መነሻ ገጽሕይወት እና ጥበብነገረ ጤናየአየር ንብረት መዛባት ቀጣይነት

የአየር ንብረት መዛባት ቀጣይነት

ዓለማችን እየሞቀች የአየር ንብረቷም እየተቀያየረ ስለመምጣቱ የዘርፉ ተመራማሪዎች ሲናገሩ ማድመጥ እየተለመደ መጥቷል። የሰው ልጅ ተግባር ለለውጡ ቀጥተኛ ምክንያት ነው አይደለም የሚሉ ሙግቶች ቆመው፣ በአብዛኛው የመቀየሩ መንስኤ የእኛው የሰው ልጆች ተግባር ነው ብለው ወደመስማማቱ ተጠግተዋል። ተግባራችንን አስተካክለን የዓለማችን አየር ወደነበረበት እንዲመለስ እንሥራ ለሚለው የብዙዎች ጥሪ የኢኮኖሚ እድገትን እንደማስተባበያ አድርገው አሻፈረን የሚሉም ሞልተዋል።

የአየር ንብረት ላይመለስ ተቀይሯል ብለው የሚሞግቱ በርካቶች ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ በየተወሰነ ዘመኑ የሚሽከረከር ዑደት ነው ብለው አሳሳቢነቱን ለመቀነስ ይጥራሉ። ሆኖም አሁን አሁን የለውጡ መታያ ክስተቶች እየተለመዱ ለውጥ ለማለትም እያስቸገሩ መሆናቸውን መመልከት ይቻላል።

ከፍተኛ የሆነ ሙቀት፤ ታይቶ የማይታወቅ ጎርፍና መጥለቅለቅ፤ አውሎ ንፋስ የቀላቀለ ውሽንፍር፤ ታላላቅ ወንዞችን ያደረቀ ከፍተኛ ድርቅ፤ ረሃብን የሚያስከትል ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የዝናብ መጥፋት፤ ሰደድ እሳትና የመሬት መንሸራተት እንዲሁም የአየር ብክለት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተው አሁን አሁን ማስደንገጣቸውንም ቀንሰዋል።

ሠሞኑን በአውሮፓና በአሜሪካ እንዲሁም በመላዋ ቻይና የታየው ከፍተኛ ሙቀት የምግብ አቅርቦትን እጅግ ከመቀነሱ ባሻገር፣ በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማምጣቱ ይቀጥላል ተብሎ ተገምቷል። በሳውዲ አረቢያና በረሃማ በሆኑ ሌሎች አገሮች ታይቶ የማይታወቅ ጎርፍና የበረሃ ወንዞች መታየታቸው እንዲሁም ፓኪስታንና ዱባይ የታየው አስፈሪ ጎርፍ ለለውጡ መደጋገም ተጠቃሽ ክስተቶች ናቸው።

እነዚህ ለውጦች ካስከተሉት ችግር በተጨማሪ፣ ለወደፊቱ እየቀነሱ ይሄዳሉ ሲባል እየጨመሩ እንደሚሄዱ የሚጠቁም መረጃ ይፋ መሆኑም ብዙዎችን እያሳሰበ ይገኛል። ከ20 ዓመታት በኋላ በእጥፍ ያህል ለውጥ ሊከሰት ይችላል። በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ ደግሞ ለከፍተኛ የጤና እክልና ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሚሆን ለውጥ ሊከሰት እንደሚችል ተመራማሪዎች መጠቆማቸውን አይ.ኤፍ.ኤል. ሳይንስ አስነብቧል።

እንደተመራማሪዎቹ ከሆነ በተለይ የምድር ወገብ አካባቢ ባሉ በአፍሪካና አሜሪካ አካባቢዎች ለመኖር አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ የአየር ንብረት ለውጡ ችግር ላይ ሊዳርግ እንደሚችል ነው። የአኗኗር መንገዳችን ላይ ለውጥ ቢደረግ እንኳን ችግሩ ይጨምራል እንጂ አይቀንስም የተባለ ሲሆን፣ እጅግ ሞቃት ቀኖች ከታመቀ አየር ጋር ሆኖ በሙቀት ሳቢያ ሰውነታችን እንዲዝለፈለፍ ያደርጋል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

መጪውን ለመገመት አስችሎናል ያሉት የሕዝብ ቁጥር የመጨመር ሂደትን፣ የኢኮኖሚ እድገት አቅጣጫንና የአገራት የኃይል አማራጭ ምርጫቸውን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ጥናት የሚጠቁመውን የለውጥ አካሄድ ከግምት በማስገባት እንደሆነ አሳውቀዋል። የአሜሪካው ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎቹ እንዳሉት፣ እጅግ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በቀጥታ ባይገድልም፣ በእለት ተእለት ኑሮ ውስጥ ኅብረተሰቡን ለጭንቀትና ማቅለሽለሽ ዓይነት ሕመሞች በመዳረግ ራስን ስተው እንዲወድቁ ያደርጋል ይላሉ።

ይህ የሰውነታችን ሙቀትን ከተለመደው 37 ዲግሪ በትንሹ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ ወደ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ የሚያደርሰው ከሆነ በቶሎ ሐኪም ዘንድ ተገኝቶ የሰውነት ሙቀት እንዲቀንስ ማድረግ ካልተቻለ ለሞት ሊዳርግ ይችላል ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ አሁን የሰው ልጆች እየሄዱበት ያለው የእድገት መስመር ከተስተካከለ የኃይል ምንጫቸውንም ሆነ ዓለምን የመበከላቸው መጠን ሊቀንሱ ይችላሉ። ሆኖም በካይ ጋዝን መልቀቃቸውን ግን ሙሉ በሙሉ ማቆም እንደማይችሉ ኤን.ቲ.ዲ. ድረ ገፅ አስነብቧል። ወደታዳሽ የኃይል ምንጮች ሙሉ በሙሉ መቀየር አይቻልም የተባለው ከተለያየ አቅጣጫ ታይቶ ሲሆን፣ ለወደፊት አይቀርም ለተባለው የአየር መዛባትም ሆነ ለብክለት መጠን መጨመር አጋዥ ማስረጃ መሆኑ ተነግሯል።

አገራትም ሆኑ ትልልቅ ኩባንያዎች አየርን ከመበከል ሙሉ በሙሉ መቆጠብ ባለመቻላቸው ሂደቱ እየተወሳሰበ ችግሩም ሆነ የሚከተለው አደጋ እንደሚጨምር እሙን ነው። የዓለማችን ሙቀት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ግግር በረዶ የሚቀልጥበት መጠን ስለሚጨምር ለውቅያኖስ ከፍታ መጨመር መንስኤ እንደሚሆን መነገር ከጀመረ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ተገምቶ ከነበረው ፍጥነት እጅግ በከፋ መጠን እየተፋጠነ እንደሆነ ተመራማሪዎች እየተናገሩ ነው።

ከሰሞኑ የአይስላድ የበረዶ ግግር እጅግ በፍጥነት እየቀለጠ መሆኑን የአገሪቱ ተመራማሪዎች ይፋ አድርገዋል። በየዓመቱ ከሚጨምረው የመቅለጥ መጠን የዘንድሮው እጅግ የተጋነነ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ይህ የየአገራት ማስረጃ ለለውጡ መፋጠን እንደማስረጃ የሚቆጠር ሲሆን፣ አውስትራሊያን የመሳሰሉ አገራትም የየራሳቸውን የለውጥ ማስረጃ ይፋ በማድረግ አስገዳጅ ሕጎች ግድ የሚሉበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ለማስገንዘብ እየጣሩ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል፣ የአየር ንብረት ለውጡ ከዓለማችን ብክለት መጠን ጋር መሳ ለመሳ እያደገ መምጣቱ አሳሳቢ እንደሆነ መነገሩን ሳይንስ አለርት አስነብቧል። ከፍተኛ ሙቀት ከሚያስከትለው ችግር በተጓዳኝ የአየር ብክለቱ መጨመር ሂደቱን የበለጠ በማፋጠን የሚያስከትለውን መዘዝ ያብሰዋል ይላሉ። ወደ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞች መጠናቸው እያደር በመጨመሩ አልፎ አልፎ ይመዘገብ የነበረው የተበከለ የአየር መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዘወተረ መጥቷል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

የዓለም ጤና ድርጀት የሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች በፊት በፊት ቻይናና ሕንድ በመሳሰሉ አገራት ብቻ ይስተዋሉ እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፣ አሁን አሁን በአገራቱ ከመለመዳቸው ባሻገር በሌሎች በማደግ ላይ ባሉ አገራትም እየተከሰተ መሆኑ ሊያሳስብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እጅግ ከፍተኛ ሙቀት ሰደድ እሳት እንዲከሰትና ያንንም ለማጥፋት አስቸጋሪ ከማድረጉ ባሻገር፣ ከአየር መበከል ጋር አንድ ላይ በሚከሰትበት ወቅት ጤና ላይ ከፍተኛ እክል ይፈጥራል። በተለይ በአዛውንቶች ላይ አስቸጋሪ ሁኔታን እንደሚፈጥር የተነገረ ሲሆን፣ ለወጣቶችም ቢሆን መጥፎ እንደሚሆንና የጤና እክል ላለባቸው ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ እንደሚሆን ተጠቁሟል። በፊት በፊት ከፍተኛ ወበቅ ያለው የሙቀት መጠን ለአጭር ጊዜ ቆይቶ የሚጠፋ የነበረ ሲሆን፣ አሁን አሁን ግን ለተከታታይ ቀናት የሚቆይ በመሆኑ መዘዙ ከፍተኛ ነው ተብሏል።

ከ2014 ጀምሮ በነበሩት ስድስት ዓመታት ውስጥ በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት የተከሰቱ ሞቶችን በመገምገም ተመራማሪዎች ይፋ ያደረጉት ግኝት አለ። እንደጥናታቸው ውጤት ከሆነ ከፍተኛ ሙቀት በተከሰተባቸውና ሰደድ እሳትን የመሳሰሉ አባባሽ ክስተቶች በግዛቲቱ በሚስተዋሉበት ወቅት የሞት መጠን ይጨምራል።

የአየር ብክለቱ ከሙቀቱ ጋር ተደምሮ ከፍተኛ በሚሆንበት ወቅትም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሟቾች ቁጥር መመዝገቡን በማረጋገጥ፣ ለሞት መጠን መጨመሩ ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ለማወቅ መቻላቸውን ይፋ አድርገዋል። ኹለቱም ማለትም የሙቀት መጠንና ብክለቱ ከፍተኛ በነበረባቸው ቀናት የሟቾች ቁጥር እስከ ሦስት እጥፍ ጨምሮ እንደነበር አሳውቀዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ለወደፊቱ መሻሻል እንደማያሳይ የተነበዩ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፣ በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ እስከ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን ሊጨምር እንደሚችል ነው። አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ከፍተኛ የሙቀት ወላፈኖችም ተደጋጋሚ ሆነው የተለመደ ሥርዓት እንደሚሆንም ገምተዋል።

ከዚህ ቀደም የሚገመቱ መላምቶች ሙሉ በሙሉ ውድቅ ባይደረጉም፣ የዓለም ሙቀት መጠንም ሆነ ብክለት ከቀደመው ትንበያ እጅግ በፈጠነ ሁኔታ መጨመሩ ታውቋል። ይህ የጭማሬው ፍጥነት እያደገ እንደሚሄድ የሚናገሩት ተመራማሪዎች፣ የሰው ልጅ ከተለመደው የበካይ እንቅስቃሴው በተቻለ መጠንና ፍጥነት መቆጠብ ከቻለ የጉዳት መጠኑንም ሆነ እየተባባሰ የሚሄድበትን ፍጥነት መቀነስ እንደሚቻል ይናገራሉ። ሙሉ በሙሉ የአኗኗር ዘይቤያችንን መቀየር ባንችልም፣ ቢያንስ ከለውጡ ጋር የሚመጡ ክስተቶችን መቋቋም የምንችልባቸው ዝግጅቶች አስቀድመው እንዲታሰብባቸው ይመክራሉ።

መንግሥታትም ሆኑ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትና ትልልቅ ኩባንያዎች ለውጡን ለመቀነስም ሆነ ብዙ ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ አብሮ ለመጓዝ የሚያስችል አማራጭ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተነግሯል። ኅብረተሰቡ በበኩሉ፣ ቁጭ ብሎ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣ ጉዳትን በፀጋ ከሚቀበል የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል ተብሏል። ቢያንስ ቢያንስ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የከፍተኛ ሙቀት ወበቆችንም ሆኑ ሌሎች ተያያዥ የተፈጥሮ አደጋዎችን ተቋቁሞ ሕይወቱን መግፋት የሚችልባቸው መንገዶች ላይ በማተኮር ራሱን ቢያዘጋጅ መልካም ነው ሲሉ የዘርፉ ምሁራን አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች