ሕጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከዓለም ዐቀፍ ድንጋጌዎች ጋር በጥብቅ የሚጣላ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ ሕጻናት በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ተሳታፊ ስለመሆናቸው ተደጋግሞ እየተሰማ ነው።
ሥሜ ከመጠቀስ ይቆይ ያሉ የመከላከያ ሠራዊት አባል ከዚህ በፊት በነበረው ጦርነትም ሕጻናት ለመዋጋት ተገደው እንደነበር አስታውሰው፤ ‹‹ሕወሓት አሁንም ቢሆን ዳግም በቀሰቀሰው ጦርነት ሕጻናትን ከፊት እያሰለፈ ነው›› ብለዋል።
በ2013 የክረምት ወቅት በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት ቡድን መካከል በተከሰተውና በድርድር ይፈታል ተብሎ በነበረው ጦርነት በተለያዩ ግንባሮች ሕጻናት ተሰልፈው እንደነበር አይረሳም።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በጦርነቱ ሳቢያ 8 ሺሕ 419 ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው መጠፋፋታቸውን እና 7 ሺሕ 165 የሚሆኑት ሕጻናትም በትግራይ ክልል የነበሩ ስለመሆናቸው በሪፖርቱ ማሳወቁ ይታወሳል።
በአማራ ክልል በነበረው ጦርነት 6 ሺሕ 305 የሚሆኑ ሕጻናት ወላጆቻቸውን በሞት እንዳጡ አዲስ ማለዳ በወቅቱ ዘግባ ነበር። በአፋር ክልልም ቁጥራቸው በውል ማወቅ ባይቻልም ተመሳሳይ ክስተት ታይቷል።
የሕወሓት ታጣቂ ቡድን በትግራይ ክልል የሚገኝ ወላጅ/ቤተሰብ ‹በአንድ ቤት አንድ ልጅ ያዋጣል› የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፉን የተለያዩ የዜና ምንጮች መግለጻቸው ይታወሳል። ቡድኑ ለሦስተኛ ጊዜ በቀሰቀሰው ጦርነትም ሕጻናትን ወደ ግንባር በማሰለፍ የተለመደ ግብሩን እየፈጸመ ስለመሆኑ በግንባር የሚገኙ የዐይን እማኞች እየገለጹ ነው።
ሕጻናትን በጦርነት ግንባር ማሰለፍ ይቅርና ከባድ ሥራ ማሠራትም አግባብነት እንደሌለው የሕጻናት መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገልጻሉ።
‹ሴቭ ዘ ችልድረን› የተሰኘው የሕጻናት መብት ተሟጋች ድርጅት፣ በድረ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ በአፍሪካ ሕጻናትን ከሚጎዱ የተለያዩ ጎጂ ልማዶች አንዱ መሆኑን ይጠቅሳል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም በተጓዳኝ በአንቀጽ 36 ድንጋጌው ሕጻናት ጉልበታቸውን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅን ጨምሮ በርካታ መብቶች እንዳሏቸው አስቀምጧል።
የሕጻናቱ እናቶች፤ የሕግ ባለሙያዎች እንዲሁም የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው፣ የሕጻናት መብቶች እየተጣሱ በመሆናቸው ድርጊቱ በአስቸኳይ መወገዝ እንዳለበት በመግለጽ ላይ ናቸው።
የተጣሰው መብት
ኢትዮጵያ ከሕጻን እስከ አዋቂ ስላለው የሰው ልጅ በየፈርጁ ጥንቅቅ ብለው የተደነገጉ ሕጎች ባለቤት መሆኗን ሕጎቿን ያገላበጡ የሕግ ባለሙያች በተደጋጋሚ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የሰው ልጆችን መብት በየፈርጁ ጥንቅቅ አድርጋ የመደንገግ ችግር የለባትም የሚሉት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በማንኛውም ፍርድ ቤት የሕግ አማካሪና ጠበቃ ብርሃኑ አያሌው ናቸው።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36 ስር ተዘርዝረው የሚገኙ የሕጻናት መብቶችን ያነሱት የሕግ ባለሞያዎች፣ ከእነዚህም መካከል የተወሰኑትን በመጥቀስ አብራርተዋል። በዚህም መሠረት ሕጻናት በሕይወት የመኖር፤ ሥምና ዜግነት የማግኘት፤ ወላጆችን ወይም በሕግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅና የእነሱንም ክብካቤ የማግኘት፤ ጉልበትን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፤ በትምህርት፣ በጤናና በደኅንነት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠራ/ትሠራ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ፤ በትምህርት ቤቶች ወይም በሕጻናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካል ላይ ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔና ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ ቅጣት ነጻ የመሆን መብቶች እና ሌሎችም ናቸው ብለዋል አማካሪው።
ሕጻናት በጦርነት ግንባር እንዲሰለፉ ማስገደድ በሕይወት የመኖር ሙሉ መብታቸውን መጣስ እንደሆነም የሕግ አማካሪው ገልጸዋል።
ሕጻናት ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሥራ ያለመሥራት መብታቸው በሕገ መንግሥቱ ተቀምጧል ያሉት ብርሃኑ፤ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መሣሪያ አሸክሞ እንዲተኩሱ ማድረግ ይቅርና፣ ተቀጣጣይ ያልሆነ ነገርን ጉልበታቸው በማይፈቅደው መልኩ ማሸከም ራሱ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር ይጣላል ነው ያሉት።
ጦርነት በሚከሰትበት ወቅት ሕጻናትና ንጹሐን ሰዎች እንዳይጎዱ በተፋላሚ ቡድኖች ስምምነት የጦርነት ሜዳ ይመረጥ እንደነበር በተደጋጋሚ ይነገራል። የሕግ አማካሪው ብርሃኑ በበኩላቸው፣ በድሮ ጊዜ በነበረ ጦርነት ንጹሐን እና ሕጻናት እንዳይጎዱ ልዩ ትኩረት ይደረግ ነበር ይላሉ።
አያይዘውም፤ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት ቡድን መካከል በተፈጠረው ጦርነት ግን እንዲያውም ንጹሐን ሰዎችና ሕጻናት በጦርነቱ ተሳታፊ መሆናቸው እየታየ ነው ብለዋል።
‹‹ሕጻናት በጦርነት ግንባር ተሰልፈው መሣሪያ ሲተኩሱ ተቃራኒ ቡድን በበኩሉ መተኮሱ ላይቀር ይችላል። በመሆኑም፤ ሕጻናት በለጋነት እድሜያቸው ለዛውም በጦርነት ተሰልፈው በመሣሪያ ቢገደሉ፤ በሕይወት የመኖር መብታቸውን አሻፈረኝ ብሎ መጣስ ነውና በፍጥነት ሊወገዝ ይገባዋል›› በማለት አሳስበዋል።
ወላጆች እንዲሁም የፖለቲካ ተንታኞች በየበኩላቸው፣ ሳይገባቸው በጦርነቱ ሰለባ እየሆኑ ያሉ የሕጻናት ጉዳይ እየተደጋገመ መሆኑን አንስተው ሕገ መንግሥቱ የሚከበረው መቼ ነው የሚል ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡:
ዘንድሮም እንደ አምናው
እስከዛሬ በሕጻናት ላይ በስፋት ሲስተዋል የነበረው ችግር ያለ ዕድሜ ጋብቻ፤ የመማር እና የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት እድል አናሳ መሆን፤ የሴት ልጅ ግርዛት፤ እንጥል ማስቧጠጥ እና የመሳሰሉት እንደነበሩ ስለሕጻናት ተቆርቋሪው ሴቭ ዘ ችልድረን ይገልጻል። በሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የግል እንዲሁም መንግሥታዊ ተቋማትም፣ የሕጻናትና የሴቶች መብት ጥሰት በተመለከተ መሥራት እንደሚገባ በየጊዜው ሲያሳስብ ይደመጣል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም የዜጎች ሰብዓዊ መብት በአንድም በሌላም ምክንያት ገሸሽ ማለቱን በየወቅቱ የሚያወጣው መረጃ ያሳያል።
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከላይ ከተጠቀሱት ሕጻናትን የሚጎዱ ድርጊቶች ይባስ ብሎ በጦርነት ግንባር እንዲሰለፉ መገዳደቸው በምሁራን በኩል ትችትን አስነስቷል።
ሕጻናትን በጦርነት ግንባር ማሰለፍ ከሕግም ከሰብዓዊነትም ያፈነገጠና ሊወገዝ የሚገባው ነው ሲሉ የሚወቅሱት የፖለቲካ ተንታኙ አብዱ አያሌው ናቸው።
ሕወሓት አገር የማፍረስ ሴራውን በተግባር ለማስመስከር የጦርነት ፊሽካ ከነፋበት ከ2013 ጀምሮ ሕጻናትን አስገድዶ የጦርነቱ ፍልሚያ ተዋናይ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹እውነት ይነገር ከተባለ ኹለተኛና ሦስተኛ ወገን ሳይጨመርበት ድርጊቱን ራሱ ቡድኑ ማውገዝ እንዳለበት ልቦናው ያውቀዋል›› ብለዋል።
በጦርነቱ የሕጻናት መብትን ጨምሮ በርካታ የሕግ ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው ያሉት አብዱ፤ ‹‹ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በተለይም የሕጻናቱን መብት አስገድዶ እየነጠቃቸው ነው›› ይላሉ።
18 ዓመት ያልሞላቸው ሴትም ሆነች ወንድ ከሕጻናት ተርታ እንደሚመደቡ ይነገራል። ታዲያ በጦርነት ግንባር እየተሳተፉ የተስተዋሉት ግን የሦስት ዓመት ለጋ ሕጻናትም ጭምር ናቸው። እነዚህ ለጋ ሕጻናት በእናቶቻቸው ጀርባ መታየታቸው ተቃራኒ ቡድን መሣሪያ እንዳይተኩስ ለማድረግ ያቀደው የሕወሓት ስልት መሆኑን በግንባር የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባል ይገልጻሉ።
ሕጻናትን ቃታ እንዲስቡ ከማድረግ በተጨማሪ ገና ጠብተው ያልጨረሱ ልጆቻቸውን በጀርባቸው አዝለው እንዲታኮሱ የተገደዱ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች መማረካቸውን ሥሜ ባይጠቀስ ያሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹እንዳንተኩስ ሕጻናቱ ይሞታሉ። ዝም እንዳንል ከፊት ለፊት አድፍጦ የሚከታተለው የሕውሓት ታጣቂ መተኮሱን አያቆምም›› ያሉት የመከላከያ አባል ‹‹የሕጻናቱንና የእናቶችን ሕይወት ማትረፍ የምንችልበት አጋጣሚ በማፈላለግ ዝም ብለን የማረክንበት አጋጣሚ ብዙ ነው›› ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደም የሕጻናቱ አሰቃቂ ሕልፈተ ሕይወት “ሀ” ብሎ የጀመረው በተለይም በ2013 ሐምሌ ወር የሕወሓት ታጣቂ ቡድን በአፋር ክልል ባደረሰው ጥቃት ነበር። ሕወሓት በአፋር ክልል ከያሎና ጎሊና ወረዳዎች ተፈናቅለው ጋሊኮማ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት ተጠልለው በነበሩ በሺዎች የሚጠሩ አርብቶ አደሮች ላይ ባደረገው አሰቃቂ ጭፍጨፋ 107 ሕጻናት፤ 89 ሴቶች እንዲሁም 44 አዛውንቶች በድምሩ 240 ንጹሐን መሞታቸውን የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ በመጀመሪያ ሪፖርቱ ገልጾ ነበር።
በአማራ ክልል ደጋማውና ቆላማው ክፍልም እንዲሁ በርካታ ሕጻናት የጦርነቱ ሰለባ መሆናቸው ሲነገር ነበር።
ጦርነቱ ‹‹በሕግ ማስከበር ዘመቻው›› ይቋጫል ሲባል፤ ይባስ ብሎ እየናረና እየተስፋፋ መጥቶ ዘርፈ ብዙ ጉዳት በማስከተል ዓመት ከስድስት ወር ገደማ እንዳስቆጠረ ‹‹በድርድር ይፈታል›› ተብሎ ተስፋ ተጣለበት። ይህም ሳይሳካ ቀርቶ ታጣቂ ቡድኑ ባሳለፍነው ነሐሴ 18/2014 ለሦስተኛ ጊዜ የተለመደ ጥቃቱን ከፍቶ ይገኛል። ታዲያ የሰሜኑ ጦርነት እየተራዘመ መጥቶ ድፍን ኹለት ዓመት ሊያስቆጥር ኹለት ወራት ብቻ ቀርተዉታል።
በአንድ ዓመት ከ10 ወር ውስጥ አዋቂዎችን ጨምሮ ጨቅላ ሕጻናት በግንባር ተሰልፈው ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስተናገድ የተገደዱበት ተደጋጋሚ ድርጊት መፈጠሩ ‹‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጥቅም የለውም እንዴ› የሚል ትችትን አስነስቷል።
የፖለቲካ ተንታኙ አብዱም ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ሲገልጹ፤ ‹‹የረቀቀ ሕገ መንግሥት ባለቤት ናት በምትባል አገር ለተከታታይ ጊዜ ሕጻናትን በጦርነት መሪ አድርጎ ማሰለፉ፤ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ትንሣኤ እንደራቀው ያሳያል›› ሲሉ ተናግረዋል።
ታጣቂ ቡድኑ በአንድ በኩል ለሕጻናትና ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ ይመስላል፤ ወዲህ ደግሞ በሕጻናቱና በሕዝቡ ላይ ግፍ ይሠራል ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ የኢትዮጵያ ገዢው መንግሥትም ቢሆን ሕግን ከማስከበር ይልቅ እያስጣሰው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ታዲያ ቡድኑ ከአምና እስከ ዘንድሮ እረፍት እየወሰደ በሚጎስመው የጦርነት ነጋሪት ሕጻናትን ወደ ግንባር እያሰለፈ ስለመሆኑ በየወቅቱ ከጦርነቱ ግንባር የሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከነሐሴ 18/2014 ጀምሮ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ዳግም በተቀሰቀሰውና ገና እልባት በራቀው ውጊያም፣ ሕጻናትን በማስገደድ በጦርነቱ ግንባር መሪ ተዋናይ አድርጎ የማሰለፍ ድርጊቱን እንዳላቆመና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብም በተገቢው እያወገዘው ስላለመሆኑ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ዘግበዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ አስከፊ ጥቃቶችና ግጭቶች ስለመከሰታቸው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅት በሰኔ ወር 2014 ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ዘግናኝ ድርጊት እየተፈጸመ ነው ሲሉ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር።
ታዲያ በሚፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት ጨቅላ ሕጻናትም ተሳታፊ መሆናቸው ይነገራል። የፖለቲካ ተንታኙ በበኩላቸው፣ ከአራት ዓመታት ወዲህ በሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ በአንድም በሌላም ምክንያት ሕጻናት ለጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል ብለዋል። አያይዘውም አስከፊ ድርጊቱን ለማስቆም ከዚህ በላይ መቆየት ብዙ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉ መክረዋል።
በዓለም ላይ ከአምስት ሕጻናት አንዱ በጦርነት ውስጥ እንደሚኖር ከሴቭ ዘ ችልድረን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የሕጻናት የመኖር መብት በበርካታ ምክንያቶች እየተጣሰ ነው። ከጦርነት ሌላ ድርቅም ለመኖራቸው መሰናክል ሆኖባቸው ተስተውሏል። በሱማሌ ክልል በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ምክንያት የተራቡ ዝንጀሮዎች ሕጻናትን ማጥቃት ጀምረው እንደነበር ሴቭ ዘ ችልድረን መጥቀሱን አዲስ ማለዳ ሰኔ 11/2014 ዘግባ ነበር።
ድርጅቱ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት በ10 ሺዎች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሕጻናት ላይ እንደተጋረጠባቸውም ማሳወቁ ተዘግቧል። ሴቭ ዘ ችልድረን በኅዳር 23/2011 ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥነምግብ ፖሊስን በማጸደቅ የምግብ ፈተናዎች ላይ እርምጃ እንደወሰደች ገልጾ የነበረ ሲሆን፤ ያሉት ኹኔታዎች ግን ችግሩ እንዳልተቀረፈ ይጠቁማሉ።
ከኹሉም በላይ ግን በሰሜኑ በኩል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከአምና እስከ ዘንድሮ በሕጻናት መብት ላይ የለየለት የመብት ጥሰት እየፈጸመ ጎልቶ ስለመታየቱ ነው የተለያዩ ምሁራን የገለጹት።
የሥነ ልቦና አማካሪው ዓባይ ተከስተ በበኩላቸው፣ ሕጻናትን በጦርነት ማሰለፍ ይቅርና ጦርነት ባለበት አካባቢ ማቆየት፤ ሰው ሲገደል፤ በጎርፍ ሲወሰድ እንዲያዩ ማድረግ በአእምሯቸው አሉታዊ ተጽዕኖን ይፈጥራል ሲሉ ያስረዳሉ።
በመሆኑም፣ በጦርነት እየተሳተፉ ያደጉ ሕጻናትን አትራፊው ፈጣሪ ስለሆነ የመኖር እድላቸው ቢረዝም እንኳ፤ የነገ ጠዋት ሕይወታቸው የሰላም ሳይሆን የጦርነት አውድማ የሞላበት ይሆናል ነው ያሉት።
የሰው ልጅ ሥነ ልቦና የሚጎዳው በተለይም በጦርነት ወቅት ነው ብለው፤ ይህ እንዳይፈጠር ድርጊቱን ወላጆችም፤ መንግሥትም ታጣቂዎችም ደጋግመው በማሰብ ሕጻናቱን መታደግ የሁሉም ኅብረተሰብ ኃላፊነት ነው ሲሉ አሳስበዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015