ጃዋራዊ እና ዐብያዊ ሳምንት

0
616

ጥቅምት 11/2012 የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሕዝብ ተወካዮች ብቅ ብለው ከሕዝብ እንደራሴው ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር። በዚህ ወቅት ታዲያ ውች አገር ዜግነት ያላቸው እና በኢትዮጵያ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤት ሆነው በሕዝብ ዘንድ ሽብርን እና አለመረጋጋትን የሚሰብኩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና ካልሆነ ግን ለአገር ደኅንነት ሲባል መንግስት እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ አስረግጠው ተናገሩ።

ይህን ተከትሎ ማኅበራዊ ትስስር ገፁ እከሌን ማለቱ ነው፣ እከሊትን ሊነካ ፈልጎ እኮ ነው በሚል መጠቋቆም ቀኑን አገባደደ። በዛው ዕለት ምሽት ደግሞ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ባለቤትና ስራ አስፈፃሚ ጃዋር መሐመድ መንግስት ጥበቃዎቼን ሊወስድብኝ ነው እና ይህም የሆነው በእኩለ ሌሊት ስለሆነ አግባብነት የለውም እንዲህ ያደረገው አካልም ለሚደርሰው ጥፋት ኃላፊነቱን ይወስዳል የሚል ጽሑፍ በፌስቡክ እና ትዊተር ገጹ ላይ ይለጥፋል። ከዚህ ቅጽበት በኋላ ከአጥናፍ አጥናፍ ዜናዎች ተስተጋቡ ፣ በቀጣዩ ቀን ማለዳ መንገዶች በአዲስ አበባ የተወሰኑ አካባቢዎች እና በአብዛኛው የኦሮሚያ ከተሞች ተዘጉ፣ ዐብይ አሕመድን (ዶ/ር) እና ለማ መገርሳን የሚያወግዙ እንዲሁም በግልጽ የሚዘልፉ መፈክሮች በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ተስተጋቡ ፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የጃዋር መኖሪያ ቤትም ለቁጥር በሚያታክቱ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ወጣቶች ተከበበ ‹‹መንግስት ጠባቂዎችህን ቢያነሳም እኛ አለንልህ››አይነት ድጋፍ ተደረገለት። በዚህ እንቅስቃሴ ወቅት በተለይም ደግሞ በሐረርጌ አካባቢ በቅርቡ በመላው ዓለም የኢትዮጵያ ኢምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ባሉበት የተመረቀው በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የተፃፈው ‹‹መደመር›› መጽሐፍ በይፋ ሲቃጠል ተስተውሏል።

እንዲህ አይነት ሐሳቦች በተስተናገዱባቸው አካባቢዎችም ታዲያ አይሆንም ‹‹ዐብይን የነካ በዓይኔ መጣ ያለ ሌላ ቡድን ደግሞ በተቃራኒው ጠርዝ በመቆም ወደ ለየለት ፍጥጫ የተገባበት ሳምንት ነበር። የማኅበራዊ ትስስር ገጾችም ጎራ ለይተው እንዱን ሲያሞካሹ ሌላውን ደግሞ አፈር ሲያስግጡት ሰንብተዋል። አንዳንዶቹ ‹‹ጎሽ አበጀህ፤ ጃዋር አንደኛ፤ ጀግና›› ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ከአብይ ጎን ነኝ ›› የሚል እንቅስቃሴ የጀመሩ ቡድኖች ደግሞ ‹‹ምነው መንግስት ግን በዚህ ሰውየ ላይ እርምጃ ቢወስድ›› የሚል አስተያየታቸውን ሲያስተጋቡ እና ዘለፋ በቀላቀለ ንግግርም ጃዋርን ሲያወግዙ ሰንብተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here