ፈጣሪዋ

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ተፈጥሮ ለእናትና ለሴት የምታደላ ይመስለኛል። ለሰው ልጅ በሕይወት የመቀጠል ተፈጥሮ የተሰጠው ለሴት ነው። በተጨማሪም ልጅን ከሁሉም በበለጠ መልኩ የመረዳት ተፈጥሮ ያላት እናት “ሴት” ናት። የብዙዎቻችንም አሁን ያለንበት ማንነታችን መሠረቱ የተጣለው በእናት ነው።

ፈጣሪና እናት። ኹለቱም በግብር ይመሳሰላሉ። ይከታተላሉ። ፈጣሪ ቀዳሚና ጀማሪ ሲሆን እናት ደግሞ ተከታይና ጨራሽ ናት። ፈጣሪ የሰው ልጅን ከነሙሉ “ሰውነቱ” ፈጠረው። እናት ደግሞ የተፈጠረው ሰውነት ላይ ማንነትን ሠራች። ፈጣሪ ለሰው ልጅ ሕግን ሲቀርጽ፣ እናት ደግሞ ተግባሩን ልጇ ላይ ቀስ በቀስ ታሰርጻለች።

ፈጣሪ ለፍጡራኑ ከትእዛዙ ሲወጡ እና ሲያከብሩ የሚደርስባቸውንና የሚደርስላቸውን አዘጋጅቶ አስቀምጧል። ተከታይዋ ደግሞ ትእዛዝ ማክበር የሚያስገኘውንና አለማክበር የሚያመጣውን ውጤት ልጇ ልብ ላይ ታሰራጫለች።

ሰውን መፍጠር የፈጣሪ ግብር ነው። ሰው ላይ ሰውነትን ማስረጽ የእናት ተግባር ነው። ፈጣሪ ሰውን ፈጠረ፣ እናት ስብእናን ሠራች። ፈጣሪ ሕይወትን ፈጠረ፤ እናት የሕይወትን መንገድ አስቀጠለች። ፈጣሪ እግር ሲፈጥር እናት አቅጣጫ መንገድ ትጠቁማለች። ፈጣሪ እናትህንና አባትህን አክብር ሲል እናት አከባበሩን በክብር ታሳያለች። የፈጣሪን ጅምር ታስጨርሳለች።

በተፈጥሮ ያገኘነው እጅ የሕይወት ሰሌዳ ላይ እንዲጽፍ የምታደርገው እሷው ናት። ከጠመዝማዛው ጀምሮ ቀጥ እስካለው ድረስ አለማምዳ የተቃናው ላይ የምታሳርፈንም እሷው ናት። ባዶው ማንነታችን ላይ ብዙ ነጠብጣቦችን አንጥባ ቅርጽ ያለው የምታደገውም እሷው ናት። ለተፈጥሮ አፍንጫ ጥሩ መዓዛ የምትሰጠው አሁንም እሷው ናት።

ማየትን የምታሳየን እናት ናት። ፈጣሪ የሰጠን ሆድ ላይ እርሱ የሰጣትን ነጭ ሕይወት ወደ እኛ የምታደርሰውና ወደ ተለያዩ ቀለም ያላቸው የሕይወት ምግቦችም የምትቀይረው የፈጣሪ ተከታይዋ ናት።

ፈጣሪ መሀንዲስ ፤ እናት የግንባታ ባለሙያ። እናት አሳማሪ ፈጣሪ ውበት ሠሪ። ፈጣሪ ብረት አቋሚ፤ እናት ሙሌት ጨማሪ። እርሱ በሐሳብ ፈጣሪ እናት ብሎኬት ደርዳሪ። እሷ ሲሚንቶ ጨማሪ፤ ጠጠርና አሸዋ አሰናጅ። ፈጣሪ መሠረቱን ቆፋሪ እናት ፎቁን ጀማሪ። ኹለቱም በየራሳቸው ፈጣሪ ናቸው፤ ፈጣሪ በባህሪው በምልዐት፣ እናት በተሰጣት የተፈጥሮ ጸጋ። ፈጣሪ ጀማሪ እናት ጨራሽ። ከፊት እሱ ከኋላ እሷ፤ እናት ተከታይ እሱ ቀዳማይ።

ኹለቱም ለአንድ ዓላማ የቆሙ ናቸው፤ ሕይወትን ለማስቀጠል። ከጨለማ ወደ ብርሀን ለመቀየር፤ ሕይወትን ለማብሰር። ለመጨረስ ለመጀመር።

ደስታ ሽርካ (ደስታ ጠማኙ)


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here