የዱባይ ቱሪዝም ከመስከረም 5 ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ትዕይንቶችን ያከናውናል

0
963

ሐሙስ ጷጉሜ 3 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ዱባይን የዓለም ኢኮኖሚ ዋና ማዕከል፣ የኢንቨስትመንት እንብርትና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየሠራ የሚገኘው፤ የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት (DET) ከመስከረም 5 ቀን 2015 ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ትዕይንቶችን ለማከናወን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።

በዱባይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የቱሪዝም ሐሳብ ለአፍሪካውያን ቱሪስቶች የማሳየት እንቅሰቃሴን እያደረገ የሚገኘው የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት (DET)፤ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራባቸው የሚገኙ ዋነኛ የአፍሪካ አገራት ናቸው።

በዚህም መሰረት ዲፓርትመንቱ፤ ከዚህ ቀደም በናይጄሪያ እና በደቡብ አፍሪካ በተሳካ መልኩ ትዕይንቶቹን ያከናወነ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ከመስከረም 5 ቀን 2015 ጀምሮ፣ በኡጋንዳ ከመስከረም 9 ቀን 2015 ጀምሮ እንዲሁም በኬንያ ከመስከረም 12 ቀን 2015 ጀምሮ ትዕይንቶቹን ለማከናወን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የእነዚህ ትዕይንቶች መዘጋጀት ዋንኛ አላማም ከአጋሮች ጋር በመሆን በመስተንግዶ፣ በህክምና፣ በመዝናኛ እና በችርቻሮ ዘርፍ የሚገኙ ቁልፍ የንግድ አጋሮችን ማገናኘት መሆኑንም ተገልጿል።

ትዕይንቶቹም በጉዞ፣ በእንግዳ አቀባበል በመዝናኛ፣ በቤተሰብ ጉዞ፣ በትምህርት፣ በህክምና ቱሪዝም እንዲሁም በዱባይ ከተማ አቀፍ ዝግጅቶች ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ሲሆን፤ የኔትዎርክ ክፍለ ጊዜዎች፣ የአጋሮች ትውውቅ፣ የአንድ ለአንድ ስብሰባዎች እና የህክምና ተቋማትን የማሻሻል ሥራዎችንም የዝግጅቶቹ ዋና ዋና ክፍሎች መሆናቸውም ተነግሯል።

በተጨማሪም ዲፓርትመንቱ የቱሪዝም ዘርፎች ላይ እየሠራ የሚገኘውን ሥራ የማስተዋወቅ፤ በኢትዮጵያ ባሉ የቱሪዝም አማራጮች ላይ በመወያየት ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እና አጋርነት ለመፍጠር መታቀዱ የተገለጸ ሲሆን፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና የቱሪዝም ዘርፉ ዋና ተዋናዮች በኹነቶቹ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ የጉዞ ወኪሎች እና አስጎብኚ ድርጅቶች ንግዳቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍ እና ሥልጠና የሚያገኙበትን መንገድም በዲፓርትመንቱ በኩል እንደሚመቻች ተገልጿል።የዱባይ የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዲፓርትመንት በዱባይ ውስጥ ለሚገኙ ሆቴሎችና ለኹሉም የንግድ ዓይነቶች ፈቃድ እና ምደባ የሚሰጥ፤ የቱሪዝም እና የንግድ ግብይቶች፣ ፌስቲቫሎች እና የችርቻሮ ንግዶችን ጨምሮ የዱባይ ኢንዱስትሪዎችን፣ ላኪዎችን እንዲሁም የዱባይ ኢንቨስትመንት ልማት ኤጀንሲን የሚቆጣጠር፣ ዕቅድ የሚያወጣ እና የሚያለማ ዋና ባለሥልጣን ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here