እናመሠግናለን!

0
666

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ ገንዘብ ሚኒስቴር የመፍቀዱን ዜና ከሰሞኑ ዐየሁ። ይህ እንዲሆን ለሠሩ ምሥጋና ማቅረብ ተገቢ በመሆኑን ለማመሥገን ወደዚህ መጣሁ።

ይህ ከቀረጥ ነጻ እንዲሆን የተሰጠው ፈቃድ በዋናነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጀት ይዞ በመግዛት በስሩ ለሚታደሩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ለማቅረብ ከማቀዱ ጋር የተያያዘ ነው። የንጽህና መጠበቂያው ከቀረጥ ነጻ ይገባል የተባለውም ለዚሁ አገልግሎት እንደሆነ የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ቢሮ አስታውቋል።

እንደሚታወቀው የምገባ ኤጀንሲ በተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ነው። ይህም ከኹለት ዓመት ገደማ በፊት የጀመረ እንደሆነ በጉዳዩ ዙሪያ ከወጡ ዘገባዎች ተመልክቻለሁ። ታድያ ከዚህ የምገባና የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት አገልግሎት በተጓደኝ ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ማቅረብም ተካትቶ ነበር ተብሏል።

ተግባራዊ ሊሆን የቻለው መች እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም። ነገር ግን አሁን ከቀረጥ ነጻ የተፈቀደው ለዚሁ አገልግሎት መሆኑ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ዜና ነው።

በወር አበባ ሰሞን ከትምህርት ቤት የሚቀሩ ሴት ተማሪዎች ጥቂት አይደሉም። ይህ ምንአልባት በከተማ የሌለ ይመስል ይሆናል እንጂ መራሩ ሀቅ ግን እንደዛ አይደለም። እንደውም የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በ2014 አደረግኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት በወር አምስት ቀን እንዲሁም በዓመት 50 ቀናት ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው በዚህ የተነሳ ይቀራሉ።

ሪፖርተር ጋዜጣ ይዞት የወጣው ዘገባ ላይ እንደተጠቀሰው ደግሞ፣ በዚህ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከ300 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ የሚደርሱ ሴት ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የተለያዩ ማኅበራትና ግለሰቦችም ጭምር ሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ማግኘት ባለመቻል ከትምህርት ቤት የመቅረታቸው ነገር አሳስቧቸው ብዙ ሠርተዋል። የዋጋውን መጨመር ተከትሎም ሊታጠቡና ለረጅም ጊዜ ሊያገለግሉ የሚችሉ የጨርቅ የንጽህና መጠበቂያዎችን ያመረቱና በነጻ ያከፋፈሉም አሉ።

በጉደዩ ላይ ንቅናቄ እንዲፈጠር ይቀሰቅሱ የነበሩ፣ በየቦታው ድምጻቸውን ያሰሙ፣ የታገሉና ይህ ውጤት እንዲመጣም ምክንያት የሆኑ ጥቂት አይደሉም። ሁሉንም እናመሠግናለን፡፡

በነገራችን ላይ ይህ የሚያስደስት ዜና መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁንም ግን በአገር ደረጃ ገና ሥራ የሚፈልግ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህም ልክ በአዲስ አበባ እንደሆነው በአገር ዐቀፍ ደረጃም እንዲሆን ብዙ ግፊትና ጥረት እንደሚጠይቅ አያጠራጥርም። ከዚህ ቀደም በግል ድርጅት ለሚገባ የንጽህና መጠበቂያ ቀረጡ ከ30 ወደ 10 በመቶ መቀነሱና ከተጨማሪ ታክስም ነጻ መደረጉ አይዘነጋም።
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here