ዳሰሳ ዘ ማለዳ ሐሙስ ጥቅምት 13/2012

0
592

1–ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ጥቅምት 13/2012 በሰጠዉ መግለጫ በአገሪቷ እንኳንስ ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጎሣንና ኀይማኖትን መሠረት ያደረጉ መጠነ ሰፊ ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋታቸው እንዳሳሰበው የገለፀው ቅዱስ ሲኖዶሱ፤ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የጸሎትና ምሕላ እንዲደረግ ማወጁን ገልጿል።(ቢቢሲ)

………………………………………………………………

2–ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ልዩነት በውይይት ለመፍታት ከስምምነት ላይ መድረሳቸዉ ተገለፀ። የሦስቱ አገራት ቴክኒካል ኮሚቴ መድረክም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚያሻቸው ጉዳዮችን ደግሞ በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን መሪዎቹ ተናግረዋል።በሩሲያ ሶቺ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሩሲያ አፍሪካ ኢኮኖሚክ መድረክ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚጉኙት ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር የጎንዮሽ ውይይት እያካሄዱ ይገኛል።(ኢቢሲ)

………………………………………………………………

3-በዚህ ዓመት 2012 ከኦጋዴን እስከ ጅቡቲ ድረስ የሚደርሰዉን የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ለማስጀመር ድርድር እየተካሄደ መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።ሚንስትር ደኤታው ኳንግ ቱትላን(ዶ/ር) ከኩባንያዎች ጋር ያለውን ድርድር በፍጥነት በመጨረስ ከኦጋዴን እስከ ጅቡቲ ኢላላ ድረስ ያለውን 760 ኪሎ ሜትር ቱቦ ዝርጋታ በያዝነው ዓመት እንደሚጀመር ገልጸዋል።ኦጋዴን ላይ የተጀመረው የሙከራ ምርት የቀጠለ ሲሆን እስካሁን 3 ሺሕ 900 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ወጥቶ ለሽያጭ የቀረበ ሲሆን 1 ሺሕ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ደግሞ እንደተከማቸ ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

………………………………………………………………

4-ሕወሓት በፓርቲዎች ውህደት ዙርያ ኢህአዴግ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች የተለየ አቋም እንደሌለው የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) አስታወቁ።የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተቀዳሚ ተግባሩ የሕዝቡን ሰላም እና ደህንነት በማረጋገጥ ልማትን በማፋጠን ኅብረተሰቡን ከድህነት በማውጣት ኑሮውን ማሻሻል፣ ከአማራ ሕዝብ ሆነ ከሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ጋር በጋራ መልማት እና ማደግ እንጂ ሌላ ፍላጎት እና ዓላማ የለውም ብለዋል።(ቢቢሲ)

………………………………………………………………

5-በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው “የሰማያዊ ልብ” ግንዛቤ መፍጠሪያ ንቅናቄ ከፍተኛ የመንግሰት ባለስልጣናት፣ ዓለም አቀፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና 11 ሺሕ ዜጎች በተገኙበት ነገ ጥቅምት 14/2012 በሚሊኒየም አደራሽ እንደሚካሄድ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዝናኑ ቱኑ ገልጸዋል።“የሰማያዊ ልብ” ተስፋን፣ ሰላምንና ደህንነትን የሚያመለክት ሲሆን  የሰማያዊ ልብ ንቅናቄ የሕገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመከላከል ግንዛቤ መፍጠር ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።(አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………

6-በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ዛሬ ጥቅምት 13/2012 በነበረዉ ግጭት አራት ሰዎች ሞተው ወደ ዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል መምጣታቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቶላ በዮ ተናግረዋል።በትናንትናው ዕለት ኹለት ሰዎች በጥይት ተመትተው መምጣታቸውንና ሕይወታቸው ማለፉን ገልፀው፤ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሦስት ሰዎች ደግሞ ምሽቱን ወደ ሻሸመኔና ሐዋሳ ለሕክምና መላካቸውን ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።(ቢቢሲ)

………………………………………………………………

7-በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው የባሌ ሮቤ ከተማ ለጀዋር መሐመድ ድጋፍ ከተደረገ ሰልፍ በኋላ በተቀሰቀሰ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። የባሌ ሮቤ ነዋሪዎች የሐይማኖት መልክ ይዟል ባሉት ግጭት ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እና ሻይ ቤቶች መቃጠላቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።የከተማዋ ነዋሪዎች ከትናንት አመሻሽ ጀምሮ ባሌ ሮቤን ከሌሎች አካባቢዎች የሚያገናኙ መንገዶች፣ የግብይት መደብሮች፣ የመንግሥት እና ማኅበራዊ ተቋማት መዘጋታቸውን ተናግረዋል።(ዶይቼ ቬለ)

………………………………………………………………

8- የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት  ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ዛሬ ጥቅምት 13/2012  ከጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተላከ ልዩ መልዕክት ለጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ አስረክበዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ጃፓን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የልማት ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የጅማ-ጪዳ መንገድን ለመገንባት 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን የን ድጋፍ ማድረጓን ሽንዞ አቤ አስታዉሰዋል።(ዋልታ)

 

 

9-በአዳማ ከተማ በተለምዶ ፍራንኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ላይ ዛሬ ጥቅምት 13/2012  ንጋት ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ከ30 በላይ አነስተኛ ሱቆች ላይ ጉዳት ደርሷል።የከተማ አስተዳደሩ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ኃላፊ ጉታ ኃይሌ እንደገለጹት ዛሬ ንጋት ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ 24 አነስተኛ ሱቆች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን 10 የሚሆኑት ደግሞ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

…………………………………………………………………..

10 የአማራ ክልል በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚከበረው ብሔራዊ የደም ልገሳ ቀን 11ሽሕ 244 ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የሚያስችል 4ሽሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታወቀ። (አዲስ ማለዳ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here