• አንድ ጣሳ ጤፍ 150 ብር እየተሸጠ ነው ተብሏል
በሰሜኑ ጦርነት ቀጠና ውስጥ ባሉ ቦታዎች የተለያዩ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ከነበረበት በአራት እጥፍ በላይ መጨመሩን አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎቹ አንደበት ሰምታለች።
በድርድር ይፈታል የሚል ተስፋ ተሰንቆበት የነበረው የሰሜኑ ጦርነት ከነሐሴ 18/2014 ጀምሮ ለሦስተኛ ዙር መቀስቀሱን ተከትሎ፣ በጦርነቱ ቀጠና ስር በሚገኙ አካባቢዎች ገበያው ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል ተብሏል።
በሦስተኛው ዙር ጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር በኩል እና በራያ ቆቦ ወረዳ ግራና ቀኝ እንዲሁም በአፋር ክልል በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች ናቸው። በተለይም በራያ ቆቦ ከተማ ሦስተኛው ዙር ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት የነበረው የምግብ ፍጆታ ዋጋ አሁን እስከ አራት እጥፍ ጨምሯል ብለዋል ነዋሪዎቹ።
በሰላሙ ጊዜ ከ50 እስከ 60 ብር ሲሸጥ የነበረው አንድ ጣሳ ጤፍ 150 ብር እየተሸጠ መሆኑም ተጠቅሷል። ዳግም ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህም የዋጋ ጭማሪው እየባሰ መሆኑ የተነሳ ሲሆን፤ ‹‹ከኹለት ሳምንት በፊት አንድ ጣሳ ጤፍ 120 ብር ሲሸጥ ነበር። አሁን ግን ወደ 150 አሻቅቧል።›› ሲሉ ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።
እንዲሁም በሌላ ጊዜ በጣም ተወደደ ሲባል ከ40 ብር አልፎ የማያውቀው አንድ ጣሳ ማሽላ ሰሞኑን ከ80 እስከ 100 ብር እየተሸጠ ነው። ክክ ሌላኛው የዋጋ ጭማሪ የታየበት የምግብ ፍጆታ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ አንደገለጹት ከዚህ ቀደም 70 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ኪሎ ክክ 270 ብር ገብቷል። አንድ ኪሎ ምስር ወደ 300 ብር መናሩም ተጠቅሷል። በሰላሙ ጊዜ ሲሸጥ የነበረው እስከ 90 ብር ነበር።
ሽንኩርት ከመጥፋቱ የተነሳ በፍሬ የሚሸጥ መሆኑን ነዋሪዎቹ የገለጹ ሲሆን፤ የአምስት ፍሬ ሽንኩርት ዋጋም 100 ብር ነው። በተለይም የሽኩርት ዋጋ በአራት እጥፍ ጭማሪ ዐሳይቷል ነው የተባለው።
የዋጋ ማሻቀብ ያሳየው ሌላው ነገር ዘይት መሆኑ ተመላክቷል። በሌላ ወቅት 500 ብር ሲሸጥ የነበረ ሦስት ሊትር ዘይት ሰሞኑን ወደ 1 ሺሕ 500 ብር እንዳሻቀበም ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። የትግራይ ክልል ተወላጆችም አስቤዛ የሚሸምቱት በተለይም በራያ ቆቦ ከተማ መሆኑ ተጠቁሟል።
በሰሜን ጎንደር በኩል በጦርነቱ ቀጠና ስር ባሉ የተለያዩ አካባቢዎችም ብዙ የተጋነነ ባይሆንም የዋጋ ጭማሪ መከሰቱ ተነግሯል። በሰሜን ጎንደር በኩል ያለው ኹኔታ በተመለከተ የተገኘው ምላሽ በይበልጥ እየተስተዋለ ያለው የተኩስ ልውውጥ መሆኑ ተብራርቷል።
በአማራ ክልል ደጋማውና ቆላማው ማለትም በተለይም በራያ ቆቦ ግራና ቀኝ የሚገኙ ቦታዎች የተኩስ ልውውጡ እምብዛም ነው የተባለ ሲሆን፤ ነዋሪዎች ግን እየታገቱ መሆኑ ተሰምቷል።
ነዋሪዎቹ ባላቸው መረጃ መሠረት፤ ሦስተኛው ዙር ጦርነት ከተጀመረ ከነሐሴ 18/2014 ጀምሮ ከ280 የሚልቁ ሰዎች በሕወሓት ታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል። ከእነዚህ መካከል ወደ 80 የሚሆኑት ታጋቾች መሣሪያ አምጡ ተብለው የሌላቸው ስለሆነ ነው ይላሉ ምንጮች።
ከ17 የሚልቁ ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት ድሮን መገደላቸውን ነዋሪዎቹ አስታውሰዋል። ሰላማዊ ሰዎቹ ለወዳጅ ዘመድ ስልክ ለመደወል ከዞብልና ከቆቦ ከተማ ተነስተው በራያ ቆቦ ከተማ በሚገኘው ሆስፒታል አካባቢ ተሰባስበው የነበሩ ሲሆን፤ ከሦስት ሳምንት በፊት በመንግሥት ድሮን መገደላቸውን ከነዋሪዎቹ ማረጋገጥ ተችሏል።
በተያያዘም በኹለት ቀን ሰባት ሺሕ መሣሪያ አምጡ በሚል ሕወሓት መመሪያ በቆቦ ከተማ ያወረደ ሲሆን፤ ‹‹የለንም›› ያሉ ከ13 የሚልቁ ወጣቶች በታጣቂዎች ተወስደው ያሉበት አይታወቅም ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015


