የትግራይ ክልል የማንነት አና የወሰን ጉዳዮች አዋጅ አንዲታገድ የፌዴሬሸን ምክር ቤትን ጠየቀ

0
572

ከትግራይ ክልል ምክር ቤት ተቃውሞ የቀረበበት የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይጣረስም በማለት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሰጠው ውሳኔ ላይ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ ያለው የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ አዋጁ ታግዶ እንዲቆይ ሲል ጠየቀ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን በሙያዊ ጉዳዮች ለማማከር እና የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎች ለምክር ቤቱ ከመቅረባቸው በፊት በመመልከት አስተያየት የሚሰጠው ጉባኤው፣ በአግባቡ ጭብጥ አልያዘም፣ የተሰጠው ውሳኔ ከተጠየቀው ጋር አይያያዝም፣ ከተፈቀደለት የሥልጣን ወሰን በመውጣት የሕገ መንግሥት ትርጉም ውስጥ ገብቷል በሚል ይግባኝ ማቅረቡን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኀላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ክልሉን የወከለው የፍትህ ቢሮው የአዋጁ 12 ነጥቦች ሕገ መንግሥቱን ይቃረናሉ በሚል ነበር አጣሪ ጉባኤው አቤቱታውን ያስገባው። ከተነሱት ነጥቦች መካከልም የአዋጁ ስያሜ ‹‹የአስተዳደር ወሰን›› የሚል ቃል መጠቀሙ አግባብ አይደለም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይም ክልሎች አስተዳደሮች ሳይሆኑ በድንበር የተከለሉ ናቸው የሚል እንደሆነ የፍትህ ቢሮ ኀላፊው አማኑኤል አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተመሳሳይም የማንነት ጉዳዮች ላይ የክልል ምክር ቤቶች ሥልጣን ተሰጥቷቸው ሳለ በፌዴራል መንግሥት የተቋቋመው እና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነው ኮሚሽኑ ጣልቃ መግባቱ አግባብ አይደለም የሚለው ይገኝበታል። በኹለት ክልሎች መካከል ያለ የድንበር ችግር ቢኖር ኹለቱም ክልሎች በመረዳዳት የሚፈቱት ሲሆን ቅር ያለው ወገን ወደ ፌዴሬሸን ምክር ቤት በመሔድ ቅሬታውን እንዲያስገባ ሕገ መንግሥቱ ማስቀመጡ እነዚህ ጉዳዮች ለክልሎች የተሰጡ እና የፌዴራሉ መንግሥት ሥልጣንም በይግባኝ የተገደበ አንደሆነ የሚያስረዳ በመሆኑ አዋጁ ሕገ መንግሥቱን ጥሷል ሲሉ አማኑኤል ተናግረዋል።

‹‹ጉባኤው ያቀረብነውን 12 ነጥቦች በአግባቡ ሳይመረምር ሦስት ጭብጦችን ብቻ በመያዝ መብታችንን ተጋፍቷል›› ሲሉም አክለዋል። ‹‹ይህ ክርክር በግለሰቦች መካከል እንዳለ ጉዳይ ሳይሆን የአገር ህልውና ላይ የራሱን ጫና ይዞ የሚመጣ እና ለወደፊትም ታሪክ የሚሆን መዝገብ ነው›› ያሉት አብርሃም ‹‹የጉባኤው አባላትም ይህንን ስለሚያውቁ ስማቸውን እንኳን በውሳኔው ላይ ማሳረፍ አልፈለጉም፣ ይህም ምልአተ ጉባኤው መሟላቱን እና የተሰጠው ድምፅም ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አንዳንችል አድርጎናል›› ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

የኮሚሸኑ ተግባራትም የማማከር እና ጥናት የማድረግ ነው በሚል የአጣሪ ጉባኤው የሰጠው አስተያየት ራሱ እንደ ሕገ መንግሥት ትርጉም የሚወሰድ ቢሆንም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተመሳሳይ የሚተረጉም ከሆነ የኮሚሽኑን ተግባር ወደ ኮሚቴ ዝቅ የሚያደርግ በመሆኑ አግባብ እንዳለው ፍርድ እንደሚቀበሉትም ተናግረዋል።

ሕገ መንግሥቱ የፌዴሬሸን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም ለመስጠት የተለያዩ ጊዜአዊ እና ቋሚ ኮሚቴዎችን ያቋቁማል ሲል መደንገጉን ተከትሎ፣ ነገር ግን ይህ ኮሚሽን የማማከር ሥራውንም ቢሆን መሥራቱ አግባብ አለመሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።

‹‹ይህ ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ የሲዳማ የማንነት ጥያቄ ተነስቷል ነገር ግን ጉዳዩ እየተስተናገደ ያለው በሕገ መንግሥቱ መሰረት ነው። አጣሪ ኮሚሽኑ በሲዳማ ጉዳይ ላይ ምንም ሥራ አለመሥራቱ ከዚህ በኋላ ለሚሠራቸው ሥራዎች እንቅፋት የሚሆን ነው፣ ጉዳይ እየመረጡ መያዝም ከፍትህ ዓላማዎች ጋር ይጣረሳል›› ሲሉ አማኑኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑም አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ሳይወጣ በፊት የተቋቋመ መሆኑ ከተነሱት ቅሬታዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው አቤቱታ በአግባቡ ለመመርመር እንኳን ፍላጎት አላሳየም፣ ነገር ግን ምክር ቤቱ ይህንን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይመለከተዋል ብለን እናምናለን ሲሉም ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ከፌዴሬሸን ምክር ቤት ያገኘችው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የይግባኝ አቤቱታው የቀረበ ሲሆን በቅርቡም ምክር ቤቱ ጉባኤውን ሲያካሒድ ለውሳኔ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። አጣሪ ጉባኤው ላይ የቀረቡ በተለይም የምልአተ ጉባኤ እና የድምፅ አሰጣጥ ግልጽነት ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች ላይ አስተያየት ለመቀበል በስልክ ያደረግነው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here