ገቢዎች ሚኒስቴር ግብር ያላሳወቁ ከ4 ሺሕ በላይ ደርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስደ አስታወቀ

0
728

በአዲስ አበባ የሚገኙ 4ሺሕ451 ድርጅቶች ከ2011 የበጀት ዓመት ጀምሮ የትርፍ ገቢ ግብር ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እያሳወቁ አለመሆኑን ተከትሎ ከጥቀምት 11 2012 ጀምሮ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ቀርበው የማያሳውቁ ከሆነ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።

በወቅቱ ያላሳወቁ ግብር ከፋዮች በሚወጣው መመዘኛ መሰረት በዘገዩበት በእያንዳንዱ ጊዜ ባልተከፈለው ታክስ ላይ ከ አምስት በመቶ ጀምሮ ሃያ አምስት በመቶ የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልባቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኡሚ አባጀማል ጥቅምት 11 ቀን 2012 በሰጡት ጋዜጣዊ መገለጫ ላይ ተናግረዋል። አክለውም የሚጠበቅበትን ግብር ያልከፈለ ድርጅት ሀብት እና ንብረትን በመያዝ የመንግሥት ገቢ እንዲሰበሰብ ይደረጋል ብለዋል።

የትረፍ ገቢ ግብር በእየ ዓመቱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደግሞ በእየ ወሩ የታክስ ማስታወቂያ በመሙላት ለታክስ አስተዳደሩ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም ያላሳወቁ ግብር ከፋዮች በተሰጣቸው እድል ተጠቅመው የማያሳወቁ ከሆነ ተቋሙ በማንኛውም ጊዜ የሚያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ የታክስ ከፋዩ መክፈል የሚገባውን ታክስ በግምት በማስላት ግብር እንደሚጣልበት ተገልጿል።

በሌሎች ክልሎች በተመሳሳይ ያላሳወቁ ድርጅቶች በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ የተገለፀ ሲሆን፣ ግብር በሚያጭበረብሩ ድርጅቶች ላይ ከሚመለከታቸው የሕግ አካለት ጋር በመሆን እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ ኡሚ አባጀማል ተናግረዋል።

ገቢዎች ሚኒስቴር በ2012 ሩብ ዓመት 57 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን እና አፈፃፀሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ከ12 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጾ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here