በዘንድሮው ዓመት ከሌሎች ዓመታት በተለየ መልኩ ከቡና የውጪ ንግድ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል
በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከቡና ዘርፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ይህን የገለጸው ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የዘንድሮውን የኢትዮጵያ የቡና ቀንን ‹‹ቡናችን ለአብሮነታችን እና ለብልፅግናችን›› በሚል መሪ ቃል ባሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች ባከበረበት መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መአዛ አሸናፊ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት ደስታ ሌዳሞ፣ የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የቡና ኤክስፐርቶች፣ ላኪዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዑመር ሁሴን በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የቡና ዘርፉ በግብርና ዘረፍ ካሉት የውጭ ምንዛሪ ግኝት የጎላ ድርሻ እንደነበረው የገለጹ ሲሆን፤ በዘንድሮው ዓመት ከሌሎች ዓመታት በተለየ መልኩ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።
ለዚህም እመርታ አስተዋጾዖ ለነበራቸው ባለድርሻ አካላት እውቅናና ሽልማት መስጠት በማስፈለጉም መድረኩ መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ በጽሁፋቸውም ኢትዮጵያ እንደ አገር የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን ከ15 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቡና ዘርፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል። በዚህ ምክንያት ቡና ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ወርቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የቡና ምርትና ኤክስፖርት ወደ 300 ሺህ ኩንታል እያደገ እንደመጣና 843 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢም እያመጣ እንደሚገኝ ዶ/ር አዱኛ ጨምረው ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የቡና ምርት ገቢ እንዲያድግ አስተዋጽዖ ላደረጉ ላኪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ የህብረት ሥራ ዩኒየኖች፣ ባለሙያዎችና ተቋማትን ጨምሮ በአጠቃላይ 267 ባለድርሻ አካላት ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እውቅና የተበረከተላቸው ሲሆን፤ አንድ ኪሎ ቡና 47ሺ ብር በተሸጠበት የ‹‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› ውድድር አሸናፊ ለሆኑ አርሶ አደሮች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በተጨማሪም በግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን የተመራ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩም የቡና ምርትና ምርታማነት በተፈለገው መልኩ እንዲያድግ ከባለሃብቱ ምን ይጠበቃል?፣ የኤክስፖርትን መጠን በአለም ገበያ ለማሳደግና አገራችንን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅራቢው ምን መሰራት ይኖርበታል? እንዲሁም እንደ አገር የአርቢካ ቡና በአየር ንብረት ለውጥ በመጠቃት የሚያጋጥመውን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው የሚሉ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015