”ተፋላሚ አካላት እና ደጋፊዎቻቸው ከማንኛውም የጦርነት ፕሮፓጋንዳና የግጭት አባባሽ ንግግሮች እንዲሁም ድርጊቶች ይቆጠቡ!”:- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች

0
854

ማክሰኞ ጷግሜ 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ተፋላሚ አካላትና ደጋፊዎቻቸው ከማንኛውም የጦርነት ፕሮፓጋንዳ እና የግጭት አባባሽ ንግግሮች እንዲሁም ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ሲሉ ከሠላሳ በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥሪ አቅርበዋል።

ድርጅቶቹ ዛሬ ጳጉሜ 1 ቀን 2014 ረፉድ በኢንተር ለግዠሪ ሆቴል ሊሰጡ የነበረው መግለጫ መሰረዙን ተከትሎ፤ ከሰዓት ላይ በበይነ መረብ <ጉግል ሚት> በሰጡት መግለጫ ነው ይህን ጥሪ ያቀረቡት።

በመግለጫውም ድርጅቶቹ፤ የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ካልተፈቱ አገሪቱ መውጣት የማትችልበት ቀውስ ውስጥ ትገባልች የሚል ስጋት አለን ብለዋል። በዚህም የተነሳ ስምንት ነጥቦችን በማንሳት አስቸኳይ ጥሪ አስተላልፈዋል።

አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ፣ የዛሬ ዓመት ተመሳሳይ የሰላም ጥሪ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ <<በተፋላሚ ወገኖች መካከል ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገ የተኩስ አቁም ሥምምነት መደረጉ እና ተፋላሚ ወገኖች ለሰላም ድርድር ፍላጎት ማሳየታቸው ትልቅ ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጎን ነበር።>> ብለዋል። ነገር ግን እንደገና አዲስ ጦርነት መቀስቀሱ እጅግ አሳዝኖናል ሲሉም ገልጸዋል።

<<ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሔዱ ነው። እነዚህ ግጭቶች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ እና የአካል ጉዳት እያስከተሉ ነው። ሴቶች መደፈርና ሌሎችም ዘግናኝ ጥቃቶች እየተፈፀሙባቸው ይገኛል። በርካታ ኢትዮጵያውያንም በግጭቶቹ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።>> በማለትም የደረሱ ቀውሶችን በመግለጫቸው አውስተዋል።

እናም በሰላም ጥሪያቸው ሐቀኛ፣ ሰላማዊና የግጭቶቹ ተሳታፊ አካላትን በሙሉ ያካተቱ የእርቅ ንግግሮች እንዲጀመሩ፣ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የተቋረጡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲደርሱ፣ የፆታ ጥቃትን የፈፀሙ የተዋጊ አካላትን ጨምሮ ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ያደረሱ አካላት ላይ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ የተጠያቂነት እርምጃ እንዲወሰድ፣ በግጭቶች ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ፈጣን የሕክምና እና የማኅበረ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ብሔር ተኮር ጥቃቶችና አግላይ ድርጊቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

ከዛም በተጨማሪ፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ መገናኛ ብዙኀን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና አክቲቪስቶች ድምፃቸውን ለሰላም እና ለእርቅ ብቻ እንዲያውሉ የጠየቁ ሲሆን፤ የተጀመረው የአገራዊ ምክክር ሒደት ሁሉን አካታችና አሳታፊ፣ ግልጽ እንዲሁም የአገሪቱን የአጭርና የረዥም ጊዜ ችግሮች ለመፍታት የብዙኃንን ይሁንታ ያገኘ አካሔድ እንዲከተል በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ ረፋድ ላይ ይህ መግለጫ እንዳይደረግ መከልከሉን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን፤ ድርጅቶቹ ይህን በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል።

በዚህም <<ማንነታቸውን ያልገለጹ ነገር ግን የመንግሥት አካል ነን ያሉ ግለሰቦች፣ ባልተገለጸ ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫውን መስጠት እንደማይፈቀድልን ነግረውን አስተጓጉለውብናል። ይህንን ክልከላ ያዘዘው አካል ማን እንደሆነ ብንጠይቅም መልስ አላገኘንም።>> ብለዋል።

አክለውም <<የዚህ መግለጫ አዘጋጅ አገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከምናውቀው ድረስ፣ ለመንግሥት የፀጥታ አካላት ቅድሚያ ማሳወቅ የሚጠይቁት የአደባባይ ሰልፎች ብቻ ናቸው። ይህ ዓይነቱ አሠራር የሕግ የበላይነትን የሚፃረር ከመሆኑም ባሻገር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ሊጫወቱ የሚገባቸውን ድርሻ ይነፍጋል።>> ያሉ ሲሆን፤ በድርጊቱ ማዘናቸውን ጠቅሰውም እንዲታረም አሳስበዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here