የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያደረገው የ18 በመቶ ደሞዝ ጭማሪ ውዝግብ አስነሳ

0
1304
  • የድርጅቱ የሠራተኛ ማህበር ጭማሪው ዋጋ ግሽበትንና የኑሮ ውድነት ያለበትን ደረጃ ያላገናዘበ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ22 ሺሕ በላይ ለሚሆኑት ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞቹ የደሞዛቸውን እስከ 18 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ቢያደርግም የዋጋ ግሽበትንና የኑሮ ውድነትን ያላገናዘበ ነው ሲሉ የድርጅቱ ሠራተኞች በማህበራቸው በኩል ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።

ጭማሪው ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ጀምሮ እስከ ሰኔ 1 ቀን 2011 ድረስ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ውሰጥ በቋሚነት እና በጊዜያዊነት ተቀጥረው እየሠሩ ላሉ ሠራተኞች እና የሥራ ኀላፊዎች የተደረገ ሲሆን፣ በደረጃ አራት እርከን ወይም የደሞዛቸውን 18 በመቶ በመጨመር ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።

በዓመታዊ የሥራ አፈፃፀም ምዘና ውጤታቸው ከ60 በመቶ በታች የሆኑ ሠራተኞች እና የሥራ አፈፃፀም ምዘና ውጤታቸው ከ65 በመቶ በታች የሆኑ የተቋሙ ሠራተኞች ከዓመታዊ የደሞዝ ጭማሪው ውስጥ አይካተቱም።

በሥራ ደረጃቸው ከደሞዝ እርከን ጣሪያ በላይ የሆኑ እና በጊዜያዊነት የተቀጠሩ ሠራተኞች እንዲሁም የሥራ ኀላፊዎች የደሞዛቸውን 11 በመቶ እንዲያገኙ ተደርጓል።
ለበርካታ ጊዜያት የተቋሙ ሠራተኞች የሥራው ባህርይ አድካሚ መሆኑን በማንሳት እና ክፍያው የኑሮ ውድነትን ያገናዘበ አለመሆኑን በመግለጽ የደሞዝ እርከን ማሻሻያ እንዲያደርግ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ሲያነሱ ነበር። አሁን የተደረገውም ጭማሪ ቢሆን አብዛኛውን ሠራተኛ ያላስደሰተ እና በየዓመቱ ከትርፍ ላይ የሚደረግ አነስተኛ ጭማሪ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተቋሙ ሠራተኞች ገልጸዋል።

አክለውም የደሞዝ እርክን እና እድገት ጥያቄውን ለሚመለከተው ክፍል በተደጋጋሚ ቢቀርብም እየታየ ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቶበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሰረታዊ የሠራተኞች ማህበር ሊቀ መንበር አድማሱ ወንድምአገኝ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ሠራተኛው በማህበሩ በኩል ለበርካታ ጊዜያት መሥሪያ ቤቱ የሚከፍለው ደሞዝ ለሠራተኛው ኑሮ የማይበቃ መሆኑን በመጥቀስ መሰረታዊ የደሞዝ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ ቢያቀርብም አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት ግን አልተቻለም።

በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት 18 በመቶ የደረሰ ሲሆን የምግብ ዋጋ ግሽበት 23 በመቶ ደርሷል። ይህ በሰባት ዓመት ውስጥ ከተመዘገበው የዋጋ ግሽበት ጋር ሲነፃፀር ትልቁ ሲሆን በድህነት አረንቋ የሚኖረው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ ይገኛል።

በተመሳሳይ፤ በአሁኑ ወቅት ያለውን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት መሰረት በማድረግ ከሐምሌ 2010 ጀምሮ ከኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ሠራተኛ ማህበሩ 11 ሰዎችን በመምረጥና ኮሚቴ በማቋቋም እንዲሁም አማካሪዎችን በመቅጠር በመሥሪያ ቤቱ ያሉትን የቆዩ አሰራሮች እና መመሪያዎች በመለወጥ የደሞዝ አከፋፈሉ የሠራተኞችን የትምህርት ደረጃ፣ የሥራ ልምድ እና አፈፃፀም መሰረት ያደረገ እንዲሆን የሚያስችል ጥናት ተደርጓል ሲሉ አድማሱ አብራርተዋል።

ጥናቱም በሰነድ ደረጃ የተጠናቀቀ ሲሆን ለተቋሙ ቦርድ አመራር ማቅረባቸውን ተናግረዋል። የአመራር ቦርዱ እስከ ጥቅምት 30 በመመልከት የደሞዝ እርከን ማሻሻያውን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል ብለዋል።

በማሻሻያውም የትራንስፖርት እና የውሎ አበል ክፍያዎች ላይም የተቋሙን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ ማሻሻያ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አድማሱ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 18 ሺሕ ቋሚ እና 4 ሺሕ ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ባለፈው በጀት ዓመት 10.1 ቢሊዮን ብር ከኀይል ሽያጭ እና መሰል ገቢዎች መሰብሰብ ችሏል።

ባለፈው ሳምንት ድርጅቱ በሰጠው መግለጫ መሰረት፤ ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ ኹለተኛ ዙር የታሪፍ ማሻሻያ ያደርጋል። ማሻሻያው በደንበኞች የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን በቀጣይ ኹለት ዓመታት ተከፋፍሎ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

መደበኛ እና አነስተኛ የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ላላቸው ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ድጎማ በማድረግ የታሪፍ ጭማሪው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ባላችው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጫና እንዳያደርስ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑም በመግለጫው ወቅት ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here