የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በመጪው 2015 ሦስት አዳዲስ የቴሌቪዥን ቻናሎችን ሊከፍት መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታወቀ።
ትኩረቱን በሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ያደረገው አንደኛው የቴሌቪዥን ቻናል፤ በመስከረም ወር የመጀመሪያ ሳምንት የሙከራ ስርጭቱን ይጀምራል ተብሏል።
ብሔራዊ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በስሩ የሚያስተዳድረው ኢቢሲ፤ በአሁኑ ወቅት ሦስት የቴሌቪዥን ቻናሎች አሉት። የመጀመሪያው ቻናል ሙሉ ለሙሉ ለዜና እና ወቅታዊ ዝግጅቶች የተመደበ ሲሆን፣ ኹለተኛው በተለያዩ ቋንቋዎች የሚካሄዱ ስርጭቶችን የሚያስተናግድ ነው። ሦስተኛው ቻናል የመዝናኛ ዜናዎች እና ዝግጅቶች የሚተላለፉበት ነው።
ኢቢሲ በ2015 ከሚከፍታቸው አዳዲስ ቻናሎች ውስጥ ከሞላ ጎደል የዝግጅት ሥራው የተጠናቀቀው የሕጻናት እና ታዳጊዎች ይዘት በተለየ ሁኔታ የሚስተናገድበት ቻናል እንደሆነ ታውቋል።
የሙከራ ስርጭቱ በአዲሱ ዓመት መስከረም ወር የመጀመሪያ ሳምንት እንደሚጀምር የተጠቆመ ሲሆን፣ ቻናሉ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባሉት ጊዜያት ወደ መደበኛ ስርጭት እንደሚገባ ነው የተገለጸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014



