በኢትዮጵያ በስፋቱ የመጀመሪያ የሆነ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተመረቀ

0
744

በኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ካስገነባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በስፋቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ኢንዱስትሪ ፓርክ በድሬዳዋ ተመረቀ። ውሺ ቁጥር 1 የተሰኘው ይህ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአርባ ሔክታር መሬት ላይ ተንጣለለ ሲሆን ለጨርቃ ጨርቅ አምራች ኩባንያዎችም ጥሬ ዕቃዎችን በመላክ ዘርፍ የተሰማራ እንደሆነ የኩባንያው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በ220 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው እና በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ለ3ሽሕ ኢትዮጵያዊያን የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ የታሰበው ውሺ ቁጥር 1 ኢንዱስትሪ ፓርክ ሐሙስ ጥቅምት 6/2012 በይፋ ተመርቋል። ውሺ ቁጥር 1 ኢንዱስትሪ ፓርኩን ባስመረቀበት ቀን ኩባንያውን አንድ መቶኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንም በተመሳሳይ አክብሯል። በቻይናው የግንባታ ኩባንያ ሲሲኢሲሲ የተገነባው አዲሱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ጥጥ ከአዎስትራሊያ በማስመጣት አቀነባብሮ ለውጭ ገበያ በመላክ ስራ እንደሚሰማራ አዲስ ማለዳ ከስፍራው በመገኘት የስራ ኃላፊዎችን አነጋግራለች።

በሲሲኢሲሲ የተገነባው ውሺ ቁጥር 1 ያቀነባበረውን ጥሬ ዕቃ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ኮሪያ፣ ጃፓን እና ደቡብ ምስራቅ አውሮፓ እንደሚልክ አስታውቋል። ኢንዱስትሪ ፓርኩ በይፋ ይመረቅ እንጂ አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል ስላልገባለት ስራውን ለመጀመር እንደሚቸገር እና በቅርቡ አስፈላጊው ኃይል ይደርላቸዋል መባሉንም ኃላፊዎች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቻይናዊው የግንባታ ኩባንያ ሲሲኢሲሲ ከውሺ ቁጥር 1 የኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በርካታ በኢትዮጵያ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ቻይናዊ ኩባንያ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here