በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ የ10ኛው የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ናቸው፤ ሰዒድ መሐመድ። ትውልዳቸው በትግራይ ሽሬ እንዳሥላሴ አውራጃ፣ አዲደእሮ በሚባል አካባቢ ነው። በግብርና ከሚተዳደሩት ወላጆች የተገኙት ሰዒድ፣ መደበኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል የ45 ደቂቃ መንገድ በእግራቸው መጓዝ ይጠበቅባቸው ነበር። እንደዛም ሆኖ ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም፤ ለዚህም ምክንያቱ በሰዓቱ የተነሳው ጦርነት ነው።
ሰዒድ የ14 ዓመት አዳጊ እያሉ፤ ወላጅ አባታቸው የሰሊጥ እርሻ ላይ ሠርተው ባገኟት 600 ብር ለመጀመሪያ ልጃቸው የልብስ ስፌት ሱቅ ከፈቱለት፡፡ ሰዒድም ከታላቅ ወንድማቸው ጋር እዚያች ሱቅ የሚውሉበት እድል ተፈጠረ፡፡ ያኔ ሙያውን ተማሩ። በኋላም ከመቀሌ ኩኻ፣ ከኩኻ ድጋሚ ወደ መቀሌ፣ ከዛ ወደ አዲሰ አበባ ሙያቸውን ይዘው ተጉዘዋል።
ከምንም በላይ ግብ ላይ ማተኮርና መሥራት ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑት ሰዒድ፣ ተቀጥሮ ከመሥራት የራሳቸው የሆነ ነገር ባለቤት መሆን ይመኙ ነበርና በአንዲት ማሽን ሳይሰለቹ ሠሩ፡፡ በ1981 አራት የልብስ መስፊያ መኪና እና 21 ሺሕ ብር ይዘው ወደ አዲስ አበባ አመሩ። ከዚህ ተነስተውም ነው አምባሳደር የልብስ ስፌትን አሁን የደረሰበት ደረጃ ያደረሱት፡፡
ሰዒድ በአሁኑ ሰዓት በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያሏቸውና ከፍተኛ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች ባለቤት ናቸው። አምባሳደር ልብስ ስፌት፤ አምባሳደር ሆቴል፤ አምባሳደር ሪል እስቴት እና አምባሳደር ሞል የረጅም ዘመን የሥራ ትጋታቸው ውጤቶች ናቸው።
የኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው መጽሔቱ አዲሱ ደረሰ፤ ሥራ ፈጣሪ እና ባለሀብት ከሆኑት ሰዒድ መሐመድ ጋር የንግድ ሥራ እንቅስቃሴአቸውንና የግል ልምዳቸውን በሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ቆይታ አድርጓል። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬም እንደሚከተለው ተርጉማ አቅርባዋለች።
(ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት እንደ አዲስ ማለዳ ሁሉ በቻምፕዮን ኮምዩኒኬሽን የሚታተም በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚዘጋጅ ወርሃዊ መጽሔት ነው።)
የቤተሰብ ሰው ነዎት። እስቲ ስለቤተሰብዎ እንዲሁም ምን ዓይነት አባት እና የትዳር አጋር እንደሆኑ ይንገሩን?
ሰባት ልጆችና 13 የልጅ ልጆች አሉኝ። ኃይለኛ ሰው አይደለሁም። በቁጣ በመናገር እና ልጆችን በመግረፍም አላምንም። ይህም ከአባቴ የወረስኩት ነገር ነው።
ከአንደኛው በቀር ሁሉም ልጆቼ ከእኔ ጋር ነው የሚሠሩት። እንደውም ከልጆቼ አንደኛው የአምባሳደር ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው። ሁላችንም እንደ ቤተሰብ እንዲሁም በንግዱ ዓለምም እንደ አንድ ቡድን ነን።
ወንዱ ልጄ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ የቦርድ ስብሰባ እና በተመሳሳይ ከአገር ውጪ ወዳሉ ሌሎች ተሳትፎ የሚፈልጉ የንግድ እንቅስቃሴ አውዶች ላይ ስወስደው አስታውሳለሁ። አንደኛዋ ሴቷ ልጄም የአምባሳደር ሆቴል እና የአምባሳደር ሞል ማናጀር ነበረች። ምርታችንም ወደ ኹለተኛ ትውልድ ተሻግሯል። አሁን ቼክ ፈራሚ እኔ አይደለሁም። ልጆቼም በዚሁ ንግድ ሥራ መስመር ውስጥ ገብተዋል።
ወጣቶች ፋይናንስን እንዲረዱ ማስተማርን በተመለከተ ያለዎት ዕይታ ምንድን ነው?
እኔ በትምህርት ቤት ደረጃ ያጠናሁት ምንም ነገር አልነበረም። ለእኔ በጣም ወሳኙና እኔንም ለዓመታት በዚህ ዘርፍ ያሻገረኝ የምለው ለራሴ ያስቀመጥኩት ግብ ነው። ልደርስበት ያሰብኩት ሕልም በፈተናዎች መካከል ሁሉ እንዳልፍ እና በነበሩ መውደቅና መነሳቶች ውስጥ እንድማር አድርጎኛል።
ለምሳሌ የየሩብ ዓመት የሽያጭ ሪፖርት እና እቅድ ማዘጋጀት የመጣው ከብዙ የንግድ ሥራ ተሳትፎ በኋላ ነው። በበርካታ ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍ፣ ከበርካታ ባለሞያዎች ጋር በመሥራት ያገኘነው ልምድ ነው በሂደት እንዲህ ያለው አቅምና ችሎታ ላይ ያደረሰን። ስለዚህ ለእኔ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ከሚያስፈልገው አቅምና ችሎታ በላይ በጣም አስፈላጊው ግልጽ የሆነ ግብ ማስቀመጥ ነበር።
በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ የነበረውን የማምረቻ ፋብሪካ ሸጣችሁ ወደ ገላን ዞራችሁ እንደነበር ይታወሳል። ስለዛ ፕሮጀክት ጥቂት ይንገሩን?
ጥሩ አልሠራም፣ መደብሩንም ሸጠን ሙሉ ሐሳቡን ትተነዋል። መጀመሪያ ላይ ሐሳባችን ቲ-ሸርቶችን በብራንዳችን ማምረት ነበር። አምርተንም ወደ ውጪ የመላክ እቅድ ነበረን።
ነገር ግን የተለያዩ ምክንያቶች ተደማምረው ሐሳቡን የመተው ውሳኔ ላይ አድርሰውናል። በአንድ በኩል በዘርፉ ተሰማርተው ካሉ አካላት ያገኘነው፣ በዘርፉ ተወዳደሪ መሆን ከባድ ነው የሚል ምክር ነው። በእኛ በኩል ደግሞ ፍርሃት የነበር ይመስለኛል።
እና አሁን ላይ ታድያ እንዴት ነው የሱፍ ልብሶችን ምርት እያስሄዳችሁ ያላችሁት?
አሁን የሱፍ ልብስ ማምረት ትተን አዳማ ኢንደስትሪ ፓርክ ለሚገኝ ፋብሪካ ሰጥተናል (‹አውትሶርስ› አድርገናል)። ይህም ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ብቻ ተብሎ የተከፈተ ሲሆን፣ ለእኛ ኹለት መስመሮችን ለቀውልናል።
ሌሎች ትላልቅ ብራንዶችም እንዲህ ያለ መንገድ ይጠቀማሉ። ናይክም ይሁን አዲዳስ፣ ማምረቻቸውን ለሌሎች ይሰጡና (አውትሶርስ ያደርጉና) እነርሱ ብራንዲንጉ ላይ ያተኩራሉ። እኛም ልክ እንደዛው ነው ያደረግነው። እንዳልኩትም፤ አሁን እኛ ትኩረት የምናደርገው ዲዛይን፣ ብራንዲንግ፣ ማርኬቲንግ፣ ማስታወቂያ እና መሰል የቢዝነስ ጉዳዮች ላይ ነው።
ኢትዮጵያ ከአጎዋ መሰናበቷ ይታወቃል። ይህ በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል ይላሉ?
የአጎዋ ልዩ ተጠቃሚነት በእርግጥ ለአገሪቱ ትልቅ ጥቅም ነበረው፤ ይህ ምንም አያጠራጥርም። ነገር ግን እኔ የሚያሳስበኝ በእኛ በኩል ያለው ችግር ነው። እስቲ ሠራተኞቻችን እየሠሩ ስላሉበት ሁኔታ እና ምርትን ለመጨመር እንዲቻል ተጨማሪ ሰዓት ለመሥራት ስላላቸውን ተነሳሽነት እንነጋገር። አንድ ምርት ወደ ጅቡቲ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ ይፈጅበታል የሚለው ላይ እናውራ። እንዲሁም በንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ውስጥ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ስላላቸው ግንዛቤ እናንሳ።
አሜሪካ ውስጥም ሆነ ሌላ ቦታ፣ ገበያው አለ። እኛ ማተኮር ያለብን ግን በእኛ በኩል ስላለው ጉዳይ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ወደ አጎዋ እንመለሳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ተቋማዊ ባህል እና የጋራ ግብ ያለው የሥራ ቡድን እንዴት ነው የሚገነባው ወይም እርስዎ እንዴት ነው የገነቡት?
ለሠራተኞቼ ነጻ የሆነ አካባቢን በመፍጠር አምናለሁ። እርስ በእርስ እንግባባለን፣ እንቀላለዳለን። በኩባንያችን ያሉ አብዛኞቹን ሠራተኞች በሥም አውቃቸዋለሁ። ይህም በአንድ ቡድን አባላት በእያንዳንዳቸው የተቋምን ግብ የምናሰራጭበት እና የምናጋራበት አንዱ መንገድ ነው።
እርስዎ እንደ አንድ የቢዝነስ ተቋም መሥራችና መሪ፣ በዘርፉ ድክመቴና ጥንካሬዬ የሚሉት ምንድን ነው?
የንግድ ሥራው ውስጥ ባለቤቴን እና ልጆቼን ማካተቴ ለሚሰጥኝ አስተያየት ወይም ትችት ዝግጁ/ክፍት መሆንን አስተምሮኛል።
ሆኖም አንዳንዴ ልናደርጋቸው እና ተጽእኖ ልንፈጥራቸው የሚያስችሉን የነበሩ፤ ነገር ግን በመወላወል እና አደጋን (ሪስክ) በመፍራት ያመለጡንን አንዳንድ እድሎችን መለስ ብዬ አስባለሁ። ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ 30 ዓመታት ሆነዋል። ከዛ ወዲህ ያሳካነውን ያህል በአንጻሩ አንዳንድ ሊያሳድጉን የሚችሉ ያልተነኩ እድሎች ነበሩ። እና ይመስለኛል ያ ድክመት ነው።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ ይሁን እንጂ እንደ እርስዎ ዓይነት ምሳሌ የሚሆንና አነቃቂ የሆነ ታሪክ ሲነገር ብዙም አይሰማም። በዚህ ላይ ምን ዕይታ አለዎት?
ለስኬት አቋራጭ መንገድን የመጠቀም ነገር አለ። ይህ ጤናማ ያልሆነ መንገድ ነው። ጤናማ አለመሆኑ ጥርጥር የለውም፤ እኔም ልጆቼ እንዳያደርጉ ደጋግሜ የማስተምራቸው ጉዳይ ነው። ግን ደግሞ ሰዎች ሁሉ ታሪካቸውን ስለማጋራት ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ስሜት ላይኖራቸው እንደሚችል ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። ለምን ብለህ ከአራተኛ ክፍል ትምህርት እንዳቆምክ ታወራለህ?
አንዳንድ በፍጹም የሌሎች ዕይታ ውስጥ ሳይገቡ የሚሠሩ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ሚድያው እንዲህ ያለው ታሪክ ለአድማጭና ለተመልካች ለማድረስ ብዙ ማጥናት እና ብዙ በሮችን ማንኳኳት ይጠይቀዋል። ነገር ግን ደግሞ ሥራ ፈጣሪ የሆነ ሰው ሌሎች ከልምዱ ወይ ከልምዷ እንዲማሩ ለማስቻል እድል መፍጠር አለባቸው ብዬ አስባለሁ። አሁን እኔ እሱን እያደረግሁኝ ነው ያለሁት።
በአንድ በኩል በሌሎች አውዶች ላይ እንግዳ ሆኜ እቀርባለሁ፣ እንዲሁም በራሴም ጥረት ታሪኬን ሰዎች እንዲሰሙት አደርሳለሁ። እንደ ሥራ ፈጣሪ፣ ወጣቶች እንዲማሩበት ብዬ ታሪኬን አጋራለሁ። ያ ምስክርነትም በርካቶች ወደ ንግድ ዓለም እንዲገቡ ይስባል ብዬም አምናለሁ።
እርስዎ በጨርቃ ጨርቅ ቢዝነስ ውስጥ ነው የቆዩት። እና ለበርካታ ዓመታት በአንድ የቢዝነስ መስመር ውስጥ ብቻ መጓዝ እና በዛ ላይ ማተኮር ምን ጥቅማ አለው ይላሉ?
ይህንን ሐሳብ ዓለማቀፍ የሆኑ የሥራ ፈጣሪዎች ሲያነሱት፣ እንቁላልን በአንድ ቅርጫት ውስጥ በማድረግ እና በብዙ ቅርጫት ውስጥ በማድረግ መካከል ያለውን ልዩነት በማሳያነት ያቀርባሉ። እያንዳንዱ የራሱ የሆነ ጥቅምና ጉዳት አለው።
እኔ የምወደው አንድ የቢዝነስ መስመር ላይ ማተኮርን ነው። ብዙ ሥራዎችን በአንድ ጊዜ መሥራት፤ አንዱ ቢዝነስ ስኬታማ እንዲሆን መሥራት የሚገባውን በበቂ ሁኔታ ላያሠራ ይችላል። ብዙ ንግድ ሥራዎች ያሉህ ከሆነ፣ ለሁሉም ለየአንዳንዱ በቂ ትኩረት አትሰጥም። ስለዚህም እንቁላልህን ብዙ ቅርጫት ውስጥ ማስቀመጥህ ትርጉም አይኖረውም።
ለምሳሌ ስታርባክስ በማስፋት እና በማሻሻል ብቻ ያምናል። ይህም አንድ የቢዝነስ መስመር ብቻ ነው፣ የተለያየ ዓይነት የለውም።
በምን መንገድ ነው የሆቴሉን ኢንዱስትሪ የተቀላቀሉት? የሪል ስቴት ቢዝነሱንስ?
ይህ የሆነው ከ15 ዓመታት በፊት ነው። እውነት ለመናገር ቀድሞ የታቀደ ነገር አልነበረም። በዛን ጊዜ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አቅም አለው እንዲሁም የሆቴል ቢዝነስ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማገዝ የሚያደርገውን ጥረት በሚመለከት ተደጋግሞ ሲነሳ ይሰማ ነበር። ስለዚህ በኢትዮጰያ በተለመደው የንግድ ሥራ ባህል መሠረት እኛም ሌሎችን ተከትለን ቢዝነሱን ተቀላቀልን።
መጀመሪያ 48 ክፍሎች ያሉት ባለአራት ወለል፣ ሁለት ብሎኮች አስገነባን። ከዛም ተጨማሪ 75 ክፍሎችን ሊያሠራን እንዲችል በዛው አቅራቢያ ቦታ ገዝተን በተመሳሳይ ግንባታ አከናወንን። ምንም እንኳ ቀድሞ የተጠና ባይሆን፣ ቀስ በቀስ ክፍሎችን 200 በማድረስ ወደ ቢዝነሱ ገባን።
ልክ የሆቴሉ ቢዝነስ ውስጥ እንደገባን ሁሉ፣ የሪል እስቴት ሥራውም በደንብ የታሰበበት የንግድ እንቅስቃሴ አልነበረም። በጊዜው ሥራው በብዙዎች እየተሠራ የነበረ ከመሆኑ አንጻር፣ ዘለን ነው የገባነው።
ነገር ግን ይህኛው ለእኔ ትርፋማ ቢዝነስ አልነበረም። እንዲሁም ደግሞ የቢሮክራሲ ሥራዎች፣ በዋጋ ንረት እና በእኛም ውስጥ በዘርፉ የአመራር ልምድ እጥረት ከመኖሩ የተነሳ በጣም ፈታኝ ሆኖብን ነበር።
እንደውም የጨርቃጨርቁ ዘርፍ የደጎመው ጊዜም ነበር። ነገር ግን በዛ ሳይት የተፈጠረው ኅብረት በእኔ የንግድ ሥራ ሕይወት ውስጥ በጣም ትርጉም ያለው ብሎም በሠራነው ሥራ ሁሌ የሚያመሰግኑ የተለያዩ በርካታ ሰዎች ጋር አስተዋውቆኛል። ከገንዘቡ ጥቅም ጉዳይ ይልቅ ይህኛው የምደሰትበትን ነገር ሰጥቶኛል።
የአምባሳደር አልባሳት/ሱፎች አገር አቋርጠው ይሄዳሉ ብለን እንጠብቅ?
የኢትዮጵያ ሕግ ገንዘብህን ከአገር ውጪ ይዘህ እንድትወጣ እና ሌላ አገር ላይ ኢንቨስት እንድታደርግ አይፈቅድም። በተለይ በክልሉ (በአፍሪካ) ለማስፋፋት እናስባለን፣ ነገር ግን የአገሩ ሕግ ይከለክለናል።
እስከ አሁን ሊጠቅመን ይችል ነበር፣ ነገር ግን ከዚህ በኋላም ጥብቅ የሆኑ ሕጎች/መመሪያዎችን ቀለል ማድረግ አለብን። ይህ ዓይነት ከባድ የሆነ ሥራ እጥነት በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ሊቀረፍ የሚችል አይደለም። ከውጪ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው።
በኢትዮጵያ፣ የትርፍ ድርሻህን ማግኘት ቀላል አይደለም። በሌሎች አገራት፣ ከኢንቨስትመንት የምታገኘው የትርፍ ድርሻህን እንድታወጣ ይፈቀዳል አልያም በቀላሉ ዳግም ኢንቨስት ለማድረግ ያስችላል።
አሁን ላይ ያለው የደኅንነት ጉዳይም ዓለማቀፍ የንግድ ትብብሮችን በእጅጉ እያከበዳቸው ይገኛል። አገሪቱ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያለችበት የብድር ደረጃም ሌላው ጉዳይ ነው። የውጪ ዜጎችም የብድር አገልግሎት ተደራሽነትን ይመለከታሉ። ወደዚህ መጥተው በትብብር ከመሥራት በፊት ያንን ሁሉ ከግምት ያስገባሉ።
ትልልቅ ተቋማት ከሚጠበቁባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው። ይህን ኃላፊነት እንዴት እየተወጣችሁ ነው?
በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ለሚቀርብልን ጥሪ ምላሽ እንሰጣለን። ከዛም በሻገር እኔ በተወለድኩባት ከተማ ትምህርት ቤት እና መስጂድ አስገንብተናል። በእናቴ ሥምም የወጣቶች ማእከል አስገንብቻለሁ።
የወጣቶች መነሻ የሚሆኑና ተነሳሽነት የሚፈጥሩ የተለያዩ የሥራ ፈጠራ ውድድሮችንም ስፖንሰር አድርገናል። ምንም እንኳ በተለየ ክፍል አይሁን እንጂ፣ ላሳደገን ማኅበረሰብ እና አገር መልሰን እየሰጠን እንገኛለን።
በንግድ ሥራዎ ላይ የወደፊት እቅድዎ ምንድን ነው?
በሪል እስቴቱ እንቀጥላለን፤ እናስፋፋለን። አሁን እንዳለው ዓይነት (አራት ኪሎ የሚገኘው) ሌላ ሞል እንገነባለን ብዬ አስባለሁ። በእርግጠኝት ደግሞ በጨርቃጨርቅ ቢዝነስ ላይ የማስፋፋት ሥራ እንሠራለን።
በመቀሌ፣ በደብረ ብርሃን፣ አዳማ እና ሐዋሳ የልማት እቅዶች አሉን። ስለዚህ በሁሉም ዘርፎች ብዙ የማስፋፋት ሥራ ይኖራል፤ አሁንም በእቅዳችን መሠረት መንገድ ጀምረናል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና አለመረጋጋቶች አሉ። ሕይወታችው በግጭት ውስጥ እየተፈተነ ላሉ ወጣቶች ምን ይመክራሉ?
እኔ ያደግኩት ደርግ ከትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር እና ከኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ጦርነት ላይ በነበረበት ጊዜ ነው። አንድ ወቅት ላይ ታንኮች፣ የተኩስ ድምጽ እና ሞት የየእለት ክስተት ሆነው ነበር። ያም የእኔ የወጣትነት ዘመን እውነት ነበር። ጭካኔውና የነበረው አስከፊ ሁኔታ አዲስ ልምድ ሲሆን፣ እኔም ልደርስበትና ላሳካው የምፈልገው ግብ ላይ እንዴት ማተኮር እንደምችል ተገነዘብኩኝ።
በዛኛው ጦርነት ብቻ አይደለም፤ የአሁኑ የሰሜኑ ጦርነት ራሱ በብዙ መንገድ ተጽእኖ ፈጥሮብኛል። ነገር ግን እኔ የማተኩረው ልደርስበት ወይም ላሳካው የምችለው ላይ ነው። ፖለቲካ ውስጥ አልገባም። እንደምታዘበው ከሆነ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ለሚሰራጨው የጥላቻ ንግግር ብዙ ትኩረት አለ። ያንን መቀነስ አለብን።
ስለዚህ ከባድና አስጨናቂ የሆነ እውነት ውስጥ እየኖሩ ላሉ ወጣቶች እኔ የምሰጠው ምክር፣ ነገሮች ምን ያህል ከባድ ቢሆኑም ሥራቸው ላይ እንዲያተኩሩ ነው።
ነገር ግን በኹለት ወገን ሆነው እየተጓተቱ ላሉ ምሁራን፣ የደረሰውን ኪሳራ ማየት እና ጉዳዩን በንግግር መፍታት የተሻለ እንደሆነ አስባለሁ።
እኛ ጦርነትን ከወላጆቻችን ወረስን፣ አሁንም በተመሳሳይ መንገድ የእኛ ልጆች ከእኛ ጦርነትን እየወረሱ ነው። ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለአገራት ወደ ጦርነት መግባት ቀላል ይሆናል ብሎ ያሰበ አልነበረም። እየተጓተቱ ያሉት ምሁራንም እንደሚያውቁት፣ ጀርመን እና መላው አውሮፓ ኢኮኖሚያቸውን የገነቡት ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው። ስለዚህ የደረሱበትን የልማት ደረጃ ለማስቀጠል ከግጭት መራቅ መሠረታዊ እንደሆነ ተረድተዋል።
አሁን እየተካሄደ ባለው ጦርነትና እኔ ልጅ እያለሁ ይካሄድ በነበረው ጦርነት መካከል ያለውን ልዩነት ታውቃለህ? ያኔ አገሪቱ የተሞላችው ባልተማሩ ዜጎች ነበር። ስለዛም ወደ ጦርነት ለመግባት የሚደረግ ውሳኔንም ሆነ የሚደርሱ ጥፋቶችን በሙሉ ከዛ አንጻር ልንረዳው እንችላለን። አሁን ግን ውሳኔ እየወሰኑ ያሉ ሰዎች የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ናቸው፤ እየተገደሉ ያሉትም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው። ይሄ አስደንጋጭ ነው!
አንድ አገረኛ ብሂል አለ፤ ‹ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ› የሚል። እናም ለትውልድ እና ለኢኮኖሚ የተሻለ ነገር ሲባል መተውና ማሳለፍ ይገባል።
ነገን ወይም የወደፊቱን ሲያስቡ ምን ይታይዎታል?
እኔ ጠንቃቃና በጎ አሳቢ (Optimist) ሰው ነኝ። በግሌ ብቻም ሳይሆን በጀትና የቢዝነስ ውሳኔአችንም ላይ ጠንቃቃ ነን። ወደፊቱ ፈታኝ ነው የሚሆነው ነው። ግን ደግሞ ብዙ እድሎችንም ይዞ ይመጣል። መንግሥት ኢኮኖሚው ላይ እንዲያተኩር እመክራለሁ። እርስ በእርሳቸው በጥላቻ ንግግር የሚቀባበሉ ወጣቶችም የተሻለ ነገር ሊገነቡ ይገባል።
ብሔራዊ የሆነ ሕልም ላይ ልናተኩርም ያስፈልጋል። ቡድኖች አሁን ላይ የየራሳቸው ሕልም ላይ ነው ያተኮሩት። ሁላችንም በጋራ ሆነን የምንሠራበት ትልቅ የጋራ ሕልም ያስፈልገናል። እንደውም በዚህ ላይ ነው መንግሥት ሚና ያለው። እነዚህን ጥረቶች ሥልታዊ ማድረግ እና ማኀበራዊ መነቃቃት መፍጠር አለበት።
ዐስር ሚሊየነሮች ብዙም ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም። በእኔ እምነት፣ በጋራ ወደተስማማነንበት ብሔራዊ ሕልም የሚያመራ ብሔራዊ የሆነ ማኅበራዊ መነቃቃት መፍጠር የታሪክን አካሄድ ሊቀይር ይችላል። በዛ መንገድ ነው ደቡብ ኮሪያም ስኬትን ያገኘችው።



