በምሥራቅ ወለጋ አምስት ወረዳዎች በኦነግ ሸኔ ከበባ ውስጥ መሆናቸው ተገለጸ

0
2149

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ውስጥ የሚገኙ አምስት ወረዳዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂ ዳግም ከበባ ውስጥ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

ታጣቂ ቡድኑ በአምስት ወረዳ ነዋሪዎች ላይ ዳግም ጥቃት ለማድረስ ከበባ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም አጣዳፊ የነፍስ አድን ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል። ታጣቂ ቡድኑ በወለጋ የተለያዩ ዞኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ላለፉት አራት ዓመታት ሲያደርሰው የነበረው ጭፍጨፋ መከላከያ በቦታው በመግባቱ ለተወሰነ ጊዜ ጋብ ብሎ ነበር።

ከነሐሴ 18/2014 ጀምሮ ሕወሓት በሰሜኑ በኩል ሦስተኛ ዙር ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ፣ መከላከያ ወለጋን ለቆ በመውጣቱ ሸኔ የተለመደ ጥቃቱን ለማድረስ ኃይሉን እያሰባሰበ መሆኑ ነዋሪዎቹ አስታውቀል።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሀሮ ሊሙ፤ ሊሙ እንዲሁም ኪረሙ ወረዳ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት ለማድረስ እየተዘጋጁበት ካሉ ወረዳዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ሦስቱ ወረዳዎች ለዓመታት ተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶባቸዋል የተባለ ሲሆን፤ አሁንም ታጣቂ ቡድኑ ተመሳሳይ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ላይ ስለመሆኑ ስጋት ያደረባቸው ነዋሪዎች ከለላ እንዲደረግላቸው ከወዲሁ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ፤ ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ያሉ ንጹሐን ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ዳግም ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ ነው ተብሏል።

በአሙሩና በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ከነሐሴ 25/2014 ጀምሮ ባሉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ በኦነግ ሸኔና በአማራ ኢ-መደበኛ ታጣቂ ኃይሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ የሸኔ ታጣቂዎች በጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳ በፈጸሙት ጥቃት የሟቾች ቁጥር ወደ 200 እንደሚጠጋ ጠቅሰዋል። አክለውም ኦነግ ሸኔ ድጋሚ ጥቃት ለመሰንዘር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎችን እያሰባሰበ ይገኛል ሲሉ ጠቁመዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ዳግም ጥቃት ለማድረስ ሰሞኑን፣ ከተለመደው ለየት ያለ ብዛት ያላቸው ታጣቂዎች እያሰባሰበ ነው ተብሏል። በመሆኑም መከታ የሚያደርግ ከፍተኛ የመንግሥት ኃይል ያስፈልጋል ሲሉ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

አሁን አሁን የኦሮሚያ ክልል ተወላጆችም በታጣቂ ቡድኑ የሞት ጥቃት እየደረሰባቸው ስለመሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ከሦስት ቀን ጀምሮ ከፍተኛ አመራሮችም ሰላም ወዳለባቸው አጎራባች ከተሞች እየተፈናቀሉ ነው።

በሆሮ ጉድሩ፤ አሙሩ እንዲሁም ጃርደጋ ጃርቴ የነበሩ አመራሮችና ካቢኔዎች ወደ አማራ ክልል ተፈናቅለዋል። እንዲሁም በሊሙ እና ሀሮ ሊሙ ወረዳ የነበሩ የመንግሥት አመራሮች ወደ አንገር ጉትን ከተማ ተፈናቅለዋል ተብሏል።

በተያያዘም ሊሙ፤ ሀሮ ሊሙ እና ኪረሙ ወረዳ በተለይም ሀሮ የሚባል ቦታ ላይ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት ለተወሰነ ጊዜ ጋብ ብሎ ቢቆይም ከሦስት ቀን ወዲህ ግን ብዛት ባለው ታጣቂ ቡድን ከበባ ውስጥ መግባቱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው በአንገር ጉትን ከተማ የሚገኙ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ነዋሪዎችም ከሦስት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ድጋፍ እያገኙ አይደለም ተብሏል። መንግሥት ድጋፍ እየላኩ ነው ይበል እንጂ ተፈናቃዮች ግን ድጋፉን እያገኙ አለመሆኑ ተሰምቷል። በታጣቂዎች ምክንያት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ከ500 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንም የክልሉ መንግሥት ገልጾ ነበር።

አዲስ ማለዳ በከበባ ውስጥ ነን ያሉ ነዋሪዎችን ካደመጠች በኋላ የክልሉ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት፣ ለክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛው ስልክ ብትደውልም  ባለማንሳታቸው ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here