10ቱ ከፍተኛ የቻይና ባለዕዳ የአፍሪካ አገራት

0
646

ምንጭ:ዘ አፍሪካን ኤክስፖነንት (2018)

ልክ የዛሬ ዓመት በዚህ ወር ዘ አፍሪካን ኤክስፖነንት በድረ ገጹ ባስነበበው መረጃ መሠረት ቻይና ገንዘቧንና ዓይኗን አፍሪካ ላይ እንደጣለች በግልጽ የሚያመለክቱ ቁጥሮች ቀርበዋል። ቻይናም ብትሆን የአፍሪካን እዳ ውስጥ መግባት የምትፈልገው ይመስል፤ ወርና ዓመት ጠብቃ ‹‹መልሱልኝ›› ከማለት ይልቅ፤ ኪሴ ኪሳችሁ ነው ብላ በየቀኑ አዳዲስ ብድሮችን እየሰጠች ዕዳዎችንም እያሸከመች ትገኛለች።

በዚህ መሠረት አንጎላ ከፍተኛ የቻይና ዕዳ ያለባት አፍሪካዊት አገር ሆና ተመዝግባለች። በዚህም መሠረት በአፍሪካ የነዳጅ ዘይት አምራችነት በኹለተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ይህቺው አንጎላ፤ በዚህ ከምታገኘው ገቢ እዳዋን ለመሸፈን ጥረት እያደረገች ነው።

ከአንጎላ ቀጥሎ ኢትዮጵያ በኹለተኛነት ስትመዘገብ ጎረቤት ኬንያ በሦስተኛ ባለዕዳነት ተቀምጣለች። በእነዚህ አገራት በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙት ብድሩ በብዛት ለመንገድ ግንባታ የዋለ ነው፤ እንደ አፍሪካን ኤክስፖነንት ዘገባ። በአንጻሩ በኮንጎ ብራዛቪል ዕዳውን ያናረው የሙስና መንሰራፋት ነው፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ!

የተበዳሪዎቿ የመክፈል አቅም የሚያሳስባት የማትመስለው ቻይና ሰላም ማጣት ናላዋን ላዞረው ሰሜን ሱዳን በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር የ2015 የአንድ ዓመት ዕዳወዋን የሰረዘችላት ቢሆንም ሰሜን ሱዳን ግን አምስተኛ ባለ ዕዳ አገር ሆና ከመመዝገብ አልዳነችም።

ይህ መረጃ እስከ ዛሬ ዓመት ድረስ የተመዘገበ ነው፤ ባለፉት የአንድ ዓመት 12 ወራት ውስጥ የቻይና ብድር መስጠትና የአፍሪካ አገራት በእዳ ውስጥ መስጠም የተቋረጠ አይደለም። ቻይና ቃሏን አክባሪ ከሆነች ‹‹ዕዳችሁን እተውላችኋለሁ›› ያለቻቸው አገራት እንዳሉ ዘገባው ጨምሮ ጠቅሷል። የምትወርሳቸው ብዙ የአፍሪካ ሀብቶች እንደሚኖሩ ግን አይጠረጠርም።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here