በአዲስ አበባ ከተማ ከ800 ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በመዲናዋ የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ እንዲሆን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ዓለማየሁ ገልጸዋል። በዚህም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮግራምና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኤጀንሲው እስካሁን ባለው ሂደት ለ870 ሺሕ የመዲናዋ ነዋሪዎች የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት መስጠቱን የጠቀሱት ዮናስ፣ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የአሻራ ናሙና መወሰዱን እንዳስታወቀ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ኤጀንሲው በ2014 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ደንበኞቹ አገልግሎት መስጠት የቻለ ሲሆን፤ በዚህም 125 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015



