የደራስያን ማኅበር የሥልጠና ጉዞ

0
872

የሺእመቤት ካሳ ትባላለች። ገጣሚና ደራሲ ናት። እድሜዋና በራስዋ ላይ የደፋችው ነጭ ሀር የመሰለ ፀጉር፤ ከዛም በላቀ ደግሞ ሥራዋ አንቱ ሊያስብላት ቢገባም፤ በዙሪያዋ ያሉ ሁሉ ‹እትዬ የሺ› ሲሉ እንደ ቅርብ ሰው በአንቺታ ይጠሯታል። ደግሞም የደራሲና የጥበብ ሰው አጠራር ወጉ አይደለምና አዲስ ማለዳም በአክብሮት በአንቺታ እየጠራች ከገጣሚዋና ደራሲዋ ጋር አጭር ቆይታን አድርጋለች።

እትዬ የሺ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በየዓመቱ በሚያዘጋጀው ሥልጠና የሦስተኛ ዙር ሠልጣኝ ነበረች። አሁን ስምንተኛ ዙር ላይ የደረሰው ይኸው ሥልጠና፣ ቀዝቃዛና ዝናባማውን የክረምት ሰሞን ጠብቆ፣ እንደ እሳት ዳር ጨዋታ በሥነ ጽሑፍ ዙሪያ የሚያሰባስብ መርሐ ግብር ነው። በዚህም የሥልጠና መርሐ ግብር የተለያዩ የጽሑፍና ተግባራዊ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ።

ታድያ መለስ ብላ የተሳተፈችበትን ይህን መሰሉን ሥልጠና ስታስታውስ፣ ከሥነ ጽሑፍ ሰዎች ያገኘቻቸው ተሞክሮዎችና ልምዶች፣ እንዲሁም የተሰጡ ሥልጠናዎች ላይ የተነሱ ነጥቦች ምን ያህል ለሥነ ጽሑፍ ሥራዋ እንዳገዟት ትጠቅሳለች። ያንንም ተከትሎ ‹አመሻሽ› የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሐፏን እንዲሁም ‹አባባ ትልቁ እና ሌሎች ትምህርታዊ ተረቶች› እና ‹አለላ እና ሌሎች ትምህርታዊ ተረቶች› የተሰኙ የልጆች መጻሕፍት እንድታዘጋጅ እንደረዳት ትናገራለች።

በእውቀት ደረጃም አጻጻፍ ላይ ልዩነቶችን እንዴት አስተካክሎ መጻፍ እንደሚገባ ተምሬአለሁ ብላለች። በዚሁ የሥልጠና አጋጣሚ ካገኘቻቸው ደራስያን መካከል ከኃይለመለኮት መዋዕል ያገኘችው ሐሳብ ደግሞ አበርትቷታል። ይህንንም ስታስታውስ እንዲህ አለች፤ <<ደራሲ ኃይለመለኮት ‘የደረቀ እንጨት እና የጠነከረ ዛፍ ብዙ ፍሬ ይሰጣል’ ብሎ ሞራል ሰጥኝ። ይህም ወደ ድርሰቱ ዘልቄ እንድገባ ያደረገኝ ነው።>>

ሥልጠናው የሥነ ጽሑፍ ፍቅር ያላቸው ወጣትም ሆኑ እንደ እትዬ የሺ ያሉ በእድሜ ተለቅ ያሉ ሥነ ጽሑፍ ወዳድ ሰዎች፤ ከአንጋፎቹ ጋር እንዲገናኙም እድልን የፈጠረም ነው። እንደ እትዬ የሺ ገለጻ ደግሞ፣ እንደውም በዘርፉ የሚሠሩ ጓደኞችን ለመተዋወቅና ለማግኘት አጋጣሚም እንደሆነ ነው።

ለዚህም እርሷም የተሳተፈችበት የሦስተኛ ዙር ሥልጠና ላይ የነበሩ ሠልጣኞች፣ ከሥልጠናው መጠናቀቅ በኋላ በጋራ የመሠረቱት ‹ፍኖተ ጥበብ› የተሰኘው ቡድን ማሳያ ነው ብላለች። በዚህ ቡድን ከሥልጠናው መጠናቀቅ በኋላም ሠልጣኞች ሳይለያዩ፣ በየ15 ቀናት በምኒልክ ትምህርት ቤት እየተገናኙ፣ ሥራዎቻቸውን በማቅረብና እርስ በእርስ በመማማር ጥሩ ጊዜ ማሳለፋቸውን የሺእመቤት መለስ ብላ አስታውሳለች።

ይህ ሥልጠና አሁን ስምንተኛ ዙር ላይ ደርሷል። በየዓመቱም ለጀማሪ እና ለነባር ደራስያን፣ እንደ እትዬ የሺ ማምሻ ላይ መጣን ከሚሉት ጀምሮ ገና በለጋነት የሚገኙ ይሳተፉበታል። ተሳትፈውም በድምሩ የድርሰት አጻጻፍ ክህሎትን ማዳበር የሚያስችላቸውን እንደ እርሾ የሆነ ሥልጠናን ያገኛሉ።

በዚህም መሠረት በ2014 ለኹለት ወራት በቆየው ሥልጠና ከሰማንያ በላይ ሠልጣኞች ተሳትፈዋል። በዚህኛው ሥልጠና ላይ ደራሲዎቹ ኃይለመለኮት መዋዕል፣ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ አበረ አዳሙ እንዲሁም ሰዓሊና መምህር አገኘሁ አዳነ፣ የሙዚቃ ባለሞያ ሰርጸ ፍሬስብሐት እና የቴአትር መምህርት ትዕግስት ዓለማየሁ ሥልጠና ከሰጡት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ገዛኸኝ ሀብቴ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባልና የሥልጠናው ዋና አስተባባሪ ነው። የአሁኑን ስምንተኛውን ዙር ጨምሮ በተለያየ ዓመት እነዚህን ሥልጠናዎች በማስተባበር አገልግሏል። ገዛኸኝ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ መለስ ብሎ ሲያስታውስ፣ ደራስያን ማኅበር ሥልጠናውን መስጠት ከመጀመሩ በፊት የተለያዩ እቅዶች ይዞ እንደነበር ያነሳል። ሥነ ጽሑፍ ላይ በዋናነት አተኩሮ መሥራት የሚለው የበለጠውን ድምጽ አግኝቶ ሥልጠና መሰጠት እንደተጀመረም ጠቅሷል።

ታድያ እስከ ቅርብ ዓመት ድረስ ሠልጣኞች በቁጥር ከሀምሳ የዘለሉ አልነበሩም። ገዛኸኝ እንዳለው ይህ የሆነው በአንድ በኩል በውስን ሠልጣኞች የመማር ማስተማሩን ሥራ ቅልጥፍ ለማድርግ በማሰብ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ማስታወቂያው በስፋት ይሠራ የነበረው በማኅበሩ የራድዮ ፕሮግራም በሆነው <የጥበብ እልፍኝ> ብቻ ነበር። በዚህኛው በ8ኛው ዙር ሥልጠና ግን ከዛም ባሻገር ማስታወቂያው በስፋት ተሰራጭቶ፣ ብዙ ፍላጎትም እንዳለ ታውቆ የሠልጣኞች ቁጥር ሊጨምር ችሏል።

በ2014 የክረምት ሥልጠና ላይ ታድያ ከወትሮው በተለየ የነበረው ‹የወርክሾፕ› ይዘት ያለው የሥልጠና ዓይነት መካታቱ ነው። ከዛ በተጓዳኝ እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ ድርሰት አጻጻፍ፣ አጭር ልብወለድ፣ ኢ ልብወለድ፣ ትርጉም፣ ሥነ ግጥም፣ ቴአትር አጻጻፍ፣ ሂስና የሥነ ጽሑፍ ታሪክ በሥልጠናው ከተካተቱ መካከል ናቸው። ሥነ ጽሑፍን ከሙዚቃ እንዲሁም ከስዕል ጥበብ እና ከሳይንስ ጋር የሚያተያይ ሥልጠናንም ሠልጣኞች አግኝተዋል። የግዕዝ እና የዐጀሚ ሥነ ጽሑፍ ደግሞ በዚህኛው ሥልጠና በልዩነት የተካተቱ ናቸው።

ገዛኸኝ ሥልጠናው ሲጀምር የነበረበትንና አሁን የደረሰበትን ደረጃ ሲያነጻጽር፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥና መሻሻል እንዳለ ሳይጠቅስ አልቀረም። ማኅበሩ በየጊዜው ያሉ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን መነሻ በማድረግ ያሻሻላቸውና እያደር የቀየራቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉም ጠቁሟል። በተለይም የሥልጠናውን ዓላማ ተረድተውና ፍሬውን ዐይተው በተባባሪነት የሚያገለግሉ አሠልጣኝ መምህራንና የሥነ ጽሑፍ ሰዎችም መበራከታቸውን አንስቷል።

‹ከተማሪዎቻችሁ ምን ፍሬስ አገኛችሁ? እንደጠበቃችሁት እየሆነ ነው ወይ?› ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃለች። ደራስያን ማኅበር በዚህ ሥልጠና ያሰበውን እያሳካ መሆኑን ነው ገዛኸኝ ያስታወቀው። በቁጥርም ሲያስቀምጥ በድምሩ ከ15 በላይ ተማሪዎቻቸው ወይም ሠልጣኞቻቸው የነበሩ ሰዎች አንድ እና ከአንድ በላይ መጽሐፍ አሳትመው ለንባብ አቅርበዋል ብሏል።

የንባብ ባህል በሚታማበትና አዳዲስ የሥነጽሑፍ ሥራዎች አስፈላጊነታቸው በማያጠራጥርበት በዚህ ወቅት፣ እንዲህ ያለው ሥልጠና የሚኖረው ድርሻ ቀላል እንዳይደለ ብዙዎች ይስማማሉ። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርም በዚህ ጉዳይ ተነሳሽነቱን ወስዶ ቀጣይነቱም ላይ መትጋቱን በርካቶች አድንቀዋል።

እትዬ የሺ በአንድ በኩል ደራሲያን በየእለቱ ተማሪና አዲስ ነገርን ለማወቅ ጉጉ ብሎም ሁሉን በትንሽ በትንሽ ቢሆንም ማወቅ ያለበት በመሆኑ፣ ሥልጣናውን ጀማሪም ሆኑ ነባር ደራስያንን የሚያግዝ ነው ብላለች። እንደውም ደረጃውን ከፍ በማድረግ፣ ሥልጠናው የሚሰጥበትን ጊዜም በማራዘም ማኅበሩ ከዚህ የላቅ ውጤታማ ሥራ መሥራት፣ በቁጥርም በርከት ያሉ ደራሲዎችን ማብቃት ይችላል ባይ ናት።

<<ቀመስኩ እንጂ ጠገብኩ አልልም>> የምትለው እትዬ የሺ፣ የኹለት ወር ሥልጠና ምጥን ብሎ ጥፍጥ ይበል እንጂ በቂ አይደለም ብላለች። ከዛም ባሻገር አንድ ሰው ደግጋሞ በየዓመቱ ልሠልጥን ቢልና ለዛም አቅሙ ካለው፣ ሁሌም አዲስ ነገር የሚገኝበት ስለመሆኑ ሳትጠቅስ አልቀረችም።

<<ቦታው አሁን ካለሁበት አንጻር ርቀት ስላለውሁ ቀረሁ እንጂ ደጋግሜ ብማር ደስ ባለኝ ነበር። እንደው በየቦታው መስጠት ቢቻል፣ አንድ ሰው ደግሞ ደጋግሞ መማር ቢችል ብዙ ነገር ያገኝበታል።>> ስትልም ሐሳቧንም ገልጻለች።

ወደፊትስ?

ማኅበሩ የእትዬ የሺ ዓይነት ሐሳብ ገብቶታል። እናም ሥልጠናው የሚሰጥበት ጊዜና የጊዜ ርዝመት ላይ ለወደፊት የያዛቸው እቅዶች እንዳሉት የሥልጠናው ዋና አስተባባሪ ገዛኸኝ ተናግሯል። በዚህም መሠረት ሥልጠናውን በዓመት ሦስት ጊዜ ለመስጠት ወይም የስድስት ወር ሥልጠና የማድረግ እቅድ አለ፤ ይህም ውሳኔና የሁኔታዎችን መመቻቸት የሚጠብቅ ነው።

ከዚህም በተጓዳኝ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብቻ ተወስኖ መቆየቱ ቀርቶ፣ በተለያዩ የክልል ከተሞችም እንዲኖር ለማስቻል ንግግሮች እየተደረጉ ነው ተብሏል።

ገዛኸኝ አያይዞም ማኅበሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠንካራ እና ደካማ ጎኑን እያየ፤ ጥንካሬውን እያበረታና ድክመቱን እያሻሻለ ለዛሬ መድረሱን ያነሳል። ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ሳይጠቅስ አላለፈም። ሥራውን ለማስኬድ ከገንዘብ አንጻር ብዙ ወጪ እንዳለውና ነገር ግን እንዳይቋረጥና እንዲቀጥል አሠልጣኝ ሆነው የተሰየሙ መምህራን እገዛና ተባባሪነት በእጅጉ ወሳኝ እንደነበር መስክሯል።

እንደውም ከምንም በላይ ሥልጠናው ሳይቋረጥ በተከታታይ 8ኛ ዙር እንዲደርስና እንዲቀጥል፣ ትልቅ አቅም ያላቸው መምህራን በእጅጉ አግዘዋል። ጊዜና ጉልበታቸው፣ እንዲሁም ልምድ፣ እውቀትና ችሎታቸውን ከማካፈልም አልሰሰቱም። እናም የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ለዚህ ትልቅ አክብሮት አለው ሲልም ገዛኸኝ አስታውቋል።

በ2014 የነበረው 8ኛ ዙር ሥልጠና የሰመረ እንዲሆን አብላጫ እና ግንባር ቀደም የተባባሪነት ድርሻን የወሰደው ሰላም ኢትዮጵያ መሆኑን ጠቅሷል። በመቀጠልም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) እንዲሁም የኢትዮጵያ የሳይንሶች አካዳሚ በየበኩላቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ተባባሪዎች ናቸው።

ባሳለፍነው ሳምንት መስከረም 7 ቀን 2015 ሥልጠናውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ሠልጣኞች በወመዘክር አዳራሽ ተመርቀዋል፣ የምስክር ወረቅት ተበርክቶላቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here