ የነበር ቢሆንም ያሰበው ሳይሳካ ቀርቷል።

የድርጅቱን ምስረታ ከጅምሩ ሲቃወሙ ከነበሩት የፋይናንስ ባለሙያዎች መካከል አብዱልመናን መሐመድ አንዱ ናቸው። እንደ አብዱልመናን ገለፃ፣ መንግሥት የችግሩን መሰረት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በመጠቀም መፍታት ሲገባው በቀጥታ መግባቱ ችግሩን እንዲባባስ አደረገው እንጂ ለውጥ አላመጣም።
ሌላኛው የመንግሥት-መር ምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ይዞት የመጣው ችግር አገሪቷን ከፍተኛ ብድር ጫና ውስጥ እንድትወድቅ ማድረጉ ነው። የተለያዩ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማካሔድ መንግሥት እስከ አሁን የወሰደው ብድር 51 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህም የአገሪቷን አጠቃላይ ምርት 57 በመቶ አካባቢ ይሆናል። ከብድሩ ውስጥ ወደ 27 ቢሊዮን ዶላር ገደማው ከውጭ አበዳሪዎች የተወሰደ ሲሆን ቀሪው ከአገር ውስጥ አበዳሪዎች የተገኘ ነው።

በተለይም ከውጭ አበዳሪዎች ከተወሰደው ውስጥ ከፊሉ ከቻይና መሆኑ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም እንዳያሳጣ እና አንዳንድ ንብረቶች እንዳይወረሱ ስጋቶች አሉ። ይህ ዓይነቱ አጣብቂኝ ውስጥ አገሪቷ መግባቷ ለድህነት ቅነሳ እና ለሌሎች ልማቶች ልታውላቸው የሚችሉ ገንዘቦችን ብድር ለመክፈል ለማውጣት ልትገደድ እንደምትችል መሰረቱን ለንዶን ባደረገው አይኤችኤስ ማርኪት በተሰኘው የጥናት ተቋም ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት አሊሳ ስትሮቤል ያነሳሉ። ብድሮቹ እንዲራዘም መንግሥት ጥረት ቢያደርግም እንኳን፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት አንድታጣ ሊያደርጋት ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን አጋርተዋል።

ዘመነ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው ፖሊሲ ምን ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። እርሳቸውም በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብላቸወም አድምተው ምላሽ ሲሰጡበት አይስተዋልም።

ይሁን እንጂ የፋይናንስ ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት ኢዮብ ተካልኝ ከሦስት ወር በፊት ገደማ በአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ‹‹ልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም›› ሲሉ አክለውም፤ ‹‹በተፈለገ ሰዓትና ወቅት የአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ እየታየ ይቀየራል›› ብለው ነበር።

በተጨማሪ ከሦስት ሳምንት በፊት በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ስለታሰበው አገር በቀል ሪፎርም በተመለከተ ውይይት በተካሔደበት ወቅት አገሪቷ ምን እንደምትከተል አይታወቅም ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ‹‹ጥቁር ወይም ነጭ ብለን የምንናገረው ነገር የለም›› ብለው ተናግረው ነበር። አያይዘውም ‹‹ከዚህ በኋላ ፅንሰ ሃሳብ (ቲዮሪ) ላይ ትኩረት አናደርግም›› ብለዋል። በሌላ በኩል፤ ኢህአዴግ እንደ አዲስ ሊመሠርተው ስላሰበው ውህድ ፓርቲ ገለፃ በሚሰጥበት ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ልማታዊ መንግሥት ፓሊሲን እንደሚከተል ተድርጎ እንደሚገለፅ ስብሰባውን የተሳተፉ ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የምጣኔ ሃብት ምሁር የሆኑት ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ ልማታዊ መንግሥት እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሲሆን ጠንካራ የግል ዘርፍ በሌለበት አገር መንግሥት መሪ የሆነበት ነገር ግን የግሉ ዘርፍን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆን አለበት ሲሉ ይከራከራሉ። የፋይናንስ ባለሙያው አብዱልመናንም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ልማታዊ መንግሥት የምትከተል ከሆነ በቅድሚያ ማሟላት ያለባት ነገሮች አሉ ይላሉ።

‹‹የመጀመሪያው ጠንካራ እና ከፓርቲ ነፃ የሆኑ የኢንዱሰትሪ ፓሊሲዎችን ማስፈፀም የሚችሉ ተቋማት መገንባት ሲሆን ኹለተኛው ብቃትን መሰረት አድርጎ የተዋቀረ የሰው ኃይል መገንባት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ተጠያቂነት የተረጋገጠበት ፓለቲካዊ ሁኔታ ሊኖር ይገባል።›› ብለው የሚያምኑ ሲሆን ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠው ድጋፍ እና ማበረታቻም ባላቸው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ለአገሪቷ በሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ መሆን አለበት፤ እንደ አብዱልመናን ገለጻ።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ታደለ በበኩላቸው መንግሥት አቅርቦትን መጨመር ላይ መሥራት እንዳለበት ያነሳሉ። በተጨማሪም መንግሥት የሚያደርገውን ሹመት በፓለቲካ እና ተሿሚው ለፓርቲው ባላቸው ታማኝነት ከማድረግ ይልቅ ብቃትን መሰረት አድርጎ ቢሆን እና የግሉ ዘርፍ መር የሆነ ምጣኔ-ሃብት ከተተገበረ ልማታዊ መንግሥት ፓሊሲ ልክ ደቡብ ኮሪያ እንዳመጣው ለውጥ በኢትዮጵያ ሊያመጣ ይችላል ይላሉ፤ ታደለ።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here