ሲሚንቶ ከማከፋፈል የታገዱ ጅምላ ነጋዴዎች ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደደረሰባቸው አስታወቁ

0
1917

የጅምላ ንግድ ፍቃድ ያላቸውና ከመታገዳቸው በፊት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወኪል የነበሩ ድርጅቶች ከሥራ በመታገዳቸው ምክንያት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደደረሰባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ከወራት በፊት ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በተጻፉ ደብዳቤዎች ሲሚንቶ ሲያከፋፍሉ የነበሩ ወኪሎች ከገበያ ስርዓቱ እንዲያስወጡ በታዘዙት መሠረት፣ ከገበያ ውጪ የሆኑ ወኪሎች በተላለፈባቸው ውሳኔ መሠረት ከፍተኛ ችግር እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

የአንድ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወኪል በመሆን ለዓመታት ሲሠራ የነበረ ድርጅት ባለቤት የሆኑ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ለ20 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ አግባብ የሆነውን ክፍያ ከፍለው ነገር ግን ሲሚንቶውን ከፋብሪካ እንዳያወጡ የተጣለው እግድ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል። ይህም ለከፍተኛ ችግር እንደዳረጋቸው ገልጸው ገንዘቡን ከፋብሪካ ተመላሽ እንዳያደርጉትም ደረሰኝ እንደተቆረጠበት ተናግረዋል።

ይባስ ብሎም እስከ ጥቅምት 30/2015 በሚዘልቀው የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ጊዜ ይህ ያልተጠቀሙበት 20 ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶን ያካተተ አጠቃላይ ግብር እንድከፍል ይጠበቅብኛል የሚሉት ግለሰቡ፣ ሌላ ሥራ እንኳን እንዳልሠራ፣ የምሠራበት ገንዘብ ተይዞ ችግር ውስጥ ወድቄያለሁ ብለዋል።

መስከረም 4/2014 በወጣው አዲሱ የፋብሪካዎች የሽያጭ ተመን መሠረትም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ይሁንታን የሚሰጧቸው አካላት ሲሚንቶን ከፋብሪካዎች በመረከብ መሸጥ እንደሚችሉ ቢገለጽም፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግን ለግል ድርጅቶች ፍቃድ አልሰጠም ብለዋል። ወኪሎች ሥራ እንድናቆም ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የሲሚንቶ ዋጋ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልተመለከትንም የሚሉት ግለሰቡ፣ ከሲሚንቶ ማከፋፈል ሥራቸው ሲታገዱ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸውና በሂደት ላይ የነበሩ ግዥዎችን ለመጨረስ እንኳን ጊዜ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

በአዲሱ የሽያጭ ተመን መሠረት እንድንሠራ ፍቃድ እንዲሰጠን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን ብንጠይቅም፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወረደ የሥራ መመሪያ ምክንያት ለእናንተ ፍቃድ እንድንሰጥ አልተፈቀደልንም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ግለሰቡ ገልጸዋል። አያይዘውም በጊዜያዊነት እስከ መስከረም 30/2015 የተጣለባቸው እግድ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል እንዳላወቁ ተናግረዋል። በዚህ ከቀጠለም እንኳን የሚደርስባቸውን ግብር ለመክፈል ቤተሰባቸውን ለማስተዳደርም እንደሚቸገሩ አሳውቀዋል።

ሌላ በተመሳሳይ ዘርፍ ላይ የተሰማራ ድርጅት ያላቸው ሥማቸው እንዳይጠቀስ ያሉ ግለሰብም ሀምሳ ሺሕ ኩንታል ሲሚንቶ ለመውሰድ ለሚወክሉት ፋብሪካ በደረሰኝ ክፍያ የፈጸሙ ቢሆንም፣ ይህንን ሲሚንቶ ሳይረከቡ ከሥራ እንደታገዱ ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ለችግር ተዳርገው መኖሪያ ቤታቸውን ለመሸጥ እንደተገደዱ ጠቅሰዋል። ይህንን በማንሳትም ከሌሎች በዘርፉ ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር በመሆን ለአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ብናመለክትም እስከ መስከረም 30 ድረስ ታገሱ ከሚል የተስፋ ቃል ውጭ ተጨባጭ መልስ አላገኘንም ሲሉ ተናግረዋል።

ለመጨረሻ ጊዜ ከፋብሪካ ሲሚንቶ ተቀብለው ባከፋፈሉበት ወቅት ገበያው ላይ የሲሚንቶ ችርቻሮ ዋጋ በኩንታል 900 ብር አካባቢ እንደነበር የሚያስታውሱት ግለሰቡ፣ በተላለፈባቸው እግድ ምክንያት ወኪሎች ከሥራ ከወጡ በኋላ ግን የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ጭማሪ በማሳየት እስከ 1800 ብር እንደሚሸጥና የአቅርቦት ችግሩም መባባሱን እንደታዘቡ ገልጸዋል። በአንዳንድ ጥፋተኞች ምክንያት በአጠቃላይ የሲሚንቶ ወኪሎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ሥራችንን በአግባቡ ስንሠራ በነበርን ነጋዴዎች ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ ነውም ብለዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን መልስ ለማግኘት አዲስ ማለዳ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራዎችን ብታደርግም ሊሳካ አልቻለም።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here