የእኛን ሰውና ዱባይን በጨረፍታ

0
1042

ኢትዮጵያዊያን ኑሮን ለማሸነፍ በዓለም ላይ በየአገሩ ተበትነዋል። ብዙዎች ተሳክቶላቸዋል፣ የሚልቁት ደግሞ ከአገራቸው ርቀውም የኑሮ ከባድ ትግል የተላቀቃቸው አይመስልም። ይህንን በዱባይ የሳምንት ቆይታው የታዘበው ታምራት አስታጥቄ፣ በክፍል ኹለት የጉዞ ማስታወሻው በዱባይ ያለውን የኢትዮጵያዊያንን ኑሮና መልክ በጥቂቱ አንስቶ፣ ካየውና ከሰማው አካፍሎናል። በዱባይ የሚገኙ ድንቅ የሚባሉ መስህቦችንም አስቃኝቶናል።

ኢትዮጵያዊያን በዱባይ

ኦሪት መሐመድ ከምሥራቁ የአገራችን ክፍል ሐረር የተገኘች ኢትዮጵያዊት ናት። በሰሜን አሜሪካ የማስትርስ ዲግሪዋን በልማት ላይ ትኩረት ባደረገው ‹ፐብሊክ ፖሊሲ› የትምህርት ዘርፍ አጠናቅቃ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰች በሦስተኛ ወሩ ነዋሪነቱ ዱባይ ከሆነው ከያኔው ፍቅረኛዋ ከአሁኑ ባለቤቷ እና የሦስት ልጆቿ አባት ጋር የመተዋወቅ ዕድል ገጠማት። ከጋብቻ በኋላ እሷም ጠቅልላ ዱባይ ላይ ከተመች።

ገና ከርቀት ለሚያያት ፊቷ ጥርስ በጥርስ የምትባልና ፈገግታዋ ከፊቷ ላይ የማይጠፋ ናት፣ እንደውም የሚጋባ፣ በቀላሉ ተግባቢና ተጫዋች ናት። ኦሪት በዐስራ ኹለት ዓመታት የዱባይ ቆይታዋ ጥሬ ቡና ከኢትዮጵያ በማስመጣትና በመቁላት ቁጥር አንድ ተመራጭ የሆነ ‹ቡን ኮፊ› የተሰኘ የቡና ብራንድ ፈጥራለች። ከዛም ባሻገር በዱባይ ብቻ ሰባት ካፌዎች በመክፈት ተቆልቶ የተፈጨና በተለያየ መጠን የተዘጋጀውን መግዛት፤ አልያም በካፌዎቹ ውስጥ የተዘጋጁትን ከነእፍታቸው መጠጣት ይቻላል።

በቅርቡ ሌሎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በአቡ ዳቢ እንዲሁም ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውጪም በሳዑዲ አረቢያ ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኗን አጫውታኛለች። ኦሪት በንጽጽር ጥቂት በሚባሉ ዓመታት ባስመዘገበችው ስኬት የዱባይ ከተማ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ቤተሰቦች መካከል አንዷ አድርጎ እውቅና እንደሰጣትም ነግራኛለች።

በእርግጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የዱባይ ኑሮ የኦሪት ግልባጭ ዓይነት ነው ማለት አይቻልም። ነገር ግን በንግዱ ዓለም ተሳክቶላቸው ከእውቅናውም ከሀብቱም ማማ ላይ ከደረሱት መካከል በብዙ የሚታወቁት በአጠቃላይ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ ዘጠኝ የ‹‹አል ሐበሻ ሬስቶራንት›› ቅርንጫፎች መሥራች የሆኑት ሣራ አራዲንን መጥቀስ ይቻላል። የዱባዩን ሬስቶራንታቸውንም የመጎብኘት እና ሣራንም የማግኘት ዕድሉ ገጥሞኛል። እንዲሁም ሌሎች በሥም ያላወቅኳቸው ኢትዮጵያዊያን በንግድ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ እንዳሉ በቆይታዬ ወቅት ተረድቻለሁ።

ኤምሬትስ በተባለው ትልቅ ሞል ውስጥ ያገኘኹት ተማም (የአባቱን ሥም ያላወቅኩት)፤ በዱባይ መኖር ከጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ሆኖታል። ቪዛውን በየሦስት ወሩ በማሳደስ እሱ ‹ተባራሪ› የሚላቸውን ሥራዎች እየሠራ አገር ቤት የሚገኙትን ባለቤቱን እና አንድ ልጁን እንደሚረዳ አጫውቶኛል። ‹‹ዱባይ ላይ ሆነህ ጾምህን አታድርም›› የሚለው ተማም፣ የዱባይን እያንዳንዱን መግቢያና መውጫ እንዲሁም ሥራ ስለማውቀው ‹‹የተረጋጋ ኑሮ ባይኖረኝም፣ የዕለት እንጀራዬን እንዲሁም ቤተሰቤን የምደግፍበትን ገቢ አላጣም›› ብሏል።

ተማም እንዳወጋኝ ከሆነ ብዙ ኢትዮጵያዊያን በታክሲ ሹፍርና እና በሱቅ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሲሆን በፊት በፊት ብዙ ሴት እህቶቻችን በሚታወቁበት የቤት ውስጥ ሠራተኝነት ግን በዚህ ወቅት ተመራጭ እንዳልሆኑ አጫውቶኛል። በዱባይ ብዙዎቹ የቤት ውስጥ ሠራተኞች ከባንግላዲሽ የሚመጡ መሆናቸውን ካሰባሰብኩት መረጃዎች ተረድቻለሁ።

በተጣበበው የጉዞ ሰሌዳዬ ምክንያት ብዙ ኢትዮጵያዊያን ይገኙበታል የተባለውን ዊምፒ የንግድ ሰፈር ለአጭር ጊዜ በእኩለ ሌሊት የመጎብኘት ዕድል አጋጥሞኛል። ባለፈው መጣጥፌ እንዳሳወቅሁት፣ ዱባይ የመብራት ችግር ስለሌለባት የብርሃን ከተማ መባሏን መጥቀሴን አስታውሳለሁ። እኩለ ሌሊት መሆኑን የሚነግረኝ ሰዓቴ እንጂ የሰዉ ብዛት፣ የሱቆች ክፍት መሆን በተቃራኒው እኩለ ቀን ነው የሚያስመስለው። ዊንፒ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፒያሳ የበዓል ግርግር ወይም የመርካቶን የዘወትር ትርምስ ነው ያስታወሰኝ። በዊንፒ እንደሌሎቹ የድባይ ሰፈሮች ሕንጻዎች እምብዛም የሉም፤ መደዳ ሱቆች እንጂ።

በዚሁ አካባቢ የሚገኝ ‹አል አሳብ› በሚባል ሕንጻ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ጭምር የሚኖሩበትን ቤት ለማየት የቻልኩ ሲሆን ንጽሕና የጎደለው፣ የተፋፈገና ምቾት የሚነሳ መሆኑ ታዝቤያለሁ። በአንድ መለስተኛ ክፍል ውስጥ ሦስት ተደራራቢ አልጋዎችን እና በአልጋዎቹ መካከል የቡና ረከቦትና ጀበና ተሰድረው ያየሁ ሲሆን መቀመጫ በማጣት በቁም የመጣኹበትን ጉዳይ ፈጽሜ ወጥቻለሁ።

የብዙኀኑ የኢትዮጵያውያን ሕይወት ይህንን እንደሚመስል ያነጋገርኳቸው ሰዎች ነግረውኛል። ይህንን ዓይነት ኑሮ በመጥላት ተማም ‹‹ብዙም ከኢትዮጵያዊያን ጋር መቀራረብ አልፈልግም። የምኖረውም የጋራ ሳሎንና መታጠቢያ ባለውና ንጽሕናው በተጠበቀ ቤት ውስጥ ከሰባት ፓኪስታንና ሕንዶች ጋር በጋራ በተከራየሁት ቤት ውስጥ ነው።›› ብሎኛል።

በየጊዜው የሚወጡ ሕጎች እንደልብ ዱባይ ውስጥ ለመሥራት አስቸጋሪ እንዳደረገበት የሚናገረው ተማም፣ በቅርቡም በየሦስት ወራት ከሚታደስ ወደ ኹለት ዓመት የሚታደስ ቪዛ በሥራ ላይ እንደዋለ ነግሮኛል። በዱባይ ለመሥራት የሥራ ፈቃድ ማግኘት ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ካነበብኩት የመረጃ ቋት ተረድቻለሁ። ይህንን በተመለከተ ተማምን ስጠይቀው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁኔታዎች ዱባይ ውስጥ ለመሥራት እየጠበቁ መምጣታቸውን ጠቅሶልኛል። ‹‹ለእኔ የመጨረሻ አማራጭ የማደርገው በብር ሲሰላ ከኹለት መቶ ሺሕ ብር በላይ በመክፈል ቪዛ በመግዛት ቆይታዬን ማራዘም ነው።››

ቅን፣ ተባባሪና ትኹት የሆነው ተማም፣ ሜትሮ ፈጣን ባቡር በመጠቀም ከኤምሬትስ ሞል ወዳረፍኩበት ሆቴል እንድሄድ ያደረገኝ ወጣት ነው።

በአጠቃላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለንግድና ጉብኝት በተደጋጋሚ ወደ ዱባይ መለስ ቀላስ ማለታቸው የሚታወቅ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ባለሀብቶች ቀልባቸውን በዱባይ ላይ እንደጣሉ ይነገራል። ከንግድ ተሳትፏቸው ባሻገር ቤት በመግዛት ዱባይን ኹለተኛ ቤታቸው ማድረጋቸው ካነጋገርኳቸው ሰዎች ለመረዳት ችያለሁ።

የዱባይ ድንቃድንቅ መስህቦች

በዚሁ ስለዱባይ ድንቃድንቅ መስህቦች ላንሳ። ከዱባይ ድንቃ ድንቅ መስህቦች መካከል የቱን አንስቶ የቱን መጣል እንደሚቻል ባላውቅም፤ የእኔን ቀልብ የሳቡትን በአጭር ባጭሩ አስቃኛለሁ።

ዱባይ ከምትታወቅባቸው መስኮች መካከል ንግድ አንዱ ሲሆን በዚህም ምክንያት በዓለም በስፋታቸው የሚታወቁ ትላልቅ ሞሎች ይገኙባታል። እቃ በርካሽ የሚገኝባቸውና ኢትዮጵያዊያን ያዘወትሯቸዋል ከሚባሉት ዊንፒ የሚገኙ ሱቆች፣ ድሪም ላንድ እና ዴይ ቱ ዴይ ከሚባሉት ውጪ እጅግ በጣም ግዙፍ ከሆኑት የንግድ ሕንጻዎች መካከል ኤምሬትስ እና ዱባይ ሞል የሚባሉት ተጠቃሾች ናቸው።

ኤምሬትስ የሚባለው ሞል ከ630 በላይ መደብሮችን፣ 7 ሺሕ 900 መኪና ማስተናገድ የሚችል ማቆሚያ ያለው እንዲሁም ከመቶ በላይ ሬስቶራንት በውስጡ የያዘ ግዙፍ ሕንጻ ነው። በዚህ ተገርመው እንዳያበቁ፣ ዱባይ ሞል በዓለማችን ከሚገኙ እጅግ ግዙፍ የንግድ ሞሎች መካከል አንዱ ሲሆን ከአንድ ሺሕ 200 በላይ መደብሮች፣ ከ14 ሺሕ በላይ መኪኖችን ሊያቆም የሚያስችል ቦታ አለው።

ሌላው ዱባይ ሞል ላይ ሆነው በትይዩ የሚመለከቱት በዓለም ረጅሙ ሕንጻ በመባል የሚታወቀው ቡርጅ ካሊፋሕ ሲሆን ርዝመቱም 830 ሜትር ነው። ከዱባይ ሞል ባለግርማ ሞገሱን ረጅም ሕንጻ በቅርብ ርቀት የሚታይ ሲሆን በሞሉ አንደኝው ጥግ በየዕለቱ ማምሻውን ዐሥራ ኹለት ሰዓት ላይ በኅበረ ቀለማት የተሸለመና በሙዚቃ የታጀበ፣ ከሙዚቃው ፍሰት ጋር አብሮ በስልት የሚንቀሳቀስ የውሃ ፏፏቴ (የውሃ ትርዒት) የሚለቀቅ ሲሆን የብዙዎችን ቀልብ ሰቅዞ ይይዛል። ውሃው የሚስፈነጠርበት ርዝመት አጃኢብ ማሰኘት ብቻ ሳይሆን አፍዝዞ ያስቀራል።

ከዚሁ ከጉደኛው ዱባይ ሞል ሳንወጣ፣ በክፍለ አኅጉሩ ትልቁ ዲጅታል የጥበብ ማዕከል የሆነውን “Infinity des Lumires” ይገኛል። የዲጅታል ጥበብ ማዕከሉ <መጻኢው ጥብበ በመጪዋ ከተማ ውስጥ> (Art of the future, In the city of the future) የሚል መሪ ቃል ያለው ሲሆን፣ የጠፈር ምርምር ትዕይንት፣ የሥርዓተ ፀሐይ ድንቅ ዑደት እና የአጽናፈ ሰማይ ወሰን አልባነት በአካል ቦታው ላይ ያሉ እስኪመስልዎ ድረስ በአዲስ የፈጠራ ዲዛይን፣ ቴክኖሎጂ፣ ጥበብ እና መስተንግዶ በተለዋዋጭ ውሕደት አማካኝነት አጃኢብ በሚያስብል ስሜት ይመለከታሉ፣ ይመሰጣሉ፣ ያደንቃሉ ብሎም ይዝናናሉ። አጃኢብ ብቻ!

በዘንባባ ዛፍ ቅርጽ የተሠራው የሰው ልጅን ዕምቅ ርዕይና ችሎታ እስከምን ድረስ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳየው በአምስት ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ዙሪያ ሰው ሠራሽ ሐይቅ በመፍጠርና አስደማሚ የሥነ ሕንጻ ጥበብ ውጤት የሆኑ ቅንጡ መኖሪያ ቤቶችና ሕንጻዎች የተካተቱበት ፓም ጁሜራሕ (Palm Jumeirah) አንዱ የዱባይ ድንቅ መስህብ ነው። ፓም ጁሜራሕ ጥበብ፣ ዕውቀት እና ርዕይ ተጣምረው ተዓምር የፈጠሩበት የሰው ልጅ ምጡቅ የአእምሮ ውጤት ማሳያ ተምሳሌት ይመስለኛል።

ሌላው ዱባይ መጠሪያዋ የሆነው ወርቅ በብዛት፣ በዓይነትና በጥራት የሚገኝባት ከተማ መሆኗን ለማመልከት ‹‹የወርቅ ከተማ›› በሚል ቅጽል ትታወቃለች። በዓለም ትልቁ የወርቅ ገበያ የሚገኘው ዱባይ ሲሆን መጠሪያውም የወርቅ ሱቅ (Gold Souk) ይባላል። ፒያሳ የሚገኙትን የወርቅ ሱቆች ለማነጻጸር ከሞከሩ ተሳስተዋል፤ ምክንያቱም ያለምንም ማጋነን አይጥ የዝሆን ያክል ግዙፍ ነች እንደማለት ይሆናልና!

ወርቅን የማውቀው ለጣት ቀለበት፣ ለአንገት ሀብል፣ ለጆሮ ጉትቻ፣ ለእግር አልቦ ሲሆን ግፋ ቢል ዘመነኞች በአፍንጫው፣ በከንፈሮቻቸው፣ በእንብርታቸው ወይም በተለያዩ የአካል ክፍሎቻቸው ላይ በማስቀመጥ ሲያጌጡበት ነው። ዱባይ ወርቅ ሱቆች ውስጥ ያየኋቸው ወርቆች ግን ልብስ ሆነው ነው። የወርቅ ልብስ!

በዱባይ የወርቅ ገበያ ጥራት ያላቸው 18፣ 22 እና 24 ካራት ወርቅ በብዛትና በዓይነት የሚገኙ ሲሆን በግራም እንደየካራቱ ልዩነት በአማካኝ ከብር 2800 እስከ 3150 ይሸጣል። ወርቅ ለመግዛት የመደራደር ብቃትም እንደሚጠይቅ አስጎብኚያችን ነግሮኛል። ሌላው ከወርቅ ጋር በተያያዘ ድባይ የምትነሳው፣ በዲራ የወርቅ ሱቅ የሚገኘውና ለጎብኚዎች ዕይታ የቀረበው ባለ 21 ካራት ቀለበት ክብደቱ 64 ኪሎግራም ሲመዝን በ5.1 ኪሎግራም የከበሩ ድንጋዮች የተሞላ ነው። ይህ ‹ናጃማት ታይባ› ወይም የታይባ ኮከብ በመባል የሚታወቀው የወርቅ ቀለበት ዋጋው 3 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ ተገምቷል። ልብ ያድርጉ! ይህ ትልቅ የወርቅ ቀለበት በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ጊነስ ላይ ሰፍሯል።

ከዱባይ በስተሰሜን ምሥራቅ 30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሌላው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ግዛት ሻርጃሕ ይባላል። ሻርጃሕ የሄድነው የበረሃ (የምድረ በዳ) ላይ የመኪና ‹ግልቢያ› በአሸዋ በተሞሉ ተራሮች ላይ ለማድረግ ነው። የአሸዋ ተራሮቹ መጨረሻ ያላቸው አይመስሉም፤ የሰማይ ጥግ ድረስ ደረታቸውን ገልጥጠው ተንሰራፍተዋል፤ ከአድማስ እስከ አድማስ።

ይህ የተፈጥሮን ተግዳሮት ወደ መልካም አጋጣሚነት የመለወጥ አንድ ተምሳሌት ይመስለኛል። ተፈጥሮን የማማረር ሳይሆን፤ ተፈጥሮ ላይ የመሥራት! ይህ የመኪና ላይ ግልቢያ በጀብድ የተሞላ ነው። እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ቶዮታ ላንድ ክሩዘር መኪኖች የጎማቸው አየር እንዲያጎል ተደርጎ እንደፈለጉ በአሸዋው ተራራ ላይ ሲጋልቡ፣ ወደጎን አዘንብለው ግማሹ አካላቸው በአሸዋ ተውጦና ሰጥሞ በፍጥነት ሲበሩ ነብስን ከስጋ ምንጥቅ ያደርጋሉ፤ ለሕይወትዎ ይሰጋሉ።

እንደመውጫ

አስደማሚውን የሰው ልጅ የአእምሮ ብስለት ውጤት የሆነውን ፓም ጁሜራሕን በዓይንዎ በብረቱ ለማየትና ዱባይን በምልዓት ለመመልከት ባለ 54 ወለል ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ‹ዘ ፓም ታወር› (The Palm Tower) የተሻለው ምርጫ ነው። የፎቁ አናት ላይ ከመውጣትዎ በፊት 52ኛው ወለል ላይ ኢትዮጵያዊያንን የሚያኮራ፣ በራስ መተማመን ስሜታችንን የሚጨምርና ራሳችንን ቀና እንድናደርግ የሚያደርገንን ቡን ኮፊ ያገኙታል። የኦሪት የማይጠገብ ፈገግታና ልዩ መስተንግዶ ደግሞ ተጨማሪ ጉልበት ይሰጣል። ሌላም የቡን ኮፊ ቅርንጫፍ በዚሁ ሕንጻ የታችኛው ወለል ላይ ይገኛል። እንደፍላጎትዎ ቡናዎን እየተጎነጩ፣ አድንቀው የማይጨርሱትን የሰው ልጅ ጥበብ የሆነውን የፓም ጁሜራን ዙሪያ ገባውን በዐይንዎ ይቃኛሉ። በተመሳሳይ በተሻለ ዕይታ በሕንጻው አናት ላይ በመውጣት የዐይን ረሃብዎን ይወጣሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here