ዕረቡ መስከረም 18 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካቸው በፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ከሚመራው የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ልዑካን ቡድን ጋር የኹለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
ኹለቱ መሪዎች በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት እና ቁርጠኝነትን ገልጸዋል። በተለይም የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ እንዲሆን አብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ ትኩረት ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ኢትዮጵያ የተሻለች ሶማሊያን ለማስቻል ለተከፈለው መስዋዕትነት አድናቆታቸውን ገልፀው፤ ኹለቱ አገራት የሚያጋጥሟቸውን የጋራ ችግሮች ለመፍታት የትብብር አስፈላጊነትን አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከአዲሱ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ አስተዳደር ጋር በተለያዩ ደረጃዎች ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፤በተለይም ለኢኮኖሚ ዕድገት አጽንዖት ሰጥተዋል።
ጠንካራ እና የተረጋጋች ሶማሊያ ለኢትዮጵያ ጥንካሬ የሚጠቅም መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን አዜአ ዘግቧል።ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለኹለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።