በዋግኽምራ ዞን 5 ወረዳዎች በዘር አለመሸፈናቸውና ቡቃያዎች ከጥቅም ውጪ መሆናቸው ተገለጸ

0
1133

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ብቻ ከስደስት በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች የሚገኙ የእርሻ መሬቶች በዘር አለመሸፈናቸውና የተዘራባቸው ቡቃያዎችም ተሰባብረው ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የግብርና መምሪያ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ጋዝጅብል፤ ሰቆጣ፤ በዝቋላ እንዲሁም በጻግብጅና አበርገሌ ወረዳ የሚገኙ የእርሻ መሬቶች በሰብል እንዳልተሸፈኑና ቡቃያዎችም ከጥቅም ውጪ እንደሆኑ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የግብርና መምሪያ ኃላፊ አዲሱ ወልዴ ገልጸዋል። ጉዳቱ የተባባሰው በተለይም ከነሐሴ 18/2014 ጀምሮ ለሦስተኛ ጊዜ የሕወሓት ታጣቂ ቡድን በቀሰቀሰው ጦርነት ነው ተብሏል።

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የሰላም መደፍረስ በተከሰተባቸው የተለያዩ ስፍራዎች በዘር ያልተሸፈኑ የእርሻ መሬቶችን በተመለከተ ያለውን መረጃ ከየክልሉ አጣሩ እንጂ ተቋሙ እስካሁን የሚያውቀው መረጃ የለም የሚል ምላሽ ለአዲስ ማለዳ ሰጥቷል። በጦርነት ቀጠና ውስጥ ባሉ ስፍራዎች የሚገኙ ባለድርሻ አካላት እና አርሶ አደሮች በአንጻሩ በ2014 የክረምት ወቅት በዘር ያልተሸፈኑ መሬቶች እንዳሉ ነው የጠቆሙት።

ከእነዚህም መካከል የዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን አንዱ ሲሆን፤ የግብርና መምሪያ ኃላፊው፤ አበርገሌና ጻግብጅ ወረዳ በጠላት እጅ የተያዙ በመሆናቸው በዘር መሸፈናቸው እና አለመሸፈናቸው አይታወቅም ብለዋል። እንደ ግምታቸው ግን በዘር የመሸፈን እድላቸው የጠበበ ነው።

በተያያዘም፣ ሕወሓት ለሦስተኛ ጊዜ በቀሰቀሰው ጦርነት በጋዝጅብል፤ ሰቆጣና ዝቋላ ወረዳ የነበሩ ቡቃያዎች ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን አዲሱ ተናግረዋል።

በሰቆጣ ወረዳ በተለይም ሦስት ቀበሌዎች በዘር የተሸፈኑ መሬቶች በታጣቂ ቡድኑ ከጥቅም ውጭ ከሆኑት መካከል ናቸው። በወረዳው ስር የሚገኙ ኪያ፤ ሐሙሲት እና ወለህ የተሰኙት ቀበሌዎች የጦርነት ሜዳ በመሆናቸው ሰብሎችም ተሰባብረዋል ብለዋል ኃላፊው።

በወረዳው ስንዴ፤ ጤፍ እንዲሁም ሌሎች የብዕር ሰብሎችና ጥራጥሬዎች ይመረቱበታል የተባለ ሲሆን፤ በሰቆጣ ከተማ በክላስተርነት የተያዘ የስንዴ ቡቃያ መጠነ ሰፊ ጉዳት እንደደረሰበት ተመላክቷል። በተያያዘም በጋዝጅብል ወረዳ ዛሮታ ቀበሌ ያሉ የእርሻ ማሳዎች ጦርነት እየተካሄደባቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የግብርና መምሪያ ኃላፊ አዲሱ፣ በዞኑ በሰብል ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ደርሷል ብለው በሄክታር ለማወቅ ጥናት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። አክለውም፣ በዘር ያልተሸፈኑ መሬቶችና የቡቃያ ጉዳት የደረሰባቸው ወረዳዎች ቁጥራቸው ሊጨምር ይችላል ነው ያሉት።

በብሔረሰቡ አስተዳደር ከ120 ሄክታር በላይ ለእርሻ አገልግሎት የሚውል መሬት መኖሩና 90 ሄክታር የሚሆነው በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል። በጦርነቱ በርካታ እንስሳት መገደላቸው ሌላኛው በግብርናው ዘርፍ የተከሰተው ችግር መሆኑ ተነስቷል።

አዲሱ እንዳሉት ከሆነ፤ የእርሻ በሬዎችን ጨምሮ ዶሮዎች፣ ፍየሎችና ገና በቁጥር ያልታወቁ በርካታ እንስሳት ተገድለዋል። አንድ በሬ ከ60 ሺሕ ብር በላይ በሚገዛበት ወቅት አርሶ አደሮች ሦስትና አራት በሬዎቻቸውን አጥተዋል ያሉት አዲሱ፤ ለመተካት አቅም ስለማይኖር በግብርናው ዘርፍ ከባድ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል ብለዋል።

በዞኑ ከአንድ ቤት እስከ 10 የቤተሰብ አባላት በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውና በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውም ተጠቅሷል።

ዞኑ ከ2013 ሐምሌ ወር ጀምሮ በጦርነት ቀጠና ነው የተባለ ሲሆን፤ መንግሥት እና ሌሎች በጎ አድራጊዎች የበኩላቸውን እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ ተላልፏል።

በጦርነት ቀጠና ውስጥ በሆነው በአማራ ክልል ደጋማውና ቆላማው ክፍል ያለውን ኹኔታ ማጣራት አልተቻለም። በኦሮሚያ ክልል ወለጋ የተለያዩ ዞኖች ግን በሄክታር ለመግለጽ ቁጥሩ ባይታወቅም ሰፊ የእርሻ መሬት በዘር አለመሸፈኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here