የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ለማከናወን ከኮሪያ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈረመ

0
855

በደቡባዊ ክፍል አዳዲስ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፊያ ጣቢያዎችን ለመገንባትና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ፕሮጀክት ግንባታ ለማከናወን ሀዮሰንግ ኮርፖሬሽን ከተሰኘ የኮሪያ ኩባንያ ጋር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ እና የሀዮሰንግ ኮርፖሬሽን ተወካይ ሀዩንግ ሶ ዩ ናቸው ተብሏል።

በደቡባዊ የኤሌክትሪክሲቲ ግሪድ ላይ አዳዲስ የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፊያ ጣቢያዎችን ለመገንባትና የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራዎችን ለማከናወን ነው ከኩባንያው ጋር ስምምነት የተደረገው ተብሏል።

ስምምነቱ 420 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታና የሦስት አዳዲስ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን የዲዛይን፣ ዕቃዎችን የማምረትና የማቅረብ፣ የመገንባት፣ የሙከራና ፍተሻ ሥራዎችን ለማከናወን እንዲሁም የኹለት ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም የማሳደግ ሥራዎችን ያጠቃልላል።

በፕሮጀክቱ ከወላይታ ሶዶ – ሽግዳን ባለ 230 ኪሎ ቮልት፣ ከሽግዳን – ጥርጋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት፣ ከወላይታ ሶዶ -ሽግዳን ከሚዘረጋው መስመር ላይ ተቀጥሎ ወደ አርባ ምንጭ ባለ 230 ኪሎ ቮልት፣ እንዲሁም አዲስ ከሚገነባው አርባ ምንጭ 2 ማከፋፈያ ጣቢያ እስከ ነባሩ አርባ ምንጭ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ድረስ የሚዘረጋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመሮቹ የሚገነቡ ይሆናል ተብሏል።

ከወላይታ ሶዶ -ሽግዳን የሚዘረጋው የማስተላለፊያ መስመር 240 ኪሎ ሜትር፣ ከሽግዳን- ጥርጋ የሚዘረጋው 77 ኪሎ ሜትር ይኖረዋልም ተብሏል።

በተጨማሪም ከወላይታ ሶዶ-ሽግዳን ከሚዘረጋው መስመር ላይ ተቀጥሎ ወደ አርባ ምንጭ የሚዘረጋው 93 ኪሎ ሜትር፣ እንዲሁም አዲስ ከሚገነባው አርባ ምንጭ 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ወደነባሩ አርባ ምንጭ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ 10 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንደሚኖረው ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱን ግንባታ በሦስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንና የፕሮጀክቱ በጀት ሙሉ በሙሉ ከኤክዚም ባንክ በተገኘ ከ178 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ብድር እንደሚሸፈን ስምምነት መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here