ሲንቄ ባንክ በአዲስ መለያ የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ

0
835

ባንኩ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉን የብራንድ አምባሳደር አድርጎ ሾሟል

ሐሙስ መስከረም 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ሲንቄ ባንክ በአዲስ መለያ (Brand) የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ አስታውቋል።

በባንኩ የአገልግሎት ማስጀመሪያና የአዲሱ መለያ ምልክት ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም የባንኩ ደንበኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል።ሲንቄ ባንክ ከማይክሮ ፋይናንስ ወደ ባንክ በማደግ በአገሪቱ የመጀመሪያውና ፈር ቀዳጅ ባንክ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ፕሬዝዳንት ንዋይ መገርሳ፤ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ፣ አዉሮፓና ዩሮ-ኤዥያ አገራት ባንኮች ጋር ለመስራት የሚያስችለውን ዓለም አቀፋዊ ትሥሥር በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ባንኩ ከዚህ ቀደም ይሰጠው የነበረውን የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎትም በማካተት የተሟላ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጸዋል።

ሲንቄ ባንክ የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ይሰጡ ከነበሩ 405 ቅርንጫፎቹ መካከል 250ዎቹ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ ማግኘታቸውንም ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ 155 ቅርንጫፎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ባንክ ቅርንጫፍነት የሚሸጋገሩበት ሥራ በሰፊው እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ቶሎሳ ገደፉ በበኩላቸው፤ ባንኩ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ኢኮኖሚው በብድር መልክ ማሰራጨቱን ገልጸው፤ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥርም ከ 1 ሚሊዮን በላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ሲንቄ ባንክ በመርሃ ግብሩ ላይ ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉን የብራንድ አንባሳደር አድርጎ የሾመ ሲሆን፤ በቀጣይ የሚጠቀምበትን አዲስ መለያም በመድረኩ ይፉ አድርጎል።

ሲንቄ ባንክ የተሟላ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የሥራ ፍቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መጋቢት 27 ቀን 2014 ያገኘ ሲሆን፤ 15 ቢሊየን ብር የተመዘገበና 7 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል በመያዝ የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ የተቀላቀለ ባንክ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here