ለእንግሊዝኛና አረብኛ ቋንቋ ትምህርት እስከ 160 ሺሕ ብር እየተጠየቁ መሆኑን በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ በሳዑዲ በዜጋ ተኮር ዲፖሎማሲ ሥራ አስተባባሪነት የተሰማሩ ምንጭ እንደተናገሩት፤ ለትምህርቱ 160 ሺሕ ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ነው።
የእንግሊዝኛና አረብና ቋንቋ መማሩ ለሥራቸው አስፈላጊ መሆኑን፣ ነገር ግን ሙሉ ክፍያውን በአንድ ጊዜ መክፍል ባለመቻላቸው የቋንቋ ትምህርቱን እንዳይማሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል። 160 ሺሕ ብር ክፍያ የሚጠየቀውም ለ9 ወር ትምህርት ብቻ ሲሆን፤ አንድ ጊዜ ጠቅልሎ ያልከፈለም መማር አይችልም ብለዋል።
ይህ የሚሆነው በሳዑዲ አራቢያ ጂዛን ክልል ውስጥ ‹‹well street English school›› (ዌል እስትሪት ኢንግሊሽ ስኩል) መሆኑን ጠቁመዋል። ክፍያው ለሳዑዲ ተወላጆችና ለሌላ አገር ዜጎች የተለያየ መሆንና አለመሆኑን በተመለከተ አዲስ ማለዳ ኹለት ዓይነት መረጃ አግኝታለች። ዜጋ ተኮር ዲፖሎማሲ አስተባባሪው ‹‹ክፍያው ለሳዑዲ ተወላጅና ለውጩም ሰው እኩል ነው›› ሲሉ፣ ሌላኛው የአዲስ ማለዳ ምንጭ ደግሞ ለሳዑዲ ተወላጆች ክፍያው የሚቀንስ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
‹‹ክፍያው ለሳዑዲ ተወላጆች በምስጢር ኢትዮጵዊያን ከሚከፍሉት 30 በመቶ ቅናሽ እንደሚከፈል አውቃለሁ። ተቋሙ ግን ለኹሉም እኩል ነው ብሎ ይናገራል።›› ሲሉም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በሳዑዲ አረቢያ ታስረው ከኖሩ ዜጎች በየቀኑ አንድ ሺሕ የሚሆኑ ወደ አገር ቤት እየገቡ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ ላምበረት አካባቢ በሚገኝ መጠለያ እንደሚያርፉ ይታወቃል። ሆኖም ግን ከተመላሾቹ መካከል ቤተሰቦቻቸው በትግራይ ክልል የሚኖሩት በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት ቡድን መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ወደ ቤታቸው መመለስ ባለመቻላቸው ዳግም ወደ ሳዑዲ እየተሰደዱ ነው ተብሏል።
የአፋር፤ የትግራይ እንዲሁም የአማራ ክልል ወጣቶች ተመልሰው ወደ ሳዑዲ አረብያ ማቅናታቸውና በድጋሚ በእስር ቤት ለመግባት ተገደው እየተንገላቱ መሆናቸው ተሰምቷል።
በሳዑዲ ድንበር (የመን) አካባቢ የሚኖሩ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ ‹‹ለምሳሌ 10 ወር ታስሮ የተሸኘ ሰው ዞሮ መጥቶ ሳዑዲ እስር ቤት እንዳለ አውቃለሁ›› ሲሉም ተናግረዋል። ተመልሰው ወደ ሳዑዲ ያቀኑ በርካታ ሰዎች በየመንና በሳዑዲ ድንበር መግቢያ (መሿለኪያ) በርሃ ላይ በርሃብ እየተሰቃዩ መሆኑም ተጠቅሷል።
በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ ለመግባት የሚሞክሩ ሰዎች እየሞቱ የአሞራ ራት እየሆኑ ነው የተባለ ሲሆን፤ ዕድል ቀንቷቸው ለመሻገር የበቁ ደግሞ ሳዑዲ ለመግባት ለአንድ ሰው ከ80 እስከ 100 ሺሕ ብር ለደላሎች ለመክፈል ይገደዳሉ።
‹‹ለደላላ በሚከፍሉት ብር ለምን አይሠሩም እንዳይባል ብር የላቸውም። ግን ድፍረትን ይዘው የመን ሲደርሱ ሳዑዲ ለሚገኝ ዘመድ ይደውላሉ። ሳያማክሩ ከተፍ ስለሚሉ ሥራቸው ያበሳጫል። በደላሎች እየተሰቃዩ ይደውላሉ። መጨከን ስለሚከብድ ከየትም መጥቶ ይከፈላል። እድል ካልቀናቸው ደግሞ ወዲያው ፖሊስ ይይዛቸውና መታሰር ይመጣል። በእስር ቤት ደግሞ መሞትም አለ።›› ሲሉ አስተባባሪ ነኝ ያሉት ግለሰብ ጠቅሰዋል።
በተለይም አሁን አሁን ዳግም የሚሰደዱ ሰዎች በመበራከታቸው የሟቾች ቁጥር ከመጨመሩ የተነሳ እስከዛሬ ወዳጅ ዘመድ ‹‹አለሁ ብሎ›› ሟቾችን እንዲቀብር ተወስኖ የነበረው የቆይታ ቀን መቀነሱም ተነስቷል።
በሳዑዲ አራቢያ ጂዛን ክልል እስር ቤት የሚገኙ ሰዎች ሲታመሙ ወደ መንግሥት ሆስፒታል፤ ታክመው ከዳኑ ወደ እስር ቤት ይመለሱ ነበር። ከሞቱ ደግሞ ‹ሬሳ እወስዳለሁ› የሚል አካል ካለ እስከ 21 ቀን ድረስ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን፤ አሁን አሁን የሬሳ ማቆያ ማዕከላት እየሞሉ ሳምንት ሳይሆናቸው የሚቀበሩ ሰዎችም አሉ ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015



