በጦርነት የተሰቀለች ሠላም!

0
1086

ኢትዮጵያ የሰላም ያለህ እያለች፤ ሕዝቧም ሰላም ከሁሉ እንደሚበልጥ ዐይቻለሁ ብሎ ደጋግሞ እየመሰከረ ይገኛል። ነገር ግን በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተነሳው ጦርነት እንዲሁም በየአካባቢው ያሉ አለመረጋጋቶች ጋብ አላሉም።
አልፎ አልፎ የሚሰሙ የነበሩ የሰላም ድርድሮችና የተኩስ አቁም ጉዳዮችም፣ ከአንድ ሰሞን እና ከአንድ ወገን ጥረት ያለፉ ሆነው አልታዩም። ይህም ኢትዮጵያን ትልቅ ዋጋ እያስከፈለ ሲሆን፣ በጉጉት እየተጠበቀች ያለችውን ሰላምም እንደሻከረች የሚያቆያት እንዳይሆን ብዙዎች ስጋታቸውን ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ከገጠማት ኹለት ዓመት ልታስቆጥር የአንድ ወር እድሜ ቀርቷታል። ይኸው የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረበት ጥቅምት 24/2013 እስከ አሁን ድረስ በተለዋዋጭ ክስተቶች ታጅቦ ለሦስተኛ ጊዜ ተቅስቅሷል።

በአንድ በኩል የፌዴራል መንግሥት፣ የአማራና አፋር ክልሎች በሌላ በኩል በሕወሓት መካከል የሚደረገው ጦርነት ለሦስተኛ ጊዜ የተቀሰቀሰው ነሐሴ 17/2014 ነው። ይህም እንደ ቀደመው ሁሉ በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልሎች በዜጎች ላይ ከሞት እስከ አካል ጉዳት፣ ከመፈናቀል እስከ ንብረት ውድመት የሚደርስ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተሰምቷል።

ሦስተኛው ዙር ጦርነት ከወራት ጋብታ በኋላ የተቀሰቀሰው ገና ጦርነቱ ሳይጀመር በተለያዩ አካላት ሲሞከር የነበረው የሰላም ጥረት ከመሻት የዘለለ በተጨባጭ ውጤት ማሳየት ሳይችል ቆይቶ፣ የፌዴራል መንግሥት  ጦርነቱን በሰላም ለመፍታት ከሕወሓት ጋር ለመደራደር በወሰነበት ማግስት ነው።

ከአፍሪካ ኅብረት እስከ ተባበሩት መንግሥታት፣ ከጎረቤት አገራት እስከ አሜሪካ የፌዴራል መንግሥቱን እና ሕወሓትን ለማደራደር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ይህም ጥረት በተለይ መንግሥት ለድርድር ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ጦርነቱ በሰላም የመፍታቱ ጉዳይ ከዚህ ቀደሙ የተሻለ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ለመደራደርና ጦርነቱን በሰላማዊ ሁኔታ ለመቋጨት ፍላጎት እንዳለው ቢገልጽም፣ ከሕወሓት በኩል ከድርድር ይልቅ ጦርነቱ በኃይል የበላይነት የመቋጨት ዝንባሌ ይንጸባረቅ ነበር። ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ሕወሓት በአፍሪካ ጥላ ስር ለሚደረግ ድርድር ዝግጁ መሆኑን ማሳወቁን ተከትሎ፣ የጦርነት ዝግጅቶች በኹለቱም ኃይሎች በኩል ቢኖሩም፣ የሰላም ጉዳይ ከመሻል ከፍ ብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

ነገር ግን በዚህም ጦርነቱን ዳግም ከመቀስቀስ ማስቆም አልተቻለም። ሦስተኛው ዙር ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በሕወሓት በኩል ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን መስከረም 1/2014 ባወጣው መግለጫ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ሕወሓት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚካሄድ የሠላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑንና በዚህም የሚሳተፉ ተወካዮችን መሰየሙን ይፋ ቢያደርግም፣ በተደጋጋሚ ግጭቱ ለማስቆም በድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን ሲገልጽ የነበረው የፌዴራል መንግሥት የሰጠው ግልጽ ምላሽ የለም።

ሕወሓት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለሚደረገው ድርድር አመቺ ሁኔታን ለመፍጠርም አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ድርድር እንዲጀመር መስማማቱን በይፋ ካሳወቀ በኋላ፣ የሕወሓትን ውሳኔ አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ ድርድር እንዲደረግ ጥረት የሚያደርጉ አካላት በአዎንታዊነት ተቀብለውታል። ሕወሓት ከዚህ ቀደም ለድርድር አመቺ ያልሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ በድርድር ጥረቱ ላይ ጥቁር ጥላ አጥልቷል ተብሎ ነበር።

ምኞት ብቻ አይበቃም!

የጦርነቱ ዋና ተዋንያን የሆኑትን የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓትን ለማደራደር ጥረት በማድረግ ላይ የነበሩ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞች የኹለቱን ኃይሎች የሰላም ፍላጎት ማሳየት አድንቀው ሳይጨርሱ ለሦስተኛ ጊዜ የተጀመረው ጦርነት ኢትዮጵያ አጥብቃ የምትሻትን ሰላም እየገፋ እንዳይሆን ብዙዎች ይሰጋሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ እና አስተዳደር ጥናቶች ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የሰላምና ደኅንነት ላይ ጥናቶችን የሚሠሩ መምህር በጉዳዩ ዙሪያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ አድርገዋል። በዚህም ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የገጠማት ጦርነት በተደጋጋሚ ማገርሸትና ለሰላም ዕድል አለመሰጠቱ የጦርነቱን በሰላማዊ ሁኔታ እልባት የማግኘት እድሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠበበው እንደሆነ ይሰማኛል ይላሉ።

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ጦርነቱ ሄድ መጣ እያለ፣ እድሜው በተራዘመ ቁጥር የሚያስከትለው ችግር ከተባባሰና ጊዜው እየረዘመ ከሄደ፣ አሁን ለሰላም የጠፋው ዕድል ወደፊትም የመጥፋት እድሉ ሰፊ መሆኑን በመጥቀስ ነው።

‹‹ሰላም በምኞት ብቻ አይመጣም፤ ዋጋ ያስከፍላል›› የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ፤ የኢትዮጵያን ሰላም ለመመለስ ከራሳቸው ወይም የእኔ ከሚሉት ቡድን ጥቅምና ፍላጎት በላይ ለአገርና ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች ጎልተው መውጣት አለባቸው ይላሉ።

በተለያየ ጎራ ቆመው የአንድ አገር ሕዝብ እንደ ባዕድ እንዲተያይና አስከፊ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ያስገደዱት የሕወሓትና የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት መሆናቸውን የሚገልጹት መምህሩ፣ ኹለቱ ኃይሎች ከእልህ ፖለቲካ ወጥተው አገርን ማሰብ አለባቸው ይላሉ።

የሰላም ዥዋዥዌ

ሰላም የሰው ልጆች ሁሉ በእድሜ ዘመናቸው የሚሹት፣ ሊያገኙትም የሚገባ የሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ የመኖር መሠረት ነው። ዓለም ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት ነው የሚለውን መርህ ታስተጋባለች፣ ነገር ግን ሰላምን ከመሻት የዘለለ መኖር የተሳናቸውና ዛሬም በጦርነት ውሰጥ የሚገኙ አገራት በቁጥር ቀላል አይደሉም።

ኢትዮጵያም ሰላም ፈልገው ሰላም ካጡቱና የእርስ በእርስ ጦርነት ከገጠማቸው አገራት መካከል አንዷ  ከሆነች ኹለት ዓመት ልታስቆጥር አንድ ወር ቀርቷታል። በሰሜኑ ክፍል የተከሰተው ጦርነት ከመቀስቀሱ አስቀድሞ በነበሩ የቃላት ጦርነቶች እና መገፋፋቶችን በመነጋገር ማስቀረት ሳይቻል ቀርቶ ኹለት ዓመት ገደማ ኪሳራ ካስከተለም በኋላ እንደቀጠለ ነው።

የሰሜኑ ጦርነት ገና ከመጀመሩ በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት መካከል የነበረው የቃላት ጦርነት ገኖ ለጦርነት መቀስቀስ ምክንያት እስከሆነበት ዕለት ድረስ፣ በኹለቱ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በሰላም ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች ኹለቱን ኃይሎች ለማቀራረብ ጥረት አድርገው ሳይሳካለቸው ቀርቷል።

በወቅቱ የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሓት የቃላት ጦርነት እየተባባሰ በመምጣቱ በአገር ላይ ስጋት መደቀኑን የተገነዘቡ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ ዝም አላሉም ነበር። ይልቁንም ልዩነቱን ለማጥበብ እና ኹለቱ አካላት ተቀራርበው ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ለማስቻል ሰኔ 9/2012 ከሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው ነበር። የአገር ሽማግሌዎቹ በራሳቸው ፈቃድ ለአገር በማሰብ በቀናነት ለማቀራረብ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

የአገር ሽማግሌዎቹ የመቀሌ ጉዞ ዋና ዓላማ በትግራይ ክልል መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ማጥበብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር ነበር። በወቅቱ የአገር ሽማግሌዎቹ በኹለቱ አካላት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ እና ልዩነታቸውን በንግግር እንዲፈቱ የሄዱበት መንገድ ውጤታማ አልነበረም።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ደግሞ ጦርነቱ በሰላማዊ ድርድር እንዲቋጭ የተለያዩ አካላት ገና ከጅምሩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ነበር። በተለይ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለማመቻቸት የጦርነቱ ተፋላሚ ኃይሎችን በተደጋጋሚ በተናጠል ለማነጋገር ከአዲስ አበባ መቀሌ በተደጋጋሚ ተመላልሰዋል።

ኦባሳንጆ ከመቀሌ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ በኹለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በኩል ተጨባጭ ለውጥ አለመታየቱን ተከትሎ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሔ ሳይገኝለት ከሦስት ሳምንት በፊት ዳግም ለሦስት ጊዜ ተቀስቅሷል።

በፌዴራል መንግሥት እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ፣ የተቀሰቀሰው የሰሜኑ ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ሳይስፋፋ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ አካላት እንደነበሩ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ፣ ጦርነቱ ወደ ኹለቱ ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ ትግራይን ጨምሮ በሦስቱ ክልሎች ያደረሰው ሰብዓዊ እንዲሁም ቁሳዊ ኪሳራ ክልሎቹንም ሆነ ኢትዮጵያን እንደ አገር ወደ ኋላ የሚጎትት ሆኗል።

ኢትዮጵያ ከገጠማት ጦርነትና ኪሳራ እንድትወጣ የተለያዩ አካላት ከሚያደርጉት ጥረት በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን በግልጽ ይፋ ካደረገ በኋላ ተደራዳሪ ኮሚቴ አዋቅሮ ሥራ መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ይሁን እንጂ ሰላም መሻት እንጂ ሰላምን መፍጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠር ጦርነት መቀስቀሱ የሰላምን እድል የሚያደናቅፍ መሆኑን ለማደራደር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አካላት እየገለጹ ነው።

ከፌዴራል መንግሥት የድርድር ዝግጁነት በኋላ የመጣውን የሕወሓትን የተኩስ አቁምና የድርድር ስምምነት የአፍሪቃ ኅብረት፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዩናይትድ ስቴትስ ደግፈዉታል። ይሁን እንጂ ኹለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በየፊናቸው በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ድርድር ለማድረግና ጦርነቱን በሰላም ለመፍታት ፈቃደኛ ከመሆናቸው የዘለለ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስና ጦርነቱን ማቆም አልቻሉም።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ጦርነቱን በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት በመንግሥትና በሕወሓት በኩል የተሰሙ የድርድር ፍላጎቶች፣ እውን ይሆናሉ ተብሎ ተስፋ ቢጣልባቸውም ገና ከጅምሩ ዳግም ወደ ጦርነት መመለሳቸው አሳሳቢ ነው ይላሉ። ሰላም እየፈለጉ ወደ ጦርነት መግባት ትክክለኛ ሰላምን የሚፈልግ አካል መገለጫ አይደለም የሚሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያ ከጦርነት ወጥታ ሰላም እንድትሆን ለሰላም ዋጋ ከፍሎ ወደ ልባዊ የሆነ ንግግር መቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያን ሰላም ለመመለስ ከሚከፈለው ዋጋ በላይ በጦርነት የሚደርሰው ኪሳራ የከፋ ነው የሚሉት መምህሩ፣ ሄዶ ሄዶ መቋጫው ድርድር ለሆነ ጦርነት የሰው ልጅ ሕይወት ባይጠፋና ተጨማሪ አራራቂ ቂም ከሚፈጠር ጦርነቱ የሚቆምበትን ሁኔታ ማመቻቸው አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ። በጦርነቱ ገፈት እየቀመሰ የሚገኘው ሕዝብ ዋነኛ የሰላም ተዋናይ ነው የሚሉት መምህሩ፣ ጦርነቱን በቃ የሚልበት እድል አላገኘም የሚል ሐሳብ አላቸው። ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተፈላሚ ኃይሎች የሕዝብንና የአገርን ጥቅም አገናዝበው መነጋገርና ሰላም መፍጠር እንደ አገር የሚበጅ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሰላም ተዋንያን ብዙ ናቸው የሚሉት መምሀሩ፣ መንግሥትና ሕወሓት ብቻቸውን ሰላም ይፈጥራሉ ብሎ ከመጠበቅ፣ ባለድርሻ አካላትና ሕዝቡ በጫና ውስጥ አልፎም ቢሆን ለሰላም ዋጋ ከፍሎ ጦርነቱ እንዲቆም ግፊት በማድረግ ተፋላሚ ኃይሎች ሕዝቡን እንዲያደምጡ ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ውስብስብ መሆኑን የሚገልጹት መምህሩ፣ በዚያው ልክ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በንግግር ለመፍታት ጥረት ካልተደረገ በየአቅጣጫው መገዳደል መቋጫ የሌለው ኪሳራ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ያሳየውን ፍላጎት ተከትሎ ሕወሓትም ለመደራደር ፈቃደኛ መሆኑን ቢገልጽም፣ ኹለቱም ኃይሎች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ከመግለጽ ያለፈ ተጨባጭ አቀራራቢ እርምጃዎች አለመውሰዳቸው ሰላም ለመፍጠር የተማመኑ አይመስሉም ይላሉ መምህሩ። ለሰላም በትክክለኛ ዝግጁ አለመሆናቸው የሚረጋገጠው ለድርድር ዝግጁ ነን እያሉ ለሰላም ዕድል በመስጠት ፋንታ ወደ ጦርነት መግባታቸውን መምህሩ ያነሳሉ።

ለሰላም መተማመን

የኢትዮጵያ መንግሥትንና ሕወሓትን ወደ ድርድር ለማምጣት ቀደም ካለው የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ ጥረት በተጨማሪ፣ የተለያዩ የአሜሪካና አውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኞች እንዲሁም የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች የጀመሩትና ያደረጉት ጥረት አለ። በዛም ላይ ኹለቱ ኃይሎች ላይ የመተማመን ችግር መመልከታቸውንና አለመተማመን ተቀራርቦ ለመነጋጋር ማነቆ ሆኖ መቆየቱን እንደታዘቡ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ኹለቱ ኃይሎች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ፣ የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ፣ የተባበሩት መንግሥታትና የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች የድርድር ጥረቱን ለማገዝ የፌዴራልና የሕወሓትን ባለሥልጣናት በተናጠል አወያይተው ነበር። ልዩ መልዕክተኞቹ የሕወሓትና ፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትን በተናጠል ካወያዩ በኋላ ስለ ድርድሩ ያላቸውን ግንዛቤ ሲገልጹ በኹለቱ ኃይሎች መካከል አለመተማመን እንዳለ ጠቁመው ነበር።

ሕወሓትና የኢትዮጵያ መንግሥት የሰሜኑን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን በየፊናቸው ቢገልጹም፣ እርስ በእርሳቸው የመተማመንና እርስ በእርስ ከመፈራረጅና የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ከመወራወር የዘለለ አካሄድ እያሳዩ አልታዩም። ይህም በድርድር ጥረቱ ላይ ጥላ እንደሚያጠላ ለማደራደር ጥረት ከሚደርጉ አካላት መሰማቱ፤ ተፋላሚ ኃይሎች ለሰላም ዋጋ ለመክፍል ቁርጠኛ አለመሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑን የሰላምና ደኅንነት አጥኚ መምህሩ ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት መካከል የሰፈነው አለመተማመን ለሰላም ድርድሩ ዋናው እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን፣ ኹለቱን ኃይሎች ለማቀራረብ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ልዩ መልዕክተኛ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። አለመተማመኑ ከኹለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በተጨማሪ፣ በኹለቱም ኃይሎች በኩል ለማደራደር ጥረት የሚያደርጉ አካላት ላይ እምነት የማጣት ሁኔታ ይታያል።

ሕወሓት ቀደም ብለው የድርድር ጥረት በጀመሩት የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ አለኝ ሲል፣ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ በልዩ መልዕክተኞች ላይ እምነት እንደሌለው የሚያመላክት መረጃ በየፊናቸው አውጥተው ነበር።

በኹለቱ ኃይሎች መከካል የተፈጠረው አለመተማመን ለሰላም እንቅፋት መሆኑን የተገነዘቡ አካላት ኹለቱ ኃይሎች መተማመን ላይ የተመሠረተ ድርድር እንዲጀምሩ እየጠየቁ ነው። ኢጋድ በጉዳዩ ላይ ከሰሞኑ በሰጠው አስተያየት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት የሚያስችል መተማመን እንዲፈጥሩ ጠይቋል።

ሕወሓትና የኢትዮጵያ መንግሥት እርስ በእርሳቸው የሚወራወሩት የጥላቻና የፕሮፖጋንዳ ሽኩቻ ካልተገታ ለድርድሩ እንቅፋት እንደሚሆን የጠቆሙት ልዩ መልዕክተኛዋ፣ ኹለቱ ኃይሎች ከጥላቻና ከፕሮፓጋንዳ ሽኩቻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የሕወሓት ባለሥልጣናት አንዱ በአንዱ ላይ የሚወራወሩት የጥላቻ ንግግር ከጦርነቱ መጀመር አስቀድሞ እስካሁን የዘለቀ ሲሆን፣ አሁንም ለድርድር ዝግጁ ነን በሚሉበት ጊዜ እንኳን የጥላቻ ንግግርና ለፕሮፖጋንዳ መወራረፋቸውን አላቆሙም።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here