የአዲስ አባባ ፈጣን አውቶቢስ መንገድ ግንባታ ኅዳር ወር መጨረሻ ይጀመራል ተባለ

0
842

በመጪው ኅዳር ተጀምሮ በኹለት ዓመት ይጠናነቀቃል የተባለው አዲስ አበባ ፈጣን አውቶቢስ መንገድ ግንባታን ለማከናወን ኹለት የፈረንሳይ ድርጅቶች ተመርጠው የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡም ውጤቱን ይፋ በማድረግ ወደ ግንባታ ሊገባ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገድ ትራስንፖርት ባለሥልጣን አስታወቀ።

ከፈረንሳይ ባንክ በተገኘ 80 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ እና በአዲስ አባባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ትብብር የሚገነባው የፈጣን አውቶቢስ መተላለፊያው፣ 17.4 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እና በሰዓት 6 ሺሕ 500 ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዝ ነው። ፈጣን አውቶቢስ መንገድ ከዊንጌት በፓስተር ተክለሃይማኖት፣ ቄራ አድርጎ መዳረሻው ጀሞ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።

ሳፌጅ እና ሳይስትራ የተሰኙ የፈረንሳይ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት የግንባታ አማካሪዎች በዲዛይን እና የማማከሩን ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ የገለጹት የአዲስ አበባ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ የሥራ ኀላፊ የሆኑት ኤርሚያስ በላቸው፣ የወሰን ማስከበር ሥራዎች በመገባደድ ላይ እንዳሉም ተናግረዋል። ‹‹መተላለፊያው የሚያልፍባቸው አካባቢዎች በርካታ ሰዎች የሚኖሩባቸው እና ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ተቋማት የሚገኙባቸው መሆናቸው የዲዛይን እና ወሰን ማስከበር ሥራውን ውስብስብ አድርጎታል›› ሲሉ ገልፀዋል።

ከ 40 በላይ የሀገር ውስጥ እና አለም ዓቀፍ የግንባታ ተቋራጮች በጨረታው ላይ ለመሳተፍ የጨረታ ሰነድ መግዛታቸው የተገለፀ ሲሆን የመንገዱን ግንባታ የሚያከናውነውን ድርጅት ለመለየት የጨረታ ሂደት እየተከናወነ ሲሆን በቅረቡ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

መንገዱ በሚያልፍባቸው እና ከፍተኛ የህዝብ እንቀስቃሴ ባለባቸው የከተማው አካባቢዎች 25 ሜትር እና በአመዛኙ ክፍት በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ እስከ 40 ሜትር የጎን ስፋት አለው።

የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ያቃልላል የተባለለት ይህ ፈጣን አውቶቢስ መንገድ 23 ፌርማታዎች ይኖሩታል። በመተላለፊያው ከሚሰማሩት 160 አውቶቡሶች ውስጥ 73 የሚሆኑት 12 ሜትር እርዝማኔ ያላቸው ሲሆኑ ቀሪዎቹ 87 የሚሆኑት ደግሞ እስከ 18 ሜትር እርዝማኔ የሚኖራቸው ተቀጣጣይ አውቶቢሶች እንደሚሆኑ ተገልጿል።

በሚሠራው ፈጣን አውቶቢስ መተላለፈያ ላይ አወቶቡሶቹ ከሌሎች ተሸከርካሪዎች ጋር ሳይቀላቀሉ እንዲጓዙ የሚደረግ ሲሆን መተላለፊያው ከመደበኛ መንገዶች ጋር በሚገናኝባቸው ቦታዎች ላይ ፈጣን አውቶቢሶቹ ቅድሚያ አግኝተው እንደሚጓጓዙ አዲስ አበባ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ዘርፍ አቅም ማጎልበት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ኃላፊ ቴዎድሮስ ፀጋዪ ገልፀዋል።

መተላለፊያው በሚሠራባቸው አካባቢዎች በሠራተኛ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ላይ ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍላጎት መኖሩ በጥናት መረጋገጡን ቴዎድሮስ ፀጋዪ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክለውም የአውቶቢሶቹን አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ተሳፋሪዎች አውቶቢሶቹ የት እንደደረሱ እና በምን ያህል ጊዜ በየፌርማታው እንደሚደርሱ የሚያሳይ ዘዴ የሚኖራቸው ሲሆን ከአምስት ደቂቃ በታች በሆነ ጊዜ ውስጥ በየአንዳንዱ ፌርማታ ይደርሳሉ ብለዋል።

በግንባታው ላይ የሚፈጠረውን የሥራ እድል ሳይጨምር ፈጣን አውቶቢሶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ 700 ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል የሚፈጥር ነው። ከነዚህም ውስጥ 300 አሽከርካሪዎች እና በፌርማታዎች እና በአውቶቢስ ማደሪያዎች ላይ የሚሠሩ በርካታ ሠራተኞችን የሚቀጥር ይሆናል።

የፈጣን አውቶቢስ መተላለፊያው በብዙኀን ትራንስፖርት አማራጮች የከተማዋን ትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ እና በከተማዋ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አውታርን ለመዘርጋት ከሚደረጉት ጥረቶች አንዱ ሲሆን፣ በቀጣይም መሰል መንገዶች እንደሚገነቡ አዲስ አበባ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ገልጿል።

እንደ አዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መረጃ መሰረት በአማካኝ አንድ ሰው ከትራንስፖርት እጥረት እና ከትራፊክ መጨናነቅ ጋር በተያያዘ በየቀኑ አራት ሰዓታትን ያባክናል። ለዚህም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተሸከርካሪዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት በመዲናዋ በአዲስ አበባ መገኘታችው እና የትራፊክ ሕግን አክብረው የማይንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች እና እግረኞች በመንስኤነት ተጠቅሰዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here