በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች ላይ ሦስተኛ ወገን ቢገባ ችግር እንደማይኖረው ተገለፀ

0
550

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ግብፅ እና ኢትዮጵያ በሚያደርጉት የፖለቲካ ውይይት ላይ ሦስተኛ ወገን ቢገባ ችግር እንደማያመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሩስያ ሶቺ ከተማ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ሲካሔድ በነበረው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ወቅት እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ትልቅ አገራት በመሆናቸው በአገራቱ መካከል የሚፈጠር ችግር አፍሪካ ላይ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል በሚል ፍራቻ የተለያዩ አገራት ሩስያን ጨምሮ ለማደራደር ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ሦስተኛ ወገን በውይይቱ ላይ እንዲካተት ግብፅ ያቀረበችውን ጥያቄ በተመለከተ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በግድቡ ዙሪያ በሚደረገው ፖለቲካዊ ውይይት ሦስተኛ ወገን ቢገባ ችግር አይኖረውም ብለዋል። ይሁን እንጂ፤ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ቴክኒካል ኮሚቴ የሚያደርጉት ውይይት ባለበት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተጨማሪም፤ ግብፅ እና ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና አጠቃቀም ዙሪያ ሰላማዊ እንዲሁም ግልፅ የሆነ ውይይት ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል። ኹለቱ አገራት በተለይም ግብፅ ከወራት በፊት የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዲዘገይና አጠቃቀሙ ላይ የመቆጣጠር ሚና እንዲኖራት መጠየቋን ተከትሎ እሰጣ ገባ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል። ለዚህም እሰጣ ገባ ዋነኛ ችግሩ ሚዲያዎች በኹለቱ አገራት መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው ሲሉ ዐቢይ ተናግረዋል።

በአገራቱ መካከል ያለውን ውይይት በድጋሚ ለማስጀመር እና የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የግብፁ አቻቸው አብዱልፈታ አልሲሲ ባለፈው ሳምንት በሩስያ ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን የግድቡ ገለልተኛ የሆነው የቴክኒካል ኮሚቴ ሥራ እንዲጀመር ተስማምተዋል።

በተጨማሪ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመስከረም ወር በግድቡ ዙሪያ ምክክር ማደረጋቸውን ተከትሎ መስማማት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ግብፅ ዓለም ዐቀፍ አደራዳሪዎች እንዲገቡ ጥሪ አቅርባ የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያ ጥያቄውን እንደማትቀበል መግለጿ ይታወቃል። በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥት ኹለቱን አገራት ለማደራደር ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን ይህንንም ግብፅ ተቀብላለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here