የገቢዎች ሚኒስቴር በሩብ ዓመት በታሪክ ትልቁን ግብር ሰበሰበ

0
658
  • በሦስት ወራት ውስጥ 56 ቢሊዮን ብር ግብር መሰብሰብ ተችሏል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሁም የንግድ መቀዛቀዝ ቢቀጥልም የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት ወራት ከተለያዩ ምንጮች የሰበሰበው ግብር የ13 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል። በ2011 በጀት ዓመት 56 ቢሊዮን ብር አቅዶ 57 ቢሊዮን ብር የሰበሰበው ሚኒስቴሩ የዕቅዱን 102 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቋል።
አርብ ጥቅምት 7፣ 2011 ሳሪስ ሙለጌ ህንጻ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤታቸው መግለጫ የሰጡት ሚኒስትሯ አዳነች አበቤ እንደገለፁት፤ ለተገኘው ጭማሪ ዋነኛ ምክንያቶች ግብር ከፋዮችን በማስተማር በተሰራው ሥራ እንዲሁም በተወሰዱ ሕግ የማስከበር እርምጃዎች እና ሠራተኞች በትጋትና በቁርጠኝነት የሥራ ድርሻቸወን በመወጣታቸው ነው።

ይሁን እንጂ፤ በአገሪቷ የነበረው አለመረጋጋት በባለፉት ሦስት ወራት ውስጥም መጠናከሩ ለግብር አሰባሰብ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑ ከንግድ መቀዛቀዝ ጋር ተዳምሮ ጭማሪው ያልተጠበቀ ሲሆን በተለይም የበጀት ጉድለት ወደ 90 ቢሊዮን በደረሰበት በጀት ዓመት ላይ የታየው ከፍተኛ ለውጥ ጉድለቱን ከመሙላት አኳያ ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል።

ባለፉት ሦስት ወራት የግብር አፈፃፀም በወራት ሲከፋፈል በሐምሌ ወር 18 ቢሊዮን ብር ሲሰበሰብ፤ በነሐሴ ወር 20 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲሁም መስከረም ላይ 19 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል። የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ማሳያ ከሆነው መርካቶ ገበያ ውስጥ የጫማ አከፋፋይና ነጋዴ የሆነው አማኑኤል መንግሥቱ በተገኘው ለውጥ ቢደነቅም ጭማሪው የውጤታማነት ማሳያ ላይሆን ይችላል ከሚሉት መካከል አንዱ ነው።

‹‹ባለፈው በጀት ዓመት (2011) ነሐሴ እና መስከረም ወራት የነበረው የአገሪቷ ሁኔታ በጣም ከፍተኛ የንግድ መቀዛቀዝ እና ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት ያልነበረበት ወቅት የነበረ መሆኑ አሁን ለታየው ከፍተኛ ጭማሪ ዋነኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል›› ይላል አማኑኤል።

በእርግጥ ባፈው ዓመት መስከረም 2011 ከፍተኛ ግጭት የተከሰተበት ወር ሲሆን ለአብነትም መስከረም 2 የተከሰተውን በቡራዩና አካባቢው ባሉ ከተሞች በደረሰ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ሕይወት ያልፈበትና በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተፈናቀሉበት፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በመጡ ወጣቶችና ፒያሳ አካባቢ ባሉ ወጣቶች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ረብሻ የተፈጠረበት እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ግጭቶች የደረሰበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዚህ ዓመት የተገኘው ጭማሪ የባለፈው በጀት ዓመት ደካማ አፈፃፀም ነፀብራቅ ነው የሚለው አማኑኤል፣ ባለፈው በጀት ዓመት ብዙ ነጋዴዎች ኪሳራ ያስመዘገቡበት ዓመት እንደነበርም አስታውሷል። የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 14 ሺሕ 96 ነጋዴዎች ኪሳራ አውጀው ፈቃዳቸውን መልሰዋል። ነገር ግን፤ የንግድ መቀዛቀዙ በዚህ በጀት ዓመት መሻሻል እንዳሳየ መረጃዎች ያሳያሉ።

የተገኘው ግብር ከተገኘበት ምንጭ ሲከፋፈል ከአገር ውስጥ የተገኘው ገቢ 31 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ሲሆን ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 24 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል፤ ቀሪው ከሎተሪ ሽያጭ የተገኘ ነው። ወደ 21 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ግብር ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች የተሰበሰበ ሲሆን 17 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከ15 ቅርንጫፎች፣ 10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ደግሞ ከሞጆ ደረቅ ወደብ የተሰበሰበ ነው።

የምጣኔ ሃብት ምሁር የሆኑት አለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) ባለፉት ሦስት ወራት የተመዘገበው ግብር ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል ከሚሉት መካከል ይመደባሉ። ‹‹የወጪ እና የአገር ውስጥ ንግድ በተቀዛቀዘበት ወቅት እንዲሁም የፖለቲካው መረጋጋት ብዙም ለውጥ ባላሳየበት ሁኔታ ይህን ያህል ለውጥ መምጣቱ አስገራሚ ነው›› ያሉት አለማየሁ ይህ ዓይነቱ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በአስተዳደራዊ እርምጃ ነው ብለዋል።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት የታክስ ባለሙያው ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል በበኩላቸው፣ የውጭ ምንዛሬ ችግር ጣራ በደረሰበት እና ምርታማነት ባልጨመረበት ወቅት ላይ ከፍተኛ የግብር ጭማሪ መታየቱ አስገራሚ ነው ያሉ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ የተጋነነ ጭማሪ የመጣበት መንገድ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር አዳነች አበቤ ለግብር መጨመሩ እንደ ምክንያት ያነሷቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሲሆኑ የመጀመሪያው ግብር ከፋዩን የማስተማር ሥራዎች ናቸው ብለዋል። ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ የተሠሩ የሕግ ማስከበር ሥራዎች ሲሆኑ ከነዚህም መካከል በግብይት ወቅት ደረሰኝ የማይቆርጡ ድርጅቶች እና ሀሰተኛ ደረሰኝ የሚጠቀሙትን በመለየት የተወሰዱት እርምጃዎች መሆናቸውን ሚኒስትሯ ለአብነት ጠቅሰዋል።

አመራሮችና ሠራተኞች የእረፍት ጊዜያቸውን በመጠቀምና አምሽተው በመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸው ለተሰበሰበው ግብር መጨመር በሦስተኝነት በሚኒስትሯ የተጠቀሰው ምክንያት ነው። በ2011 በጀት ዓመት 160 ቢሊዮን ብር ግብር የተሰበሰበ ሲሆን በአሁኑ በጀት ዓመት 190 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here