ዳሰሳ ዘ ማለዳ ጥቅምት 14/2012

0
833

1-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል የዘረጋውን ዘመናዊ የህክምና አስተዳደር ስርዓት አስመርቆ አስረከበ። ዘመናዊ የህክምና አስተዳደር ስርዓቱ የታካሚዎችን መረጃ ዲጂታል በሆነ መልኩ የሚይዝና የወረቀት ካርድ አሰራርን የሚያስቀር መሆኑ ታዉቋል። አንድ ታካሚ የሚሰጠው ዘመናዊ ካርድ በሆስፒታሉ በሚገኙ ሁሉም ኮምፒውተሮች ላይ ሊነበብ የሚችል የታካሚ መረጃን እንዲይዝ ተደርጎ ስርዓቱ በተዘረጋባቸው ሆስፒታሎች ሁሉ መገለገል በሚያስችል መልኩ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ገልጸዋል።(አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………….

2-በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 65 ሺሕ 200 የአሜሪካ ዶላር ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ከነተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቋል።ጥቅምት 12/2012 ከንጋቱ 11 ሰዓት 50 ላይ 65 ሺሕ 200 የአሜሪካ ዶላር በላስቲክ ጠቅልሎና በፒላስተር አሽጎ በሻንጣ ውስጥ ከልብስ ጋር ደብቆ ወደ ክፍለ አገር ለመጓዝ መስቀል አደባባይ ላይ አውቶቡስ ሊሳፈር የነበረ ግለሰብ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተደረገ ክትትል ሊያዝ መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል። (አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………….

3-አፍሪካ የራስ በቀል የICT ቴክኖሎጂን (Indigenous ICT Technology) በማልማት ረገድ በስፋት ልትንቃሳቀስ እንደሚገባ 3ኛው የአፍሪካ ኅብረት የልዩ ቴክኒካል ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ላይ የኮሚቴው ሰብሳቢ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የICT ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል አብዮት ሴናሞ ተናግረዋል። የአፍሪካን የመገናኛና የ ICT ደህንነትን ለማስጠበቅ የአፍሪካ የሳይበር ደህንነት ሰራዊት (African Cyber Security Force) እንዲቋቋም ጥሪ አቅርበዋል። (አዲስ ማለዳ)

……………………………………………………….

4-ባለፉት ኹለት ቀናት በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀዉ ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖችን ለማረጋጋት እና መልሶ ለማቋቋም ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ድጋፍ እንደሚያደርግ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት አስታውቋል። ክልሉ  ጥቅምት 14/2012 በሰጠዉ መግለጫ በግጭቱ  የዜጎችን ሕይወት ማለፍ፤ ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለንብረት ውድመት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

……………………………………………………….

5-ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ለሴፍቲኔት መርሃ ግብር  የሚውል የ325 ሚሊዮን ብር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ።የድጋፍ ስምምነቱን የንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እና የአየርላንድ መንግስት የትብብር መሪ ፓትሪክ ማክማኑስ ተፈራርመዋል።በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ድንገተኛ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ለመቋቋም፣ ለምግብ ደኅንነት እና የአመጋገብ ስርዓትን ለማሻሻል የሚውል ነው ድጋፉ ተብሏል። መርሃ ግብሩ ከፈረንጆቹ 2015 እስከ 2020 የሚቆይ ሲሆን ዛሬ የተፈረመው ድጋፍ ለ2019/2020 የሚውል መሆኑን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታዉቋል።(ኢቢሲ)

……………………………………………………….

6-የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ የአገርን ሰላም በማስቀደም ለመረጋጋት መስራት እንደሚገባ አሳስቧል።ምክር ቤቱ በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች ሁሉንም በጋራ የሚጎዱ ቀውሶች የሁሉንም ዜጋ መስተጋብር የሚፈትኑና ማኅበረሰባዊ ትስስሮችን የሚበጥሱ በመሆናቸው አላህ የሰጠን ፀጋ አካል የሆነችው ውድ እናት አገራችን ወደ ተወሳሰበ የችግር አዘቅት እንዳትገባ መጠንቀቅ ሃይማኖታዊም ዓለማዊም ግዴታ ነው ብሏል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

……………………………………………………….

7-ባለፉት ኹለት ተከታታይ ቀናት በሩሲያ ሶቺ ከተማ ሲካሄድ በነበረው የሩሲያ አፍሪካ የትብብር መድረክ ላይ ሞስኮ ኢትዮጵያ የነበረባትን 163 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የብድር እዳ መሰረዟን አስታዉቃለች።የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈትቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን የተሰረዘው ዕዳ የኢትዮጵያን ልማት ሊያፋጥኑ በሚችሉ ስራዎች ላይ እንዲውል መሪዎቹ መስማማታቸውን ገልጸዋል።ኹለቱ አገራት በትምህርት፣ ማዕድንና ግብርና ዘርፎች ተደጋግፈው ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውም አስታዉቀዋል። (አብመድ)

……………………………………………………….

8-የኦሮሚያ ክልል በቡና ልማት ላይ በትኩረት ለመስራት የሚያስችለውን የአምስት አመታት ፕሮጀክት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት በነቀምቴ ከተማ ይፋ ሆኗል። ለኢትዮጵያየ ወጪ ምንዛሪ የሚያስገኘውን ቡና በመላክ ሥራ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የ15 ቢሊዮን ብር ብድር ለማቅረብ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።የክልሉ መንግስት በተያዘው ዓመት ለቡና ልማት ብቻ 127 ሚሊዮን ብር መድቦ ስራዎችን መጀመሩንና ጥራቱን የጠበቀ እና እሴት የታከለበት ቡና ወደ ገበያ ለማቅረብ በአግሮ ኢንዱስትሪ የማቀነባበር ስራ እንደሚከናውንም ሽመልስ ገልጸዋል። በክልሉ በተያዘዉ በጀት ዓመት ለቡና እና አቮካዶ ምርት ልማት 147 ሚሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል።(ዋልታ)

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here