የሴቶች ሰውነት ጦር ሜዳ አይደለም!

0
689

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በደኅና አደረሳችሁ/አደረሰን!

ባሳለፍነው ሳምንት የ2014 መጨረሻ ወይም ጷጉሜ 3/2014 ላይ አንድ የሰላም የእግር ጉዞ ተካሂዷል። ይህም በትምራን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የተዘጋጀ ነበር። ‹ሴቶች ሰላምን ይሻሉ፤ ሴቷ ሰላምን ትምራ› የሚል መሪ ሐሳብ በያዘው በዚህ የእግር ጉዞ ላይ፣ በርካታ መፈክሮች ተይዘው ተመልክተናል።

ከመፈክሮቹ መካከል አንደኛው በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ላይ የተመለከተው ‹የሴቶች ሰውነት ጦር ሜዳ አይደለም!› የሚለው ይገኝበታል። ይህ መፈክር ወይም መልዕክት በተለየ ሁኔታ በማኅበራዊ ገጽ ላይ ሲንሸራሸር አስተዋልኩኝ። ‹ይሄ መፈክር ምን ማለት ነው?› የሚሉ ጥያቄዎችም ተያይዘው ብዙ አስተያየት ሲሰጥባቸው ታዝቤአለሁ።

ጥያቄው ነገሩን ተመልካች በሚገባ እንዲረዳውና ትኩረት እንዲያገኝ፣ የሰዎች አስተያየትም ምን እንደሆነ ለመረዳት የወጣ ሊሆን ይችላል። ያ እንዳለ ሆኖ ግን ከጥያቄው ስር የተሰጡ ምላሾችና አስተያየቶች (Comment) በጣም አሳፋሪና የሚያበሳጩ ነበሩ።

ጉዳዩን ቀልድ ያደረጉት ይበዛሉ። በርካቶቹም ዋልጌ የሆኑ የስድብ ቃላትን ጽፈዋል። ይህ የተመለደ ጉዳይ ሳይሆን አልቀረም! ግን በሁሉ ነገር አላግጦና አፊዞ እስከመቼ ነው? ለማንኛውም ግን መፈክሩ ምን ማለት ነው ለሚለው በገባኝና በተረዳሁት መጠን አንድ ነገር ማለትን ወድጄ ነው ወደዚህ የመጣሁት።

ጦርነት የራሱ ሕግ አለው። ምንም እንኳ ኹለት ወገኖች እርስ በእርስ በመገዳደል አንዳቸው አሸናፊ ለመሆን የሚያደርጉት ትግል ቢሆንም፣ ሕግ ግን ተሠርቶለታል። ይህም ብዙውን ጊዜ በቀደሙ ጦርነቶች የታዩ ክስተቶችን መነሻ ያደረገ ነው። በዚህም ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት በዓለም ፍርድ ቤት ቆመው ሲከሰሱም ተመልክተናል።

ለምሳሌ ረሀብን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም አንደኛው የሚከለከል ጉዳይ ነው። ልክ እንደዛው ሁሉ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ይጠቀሳል። አንዱ ወገን የሌላኛው ወገን ናቸው ያላቸው ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳትን ያደርሳል። በዚህም የማኅበረሰብን ሥነልቦና በመስበር፣ እንዲሸማቀቁና እንዲያፍሩ ብሎም እንዲገለሉ በማድረግ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል።

የተጠቀሰው መፈክር መልዕክትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ሴቶችንና የሴቶችን ሰውነት እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀምን ያወግዛል። የሴቶች ሰውነት የጠላቶች መፋለሚያ አውድ እንዳልሆነም ይናገራል። የሴቶች አካል ኹለት ጠበኞች ‹የእኛ ወገን የሆኑ ሴቶች ላይ ጥቃት ደርሷል፤ የእናንተ ወገን የሆኑ ሴቶች ላይ እኛም ጥቃት እናደርሳለን› ብለው የሚዛዛቱበትም እንዳልሆነም ያሳስባል። እናም ይህ መፈክር ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሊስተጋባ የሚገባ ትልቅ መልዕክት ነው።

መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here