አገር ዐቀፍ የደም ልገሳ ዘመቻ ተጀመረ

0
820

ጥቅምት 15/2012 ለሚካሔደው አገር ዐቀፍ የደም ልገሳ 10 ሺሕ ሰዎች ቅድመ ምዝገባ እና ቋሚ ለጋሽ ለመሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደም ለጋሽ የሚያሳትፍ ዘመቻ ይካሔዳል።

ዘመቻው ላይ ዜጎች እንዲሳተፉ በማህበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ቅስቀሳዎች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን በመላው አገሪቱ በተዘጋጁት 43 የደም ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች ከተመዘገቡት 10 ሺሕ ሰዎች ደም ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚገኙ ይጠበቃል።

የደም ልገሳ ዘመቻውን ለማስተባበር 720 የሚደርሱ በጎ ፈቃደኞች ዝግጅት ያደረጉ ሲሆን እድሜው ከ 18 እስከ 65 ሆኖ ከ45 ኪሎ በላይ የሚመዝን ማንኛውም በጎ ፈቃደኛ መሳተፍ ይችላል።

የብሔራዊ የደም ባንክ ምክትል ዋና ዳይሬክትር አቶ ያረጋል ባንቴ፣ ብሔራዊ የደም ባንክና የጤና ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ ስታዲየምና ጎማ ቁጠባ በሚገኙት የደም ባንክ መሥሪያ ቤቶች፣ በተለምዶ መገናኛ፣ ሚክሲኮ እና ጦር ኃይሎች አደባባይ ደም የሚሰጥባቸው ቦታዎች ተዘጋጅተዋል።

የደም ልገሳውን ለየት የሚያደርገው በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በተጀመረው የድረ ገጽ ምዝገባ ላይ ቀድመው ቦታ መያዛቸው ሲሆን፣ የተዘጋጀውን መተግበሪያ በቋሚነት ደም ለመለገስ የሚፈልግ ሰው ቋሚ አባል የሚሆንበት አሠራር ይፋ መደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

‹‹መተግበሪያ ከበጎ ፈቃደኛው የተገኘው ደም ወደ ሕክምና ተቋማት ሲሰራጭ ለለጋሹ መልዕክት የሚላክበት አሰራር የያዘ ነው›› ሲሉ ኀላፊው ገልፀዋል። በተጨማሪም በጎ ፈቃደኛው ከሦስት ወር በኋላ በድጋሚ ደም ለመስጠት እንዲችል ማስታወሻ የሚልክ መተግበሪያ እንደሆነ አክለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here