ራይድ ትራንስፖርት ዛይ ራይድ ስያሜዬን ተጠቅሟል ብሎ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ

0
1438

ራይድ ትራንፖርት የቅርብ ተወዳዳሪው ዛይ ራይድ ታክሲ ላይ አቅርቦት የነበረው ከስያሜ እና ከንግድ ምልክት ባለቤትነት ጋር የተያያዘ አቤቱታ ለክስ የሚያበቃ ምክንያት የለውም በማለት የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ውድቅ አደረገው።

ኹለቱ ተቋማት የትራንስፖርት አገልግሎትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ተጠቃሚዎችን እና ደንበኞችን በስልክ መተግበሪያዎች በማገናኘት የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሲሆን ከንግድ ስያሜ እና ከባለቤትነት መብት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ወዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር የሚታወስ ነው።

ሃይብሪድ ዲዛይን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባቀረበው አቤቱታ፤ ዛይ ራይድ ትራንስፖርት ራይድ የሚለው የንግድ ስያሜ ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በኩል ለሃይብሪድ ዲዛይን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጥበቃ እንደተደረገለት እያወቀ ራይድ በሚለው ቃል ላይ ዛይ የሚል ቃልን በመጨመር ደንበኞችን እና ህብረተሰቡን በማጭበርበር እና እንዲደናገሩ በማድረግ፤ የድርጅቱን መልካም ስም በሚያበላሽ መልኩ ያልተገባ የንግድ ውድድር ፈፅሞብኛል የሚል ነው።
በተጨማሪም በቃላት መመሳሰሉ ደንበኞች የእኛ አገልግሎት እየመሰላቸው ወደ ዛይ ራይድ እየሄዱ ነው የሚል እንደነበር የሃይብሪድ አቤቱታ ያሳያል።

ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ክስ አቀባበል እና ምርመራ ዳይሬክቶሬት ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ጋር ጉዳዩን በጋራ እንዳጣራ ገልጿል።

ባለሥልጣኑም ሀይብሪድ ዲዛይን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ያስመዘገበው የንግድ ምልክት በብቸኝነት እንዲጠቀም የተፈቀደለት እና ጥበቃንም ያገኘው በመተግበሪያዎች ሥራ እና ልማት ዘርፍ እንጂ በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ አለመሆኑን ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በኩል በተላከ ደብዳቤ አረጋግጧል። ጥበቃውም ከዚህ አገልግሎት ውጪ ሊደረግ እንደማይችል መረዳት መቻሉን የባለሥልጣኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አልቃድር ኢብራሂም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ራይድ የሚለው ቃል በኢኮኖሚያዊ እና ንግድ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች በጋራ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እና በተለይም በታክሲ እና በትራንስፖርት ዘርፍ የተለመደ እንዲሁም የጋራ አገልግሎትን የሚያመለክት ስያሜ በመሆኑ ለአንድ ተቋም ብቻ በንግድ ምልክትነት ለመስጠት እንደማይቻል የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ መግለፁን ተናግረዋል።

ራድይ በሚለው የንግድ ስያሜ መመሳሰልን ለማጣራት የሕግ እና የቴክኒክ ባለሙያዎችን በመመደብ ምርመራ እንዳደረገ እና ንግድ ስያሜው በቃላት አጣጣል እና ዕይታ አንፃር ልዩነት ያለው መሆኑን እና በቀላሉ ለመለየት አስቸጋሪ አለመሆኑን በማጣራት አቤቱታው ተቀባይነት እንደሌለው ባለሥልጣኑ ገልጿል። ኹለቱም የየራሳቸው የስልክ መተግበሪያ እና የስልክ የጥሪ ማዕከል ያላቸው በመሆኑ ደንበኞችን ሊያሳስት የሚችል ክፍተት አለመኖሩንም ለማረጋገጥ እንደተቻለ ተገልጿል።
እነዚህን መረጃዎች መሰረት በማድረግ ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ክስ አቀባበል እና ምርመራ ዳይሬክቶሬት በጉዳዩ ላይ ለክስ የሚያበቃ ምክንያት የለም በማለት አቤቱታውን ውድቅ አድረጎታል።

የዛይ ራይድ መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሀብታሙ ታደሰ በወሳኔው እና እውነቱ በመውጣቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው፣ ከዚህ ቀደም ራይድ ትራንስፖርት እኛ ከአራት ዓመታት በፊት ዛይ ራይድ በሚል ስም ለኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ያስገባነውን ስያሜ የራሳቸው በማስመሰል ለማስመዝገብ መሞከራቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ስላለን እሱንም ለማስተካከል በሕግ አግባብ ጥያቄ እናቀርባለን ብለዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የራይድ ትራንስፖርት መስራች እና ባለቤት ሳምራዊት ፍቅሩን ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here