መፍትሔ ያልተገኘለት የመዲናይቱ የትራንስፖርት ችግር

0
1587

ጠዋት እና ማታ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ትራንስፖርት ፍለጋ የሚሰለፉ የመዲናዋን ነዋሪዎች መመልከት በከተማዋ የትራንስፖርት ችግር ስለመኖሩ ያሳብቃል። በየእለቱም መምጣታቸውን እንኳን እርግጠኛ የማይሆኑባቸውን የብዙኀን ትራንስፖርት አማራጮች ለረዥም ደቂቃዎች በተስፋ ቆመው ይጠባበቃሉ። አብዛኛዎቹም በሰዓት ገደብ የሚንቀሳቀሱት ተማሪዎች እና ሠራተኞች ናቸው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ የአዲስ አበባ ነዋሪ እየተላመደው የመጣውን ነገር ግን ለብዙዎች መሰረታዊ ጥያቄ ሆኖ የሚገኘውን የብዙኀን ትራንስፖርት ችግር መንስኤዎችን ለማጣራት እና መፍትሔ ለማፈላለግ የሚመለከታቸውን አካላት እና ባለሙያዎች በማነጋገር በለጠ ሙሉጌታ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

መንደርደሪያ
የማለዳዋን ፀሐይ መውጣት ተከትሎ አንቀላፍታ የነበረችው አዲስ አባባ የሌሊቱን የዕረፍት ጊዜዋን ጨርሳ ከተኛችበት መንቃት ትጀምራለች። ነዋሪዎቿም ማልደው በየፊናቸው ይሰማራሉ፤ ባለጉዳዮች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን እና ጉዳያቸውን ለመፈፀም፣ ተማሪዎች ነገ አገር የሚረከቡበትን የእውቀት ማዕድ ወደሚቋደሱበት የትምህርት ገበታቸው ለመድረስ ይፋጠናሉ። የማለዳው ሩጫ በዚህ መልኩ ይጀመራል።

በዚህ መሀል የግል የትራንስፖርት አማራጭ ያላቸው ሰዎች የከተማዋን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እየተጋፈጡ ወደሚፈለጉት ቦታ ለመድረስ ሲጥሩ በሕዝብ እና በብዙኀን የትራንሰፖርት አማራጮች የሚጠቀሙ ነዋሪዎች ሩጫ ግን ባሰቡት ልክ የተፋጠነ አይሆንላቸውም። ልባቸው ወደ ጉዳያቸው ቀድሞ ቢደርስም ማልደው የጀመሩት ሩጫ ባሰቡት ልክ የተፋጠነ እንዳይሆን በከተማዋ ያለው ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ምክንያት ሲሆንባቸው ማስተዋል የተለመደ ክስትት እየሆነ መጥቷል።
ከየቤቱ እና ከየሰፈሩ የሚወጡት ተሳፋሪዎች በታክሲ ተራዎች እና በአውቶቢስ ማቆሚያዎች ለረዥም ሰዓታት ተሰልፎ አሊያም እየተጋፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማገኛት በመጣር ረዥም ጊዜያቸውን ያባክናሉ። ይህንንም ተከትሎ በሠራተኛ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ላይ ረዣዥም ሰልፎችን መመልከት አዲስ አይደለም።

የችግሩ ገፈት ቀማሾች ምን ይላሉ?
ዓለም ተፈራ በአንድ ጤና ተቋም ውስጥ በገንዘብ ያዥነት ታገለግላለች። ኹለት ልጆች ያሏት ሲሆን በሥራ እና በትምህርት ቀናት በእያንዳንዱ ማለዳ ለልጆቿ የሚሆን ምግብ ለማሰናዳት እና ወደ ትምህርት ቤት እንዲሔዱ ለማዘጋጀት ሊነጋጋ ሲል 11፡30 ከእንቅልፏ ትነሳለች፤ ዝግጅቷን እስከ 1፡30 አጠናቅቃ ለመጨረስ ትጣደፋለች። ለምን ቢባል ከምትኖርበት በተለምዶ ፈረንሳይ ተብሎ ከሚጠራው ሰፈር ተነስታ ወደ ሥራ ቦታዋ መገናኛ ለመድረስ ከሥራ መግቢያ ሰዓቷ አንድ ሰዓት ተኩል ቀደም ብላ መውጣት ይኖርባታል።

ዓለም በአካባቢው በቂ የትራንፖርት አማራጭ ባለመኖሩ እንዲሁም ፍትሐዊ የትራንስፖርት ክፍፍል እና ቁጥጥር ባለመኖሩ ለረዥም ደቂቃዎች ትራንስፖርት ፍለጋ እንደምትሰለፍ ትገልጻለች። ታክሲዎች እና አወቶቢሶች ከዘገዩ እና በታሰበው ሰዓት ካልደረሱ ደግሞ ከአለቆቿ ጋር ከመጋጨቷም በላይ ወር ሙሉ ለፍታ የምታገኛት ደሞዟ የቅጣት ሲሳይ እንደሚሆን ትናገራለች።

ከሥራ በኋላም ተመሳሳይ የትራንስፖርት እክል እንደሚገጥማት የምትናገረው ዓለም፣ ወደ ቤቷ ለመድረስ ከአንድ ሰዓት በላይ በሰልፍ ላይ ታሳልፋለች። ይህም ከሥራዋ ሌላ ተጨማሪ ሥራ እንደሚሆንባት፣ በጊዜ ወደ ቤቷ ገብታ በሥራ የደከመ አካሏን እንዳታሳርፍ እና ለነገ ውሎዋ እንዳትዘጋጅ እንደሚያደርጋት ትገልጻለች።
ከብዙ ጥበቃ በኋላም የሚመጡት ታክሲዎች መምሸቱን ምክንያት በማድረግ ከመደበኛው ታሪፍ በላይ እንደሚጠይቁ ገልጻ አውቶቢሶቹም ቢሆኑ ሲፈልጓቸው አይገኙም በማለት ታማርራለች። ከዚህ በተጨማሪም ትርፍ ለመጫን በማሰብ እና ከትራፊክ ፖሊሶች ዕይታ ውጪ ለመሆን መንገድ ማቆራረጥ እና ተሳፋሪ ማንገላታት፣ ምሽትን ምክንያት በማድረግ ከሚደረገው ታሪፍ ጭማሪ በተጨማሪ የሚፈፀሙ ድርጊቶች መሆናቸውንም ትናገራለች።

በተመሳሳይ ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ደረጀ ሞገስ ከሚኖርበት አካባቢ ተነስቶ ጦር ኀይሎች ለመድረስ ቀላል የከተማ ባቡር አገልግሎትን አልፎ አልፎ ደግሞ ታክሲዎችን እንደሚጠቀም ይናገራል። “የከተማ ቀላል ባቡሩ ከመነሻው ከአያት ከአቅሙ በላይ ሞልቶ ይመጣል” የሚለው ደረጀ፣ በባቡሩ መሳፈር ይቅርና ከባቡሩ ለመውረድ እንኳን እንደማይቻል፣ ወደ ባቡሩ ለመግባት የሚደረግ ትንቅንቅ አንዳንዴ ለፀብ መንስዔ፤ አንዳንዴም ፈገግታን የሚያጭር እንደሆነ ይጠቁማል። የባቡሩን ከአቅም በላይ መሙላትን ተገን በማደረግም የሰዎች ኪስ የሚበረብሩም እንዳሉ ይናገራል።

በዚህም ምክንያት ቢያንስ ሦስት ባቡሮች ሲያለፉ ለመመልከት ተገድጃለሁ ይላል። የባቡሮቹ ስምሪት በመስመሩ ላይ የሚገኙትን ተጠቃሚዎች ቁጥር እና ፍላጎት ያማከለ አይደለም የሚለው ደረጀ፣ በአመዛኙ የተሳፋሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ ወደ ሆነበት መስመር የባቡሮቹ ስርጭት እንደሚበዛ ይገልጻል።

የመዲናዋ የሕዝብ ትራንስፖርት አማራጮች
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለሥልጣን መረጃ መሰረት በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍላጎት መሰረት በማድረግ ባሳለፍነው በጀት ዓመት 550 አንበሳ ከተማ አውቶብስ፣ 242 ሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት፣ 190 ፐብሊክ ትራንስፖርት ሲኖሩ በአጠቃላይ 982 ያህሉ አውቶብሶች ወደ ሥራ ገብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ያሳያል። ይህም ከአገልግሎት ዘርፉ 97 ከመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው።

ከዚህ በተጨማሪም 439 ሃይገር መካከለኛ አውቶብሶች፣ 374 በተለምዶ ቅጥቅጥ የሚባሉ ባሶች፣ 5 ሺሕ 667 ኮድ 1 ታክሲዎች፣ 8 ሺሕ 607 ኮድ 3 ሚኒባሶች እና 1 ሺሕ 163 ሜትር ታክሲዎች በአጠቃላይ 16 ሺሕ 250 የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽርካሪዎች በከተማዋ የሚገኙ ሲሆን በአማካኝ በቀን ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተሸከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ያሳያል። እነዚህ የትራንስፖርት አማራጮችም በቀን እስከ 3 ሚሊዮን የሚደርስ የከተማዋን ነዋሪ ከቦታ ቦታ ያጓጉዛሉ።

የሕዝብ ትራንስፖርት ማነቆዎች
አዲስ አበባ ከላይ በተጠቀሱት የትራንስፖርት አማራጮች ደረጃ ማቅረብ ከተቻለ ለምን ችግሩ ሙሉ በሙሉ መቅረፍ አልተቻለም የሚለውን ምላሽ ለማግኘት አዲስ ማለዳ የከተማው ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጠይቃላች። ባለሥልጣኑ ለከተማው የትራንስፖርት እጥረት መንስዔ ያላቸውን ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ለይቷል። እነዚህም የአቅርቦት ችግር፣ የስምሪት እና የቁጥጥር ማነስ እንዲሁም በከተማዋ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ዝቅተኛ መሆን ናቸው።

በከተማዋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ከሚገኙት የሕዝብ እና የብዙኀን የትራንስፖርት አማራጮች ላይ ከፍተኛ የሚባል እጥረት እንዳለ ለአብነትም በከተማዋ መሰማራት አለባቸው ተብለው ከሚገመቱ 3 ሺሕ አውቶቢሶች መካከል አሁን አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ከ 1 ሺሕ እንደማይበልጡ የባለሥልጣኑ መረጃ ያመላክታል። እነዚህም አውቶቢሶች ቢሆኑ በከተማ ውስጥ ባለው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት በሚፈለገው መጠን ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዳልቻሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ መአረ መኮንን ይገልጻሉ።

የትራንስፖርት ጉዳይ ሲነሳ በተለይም በሠራተኛ እና ተማሪ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ላይ የብዙዎቹ የከተማችን ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ተግዳሮት የሆኑት እነዚህ የትራንስፖርት ችግሮች መንስዔ ምን እንደሆነ ለመታዘብ አዲስ ማለዳ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ተንቀሳቅሳለች። በዚህ ወቅት በከተማዋ ከሚገኙ ታክሲ ተራዎች አንዱ በሆነው አራት ኪሎ ታክሲ ተራ ካገኘቻቸው የታክሲ ሾፌሮች መካከል ዳንኤል ሙላት (ሥሙ የተቀየረ) እንዲህ ሲል አወጋን።

ወጣቱ በታክሲ ረዳትነት እና ሹፌርነት ላለፉት 5 ዓመታት መሥራቱን ይገልጻል፤ “በከተማዋ የታክሲ ሥራ ጠዋት እና ማታን መሰረት ያደረገ ሥራ ነው፤ ጠዋት እና ማታ ተሯሩጠን ካልሠራን ከሦስት ሰዓት እና ከአራት ሰዓት በኋላ በታክሲ ተራዎች ላይ ረዥም ሰዓትን እናሳለፋልን” በማለት ያለውን ሁኔታ ይገልጻል።
እንደ ታክሲ ሹፌሩ ወጣት ዳንኤል ገለጻ፣ ከጠዋቱ 4፡30 ላይ ሠራተኛው እና ተማሪው በመንገድ ላይ አይታይም። ለዛም ይመስላል በርካታ ታክሲዎች ተሳፋሪዎቹ ተሰልፈውበት በነበረው ቦታ ላይ በተራቸው ይሰለፋሉ።

ዳንኤል፣ “እንደሚታወቀው የታክሲ ሥራ ደግሞ ከእጅ ወደ አፍ ሆነ ሥራ ነው። ነዳጅ ተሞልቶ፣ የተራ ተከፍሎ፣ ለባለቤቶች ቀን ገቢ ገብቶ የሚቀረው ነው እኛ የድካም ትርፍ። መንግሥትም ቢሆን በየጊዜው የታሪፍ ማሻሻያ የማያደርግ መሆኑ እንዲሁም ተሳፋሪውም ቢሆን ለሌላ አገልግሎት በርካታ ብሮችን እያወጣ ከእኛ ጋር ከመልስ ጋር በተያያዘ መጣላት እና መጨቃጨቅ ይቀናዋል” ብሏል። በዚህ መልክ ከሚገኘው ገንዘብ ላይም “ትራፊክ ፖሊሶች ሲይዙን የምንቀጣውን የቅጣት ክፍያ ባለቤቱ ሳይሆን እኛ ነን የምንከፍለው፣ ስለዚህ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እያንዳንዷን ሳንቲም እንሰበስባለን” ሲል ያክላል።

አዲስ ማለዳ የታክሲ ሹፌሩን ምሽትን ተገን አድርጎ ከታሪፍ በላይ አንዳንዴም እጥፍ በማድረግ ስለሚሰጡት አገልግሎት አንስታበት የነበረ ሲሆን “አምሽተን ከብርድ ጋር ታግለን ስንሠራ ልናገኘው የሚገባ ጥቅም ነው” ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

የችግሩ መንስዔ ይህ ብቻ አይደለም፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የብዙኀን የትራንሰፖርት አማራጮችን በተለይም አውቶቢሶችን የመጠቀም ልማድ ዝቅተኛ ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት አውቶቢሶች በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚጠቀሙባቸው አማራጮች ናቸው የሚለው የተሳሳተ አመለካከት እንዲሁም አውቶቢሶቹ የሚሰጡት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እና ቀልጣፋ አለመሆኑ በተጨማሪም በስፋት እና በተፈለጉበት ጊዜ አለመገኛታቸው መሆኑን ያነሳሉ።

በመሆኑም ሰዎች የግል መኪኖችን እንዲገዙ ምክንያት ሆኗል። ይህም በከተማዋ ለሚስተዋለው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረከት መአረ መኮንን ይገልጻሉ። የትራፊክ መጨናነቁ ምክንያት ይህ ብቻ አይደለም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር እና የተሽከርካሪዎች ቁጥር ዕድገት ጋር የሚመጣጠን የመንገድ እና መሰል መሰረተ ልማት በአነስተኛ ደረጃ ላይ መገኘት ችግሩን እንደሚያባብሰው መአረ ይገልፃሉ።

ችግሩ በመንግሥት የትራንስፖርት አማራጮች ላይ ብቻ የሚስተዋል አይደለም። በግሉ ዘርፍ ያሉ የብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን የሚያበረታቱ የታሪፍ ማሻሻያዎች አለመደረጋቸው፣ ከብድር እና ከቀረጥ ነፃ መኪኖችን አስገብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ሕጎች እና መመሪያዎች አለመስተካከላቸው ባለሀብቶች ደፍረው ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ አድረጓል።

ከዚህም በተጨማሪ አውቶቢሶቹ ረዥም አገልግሎት እንዲሰጡ እና በጥገና ወቅትም መለዋወጫዎችን ከማግኘት አንጻር በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን እና ለማሳድር፣ ለመጠገን እና ንፅሕናቸውን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስፍራዎች ከከተማዋ እድገት እና ከአውቶቢሶቹ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑ በችግርነት ተነስተዋል።

ሌላው እንደችግር የሚነሳው በመንገዶች ዳር እና ዳር መኪኖችን ማቆም ነው። በከተማዋም በየመንገዱ የሚቆሙትን ተሽከርካሪዎች ሳይጨምር በኤጀንሲው የተዘጋጁ ከ3 ሺሕ 600 በላይ የመኪና ማቆሚያ ሳጥኖች ይገኛሉ። ከእነዚህ የመኪና ማቆሚያ ሳጥኖች የመኪና ማቆሚያ እጥረትን ለመቅረፍ እና የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ዓይነተኛ መንገድ ቢሆንም መኪኖችን መመላለሻ መንገድ በማጥብብ እንደልባቸው እንዳይጓዙ እክል በመፍጠር ለትራፊክ እንቀስቃሴው መጓተት የራሱ አስተዋጽዖ አለው።

መንግሥት ለግል ብዙኀን ትራንስፖርት ድጋፍ እንደሚያድረግ ቃል መግባቱን ተከትሎ ወደ ዘረፉ ከመጡት መንግሥታዊ ካልሆኑ ብዙኀን ትራንስፖርት ድርጅቶች አንዱ በ2 ሺሕ 500 ባለ አክሲዮኖች የተመሰረተው እና በዘረፉ ብቸኛ ሆነው አሊያንስ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ነው።

በ2009 አጋማሽ ከንግድ ባንክ በተገኘ 70 በመቶ ብድር አንድ መቶ አውቶቢሶችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት አግልግሎት መስጥት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በማቆሚያ እና ነዳጅ መሞያ ቦታ እጥረት ፍትሐዊ ባለሆነ ስምሪት አሰጣጥ እና የታሪፍ ድጋፍ አለማግኘቱን ተከትሎ ለንግድ ባንክ ያለበትን ዕዳ ሳይከፍል ቀርቶ አውቶቢሶቹ በመያዛቸው 100 አውቶቢሶች ያለሥራ ቆመው ይገኛሉ።

የአሊያንስ የከተማ አውቶቢስ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አብዱል ፈታ ሁሴን አውቶቢሶቹ ከቆሙበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ድጋፍ ተደረጎልን አያውቅም ይላሉ። “ወደ ሥራ ከመግባታችን በፊት ማቆሚያ ቦታ እንደሚመቻችልን በታሪፍ ላይ ድጋፍ እንደሚደረግልን ቃል ተገብቶልን ነበር እሱም ቀርቶ ስምሪት ሲሰጠን እንኳን በኦሮሚያ አጎራባች ቦታዎች በመሆኑ እና በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ምክንያት እንደልባችን ተንቀሳቅሰን መሥራት አልቻልንም” ነበር ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት አውቶቢሶቹ ገና መሥራት ሳይጀምሩ ለብድሩ የተሰጠን እፎይታ ጊዜ አልቆ ባንኩ ያበደረውን ገንዘብ መክፈል ባለመቻሉ ከመደበኛ ስምሪት ውጪ ሆነው አውቶቢሶቹም ጎማቸው ተንፍሶ እና አቧራ ለብሰው በየካ አባዶ እና በገላን ኮንደሚኒየሞች እንዲቆሙ ሆነዋል ይላሉ።

በዘርፉ ብቸኛ እና ብርቅዬ ብንሆንም መንግሥት የገባውን ቃል ካለመጠበቁም በላይ ችግሩን ለአዲስ አበባ ትራንስፖረት ቢሮ እና ለንግድ ባንክም ጭምር ብናቀርብም ተቀዋማቱ የየራሳቸውን ሥራ ከመሥራት ባለፈ ምንም ዓይነት እገዛም ይሁን መፍትሔ ሊሰጡ እንዳልቻሉ ገልፀዋል።

የከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ
እንደ አዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መረጃ መሰረት በአማካኝ አንድ ሰው ከትራንስፖርት እጥረት እና ከትራፊክ መጨናነቅ ጋር በተያያዘ በየቀኑ አራት ሰዓታትን ያባክናል። ለዚህም በኢትዮጵያ ከሚገኙ ተሸከርካሪዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት በመዲናዋ በአዲስ አበባ መገኘታችው ካለው የመንገድ መሰረተ ልማት ማነስ ጋር ተዳምሮ በተለይም በሠራተኛ መግቢያ እና መውጫ ሰዓታት ላይ የመኪኖች ጉዞ የዔሊ እንዲሆን አድርጎታል።

የትራንስፖርት ስርጭት እና ቁጥጥር
ስርጭትን በተመለከተ በከተማዋ 406 የጉዞ መስመሮች ይገኛሉ እነዚህን የጉዞ መስመሮች የሚሸፍኑ በአጠቃላይ በእየቀኑ 13 ሺሕ የሚደርሱ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ኮድ 1 እና ኮድ 3 ታክሲዎች፣ ሀይገር እና በተለምዶ ቅጥቅጥ ተብለው የሚጠሩት ተሽርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ከነዚህም በተጨማሪ አንበሳ አውቶቢስ 124 መስመሮችን እንዲሁም ሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት 38 መስመሮችን ይሸፍናሉ። ለመንግሥት ሠራተኞች ጠዋት እና ማታ የትራንስፖርት አገልገሎት የሚሰጡት ፐብሊክ ሰርቪሶች በትርፍ ሰዓታቸው የታክሲ አገልግሎት ይሰጣሉ። እነዚህ በአጠቃላይም በከተማዋ በእየቀኑ 3 ሚሊዮን ሰዎችን ከቦታ ቦታ ያጓጉዛሉ።

እነዚህ ታክሲዎች እና መካከለኛ አውቶቢሶች በየማኅበራቸው በኩል በሚወጣላቸው የሦስት ወር የጉዞ መዳረሻ ስምሪት መሰረት እንዲሠሩ ይደረጋል። ይህንንም የሚቆጣጠሩ ከ400 በላይ ሠራተኞች ተሰማርተው ይገኛሉ።

ሆኖም “ከከተማው አጠቃለይ ስፋት እና የተሽከርካራዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ቁጥሩ በቂ ባለመሆኑ በተለይም ኮድ ሦስት ታክሲዎች ከተሰመሩበት መስመር ውጪ እየጫኑ እና ከታሪፍ በላይ በማስከፈል ለትራንስፖርት ባለሥልጣኑ ራስ ምታት ሆነውበታል” ሲሉ በአዲስ አበባ ሕዝብ እና የጭነት ትራንስፖርት ስምሪት ኀለፊ አካሉ ዘውዴ ይናገራሉ።

እነዚህን ሕገ ወጥ ድርጊቶች ለመከላከልም በ2009 በወጣው የቅጣት ደንብ መሰረት የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ መንጃ ፈቃድን እስከማስነጠቅ የሚደረሱ ቅጣት መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህ መሰረትም ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ እና ከስምሪት ውጪ አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሁም ጉዞ መዳረሻ (‘ታፔላ’) ሳይሰቅሉ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች ከብር አንድ ሺሕ ጀምሮ እንደሚቀጡ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ አቆራርጦ የጫነ ከተፈቀደው ጉዞ መስመር ውጪ በአቋራጭ ሲጓዝ የተገኘ ተጓዦችን ያንገላታ እና የተሳደበ አስከ አምስት መቶ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልበት እና እንደየ ጥፋቱ ድግግሞሽ መንጃ ፈቃድን እስከ መንጠቅ እንደሚደርስ በዚሁ መመሪያ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

እነዚህ ድርጊቶች የሚስተዋሉባቸው 31 የጉዞ መስመሮች ተለይተው ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው ሲሉም አካሉ ይገልፃሉ። ሆኖም ኅብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ሕገ ወጥ ድርጊቶቹ ሲፈፀሙ በመጠቆም እና እንዲጠየቁ ለማድረግ እየረዳን አይደለም ይላሉ።

ሆኖም በተቆጣጣሪዎች ተደራሽነት ላይ እና በሕጎች ተፈጻሚነት ላይ ከፍተኛ ክፍትት በመኖሩ ተጓዦች ለእንግልት እና ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ ይገኛሉ። ኅብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆኑም ሕገ ወጥ ድርጊቶቹ ሲፈጸሙ በመጠቆም እና እንዲጠየቁ ለማድረግ እየረዳን አይደለም ይላሉ። በመሆኑም ኅብረተሰቡ እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች ሲያጋጥሙት በሚኖርበት ክፍለ ከተማዎች በመሔድ መጠቆም እና መብቱን ማስጠበቅ እንደሚገባው አካሉ ዘውዴ ያሳስባሉ።

ችግሩ በባለሙያዎች ዓይን
በሲቪል እና በአካባቢያዊ ምህንድስና ላይ ከ18 ዓመታት በላይ የሠሩት የብሉ ሜትሪክስ የግንባታ አማካሪ መሠራች እና ባለቤት ጀማል መሐመድ ለትራንስፖረት ችግሩ መንስዔ ያሏቸውን ጉዳዮች እንዲህ ሲሉ ይዘረዝሯቸዋል።

የመንገድ መሰረተ ልማቱ ከከተማዋ ወቅታዊ ዕድገት ጋር የተጣጣመ አለመሆኑ እና ባለፉት 20 ዓመትት ከተማዋ በተቀናጀ ትራንስፖረት ማስተር ፕላን አለመመራቷ ለችግሩ እዚህ ደረጃ መድረስ ዋነኛው ምክንያት ነው ይላሉ። ከዚህ ጋርም ተያይዞ በከተማው ያለው የትራፊክ እንቅስቃሴ በዘመናዊ መንገድ ያልተደራጀ መሆኑ ሰዎች በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት ብዙ ደቂቃዎችን በመንገድ ላይ እንዲያሳለፉ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ይገልጻሉ። አክለውም የከተማ ትራንስፖርት ያልተስተካከለ ነው ማለት ሠራተኞች በገንዘብ የማይተመን የሥራ ሰዓታቸውን እንዲያባክኑ በማድረግ ምርታማነትን ይቀንሳል ሲሉ ያብራራሉ።

የከተማው ማስተር ፕላን የተዘበራረቀ እና የተበታተነ ነው የሚሉት ጀማል መሐመድ በከተማዋ የተዘጋጀ ማስተር ፕላን ቢኖራትም ወደ መሬት ወርዶ ሲተገበር በሳይንሳዊ ጥናት ላይ አይደለም ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የከተማዋ መንገድ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ቢመጣም ይህንን ሊያስተናግዱ የሚችሉ የአውቶብስም ሆነ የሌሎች ተሽከርካሪዎች ፌርማታዎች በሚፈለገው ደረጃ እና በስፋት አለመሠራታቸው ተሽከርካሪዎች በየመንገድ ዳርቻው እየቆሙ እንዲጭኑ አድርጓል። ይህም መንገዶቹ ተሽከርካሪዎችን ከማስተናገድ በተጨማሪ ሌላ ጫና እንዲኖርባቸው አድርጓል ሲሉ ይገልጻሉ።

ከዚህ በተጨማሪም እንደ ትምህርት ቤት ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዋና መንገድ ዳርቻዎች መሆናቸው በመንገዶች ላይ ለሚስተዋለው መጨናነቅ ራሱ የራሱ ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

ዓለምገና አለነ (ዶ/ር) በመንገድ ግንባታ እና ዲዛይን አማካሪነት በርካታ ዓመታትን ሠረተዋል። እንደ እርሳቸው አመለካከት ለከተማይቱ የሕዝብ ትራንስፖርት ችግሩ መንስዔ ያለቅጥ እየጨመረ ያለው ሕዝብ ቁጥር ነው። ለዚህ ምክንያቱ ባለፉት 20 ዓመታት የአገሪቱን ፖለቲካዊ የኀይል መዘውር ወደ ክልሎች ለማሰራጭት ጥረት የተደረገ ቢሆንም የአገሪቱ ከፍተኛው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በመዲናዋ ተገድቦ የቀረ እና በሌሎች የክልል ከተሞች ያልተስፋፋ መሆኑ በክልል የሚገኙ ዜጎች የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ፍለጋ ወደ ከተማዋ እንዲፈልሱ አድርጓል። ይህም ውስን የሆኑት የመንገድ የመሰረተ ልማት አውታሮች ከአቅማቸው በላይ ጫና እንዲሸከሙ አድርጓቸዋል ይላሉ።

የከተማዋ ወደ ጎን መስፋት ካለው የመንገድ የመሰረተ ልማት አውታሮች ወስንነትን ጨምሮ ያለው የአስተዳደር እና የአጠቃቀም ችግር መንገዶቹ መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።

ሌለው መሰረታዊ ችግር የሥራ እና የመኖሪያ አካባቢዎች የተራራቁ መሆናቸው በሠራተኛ መውጫ እና መግቢያ ሰዓታት ላይ ብዙ ሰዎች ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል። ይህም ሰፊ የሆነ የትራንስፖርት አቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ የተሽከርካሪዎች እጥረት እና የትራፊክ መጨናነቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

ማስተንፈሻ እርምጃዎች
ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ዓመታት በከተማዋ የሚኖረውን ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ትኩረቱን በብዙኀን ትራንስፖርት ላይ አድርጓል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የብዙኀን ትራንስፖርት አማራጮችን በስፋት ለማቅረብ የሚደረጉ እንቅስቀሴዎች ናቸው። ለአብነትም በመስከረም 2012 አንበሳ የከተማ አውቶቢስ 100 አውቶቢሶችን በመግዛት ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ ኹለት ዓመታት ውስጥ ተገንብተው ወደ አገልግሎት የሚገቡ በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በሚስተዋለባቸው ቦታዎች ተነስተው ከመሃል ከተማው ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች የሚገነቡ በሰዓት እስከ ስድስት ሺሕ ሰዎችን ማጓጓዝ የሚችሉ የፈጣን አወቶብስ መስመሮች ማሳያዎች ናቸው።

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ አውቶቢሶች የሚያድሩበት፣ ነዳጅ የሚቀዱበት እና ንጽሕናቸው የሚጠበቅበት አለፍ ሲልም መለስተኛ ጥገናዎች የሚደረጉበት ከ250 እስከ 300 አውቶቢሶችን ማስተናገድ የሚችል የባሶች ማደሪያ በቀድው በሼጎሌ ግቢ ውስጥ በ550 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ተጠናቋል። በቀጣይም ይህን መሰል ማደሪያዎችን እና የአውቶቢስ እና ታክሲ ተርሚናሎችን ለመገንባት እቅድ መያዙን ባለሥልጣኑ ይገልጻል።

ከዚህ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ የብዙኀን ትራንስፖርት አማራጮችን ቢጠቀም ወጪን ከመቆጠቡም በላይ በአንድ ላይ መጓዝ የትራፊክ መጨናነቁን ለመቅረፍ ይረዳል። በመሆኑም በመጪዎቸሁ ጊዜያት ማኅበረሰቡ የብዙኀን ትራንስፖርት አማራጮችን እንደሚጠቀም ለማድረግ የግንዛቤ ለውጥ እንዲያመጣ ጥረት ይደረጋል ተብሏል።
ይህንንም መሰረት በማድረግ የመጫን አቅማቸው ከ4 ቶን በላይ የሆኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 12 እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት እንዲሁም ከሰዓት ከ10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት በከተማ ክልል ውስጥ እንዳይገቡና እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ መንገዶቹን ከመጨናነቅ ለመታደግ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ይህም የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ተሸከርካሪዎች፣ ፍራፍሬ እና አባባ እንዲሁም ለድንገተኛ አደጋዎች እና መሰል ሥራዎች የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን የሚጨምር አይደለም።

ሌላው በከተማዋ የሚገኙ አደባባዮችን በጥናት ላይ በመመስረት ወደ ትራፊክ ማሳለጫ መብራቶች ለመቀየር፣ የመንገድ ላይ ምልክቶችን በተገቢው ቦታ ለመስቀመጥ እንዲሁም ጠዋት እና ማታ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በሚስተዋልባቸው መንገዶች ላይ ጥናት በማድረግ በአመዛኙ ነፃ የሚሆነውን አንዱን ክፍል የትራፊክ መጨናነቅ ያለው መስመር እንዲጠቀምበት ማድረግ አልፎም አውቶቢሶች ብቻ የሚጓዙባቸውን መንገዶች በቀለም የመለየት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ብርሃኑ ለማ ይገልፃሉ። ከዚህም በተጨማሪ በተመረጡ የከተማዋ አካባቢዎች ከጠዋቱ 12 እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት እንዲሁም ከሰዓት ከ10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት መኪኖች በየመንገዱ ዳር እንዳይቆሙ ተደርጓል።

ሆኖም በመንገድ ላይ የሚፈፀም ሕገ ወጥ ንግድ እንዲሁም የትራፊክ ሕጎችን አክብረው የማይነቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች እና እግረኞች ለትራፊክ እንቅስቃሴው የተቀላጠፈ አለመሆን የራሳቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ኤጀንሲው ይገልጻል።

ዘለቄታዊ መፍትሔ
በከተማዋ እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር መሰረት በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረቱን በብዙኀን ትራንስፖርት አማራጮች ላይ በማድረግ እየሠራ ይገኛል። ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም ፈጣን አውቶቢስ አገልግሎት ለችግሩ መፍትሔ እንደሚሰጥ በማመን ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል። እነዚህ የፈጣን አውቶቢስ መስመሮች አገልግሎት ለአውቶቢሶቹ ብቻ ታስበው በሚገነቡ መንገዶች ላይ የሚከወን እና ተሳፋሪዎች ከትራፊክ መጨናነቁ ጋር እንዳይገናኙ የሚያድረጉ ናቸው።

ለአብነትም በያዝነው ዓመት ከፈረንሳይ መንግሥት በተገኘ 80 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የግንባታ ሥራቸው ይጀመራል ተብለው የሚጠበቁት ከዊንጌት በጦር ኀይሎች ጀሞ የሚደረሰው እና 17 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን የፈጣን አውቶቢስ መንገድ እንዲሁም ከቦሌ በቄራ ጦር ኀይሎች የሚገነባው 11 ኪሎ ሜትር ፈጣን አውቶቢስ መስመር ለችግሩ መፍትሔ እንደሚሰጡት ይጠበቃል።

በቀጣይም ከተማዋን በእነዚህ የፈጣን አውቶቢስ መስመሮች ለማገናኘት እንደሚሠራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ይገልጻል።
የቢሮው የዘርፍ አቅም ግንባታ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ኀላፊ ቴዎድሮስ ፀጋዬ እንደሚገልጹት፣ ችግሩ የአቅርቦት ብቻ አይደለም። የትራንስፖርት አገልግሎቱ የሚሰጥባቸው ቦታዎች ለተሳፋሪዎች ምቹ ያልሆኑ እና ከአንዱ የአውቶቢስ ማቆሚያ ወደ ሌላኛው በማገለባበጥ የሚሠራ መሆኑ ተሳፋሪዎች በመንገላታት ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ ከማድረጉም በላይ እንደ መገናኛ ባሉ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የእግረኞች ቁጥር እንዲኖር አድርጓል ይላሉ። ይህም የትራፊክ መጨናነቅን ከመፍጠሩም በላይ ከተማዋ ለኑሮ የተመቸች እንዳትሆን እንዳደረጋት ይገልፃሉ።

ለወደፊት የትራንስፖርት ችግሩን ለመቅረፍም ሁሉም ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት በአንድ ስፍራ ላይ መሰጠት የሚችሉ ተርሚናሎችን በከተማዋ ፍኖተ ካርታ መሰረት ለመገንባት ጥናቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። በተጨማሪም ለአውቶቢሶች ማደሪያ እና የጥገና አገልግሎት የሚሰጥባቸው ባስ ዴፖዎችን በስፋት ለመገንባት እና ያሉትንም በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ቢሮው ይገልጻል።

ዘላቂ መፍትሔዎቹስ ምንድን ናቸው?
ጀማል መሐመድ ከሚያነሷቸው የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል የከተማውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና የሕዝብ ቁጥር ያማከለ እና በጥናት ላይ የተመሰረተ ማስተር ፕላን ማዘጋጀት አንደኛው ነው። በዚህም ከተማዋን በተጠና እና ተመሳሳይ በሆነ የትራንስፖረት መሰረተ ልማት ማገናኘት ተገቢ መሆኑን ያነሳሉ።
ከዚህ ጎን ለጎንም የትራፊክ ፍሰቱን ለሚቀላቀሉ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ የሚያደርጉ መጫኛ እና ማውረጃ ቦታዎች እንዲሁም ማደሪያ ስፍራዎች በስፋት መገንባት እንደሚኖርባቸው ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ የሰዎች እንቅስቃሴ የሚስተዋልባቸው እንደ ትምህርት ቤት፣ ሰፋፊ የገበያ ስፍራዎች እና መንግሥታዊ ተቋማት በዋና መንገዶች ዳርቻ ከመገንባት ይልቅ በተመሳሳይ አካባቢ ለእግረኞች በሚመች እና ከተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ወጣ ባለ ስፍራ መገንባት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የአሊያንሱ አብዱልፈታ በበኩላቸው የከተማውን ትራንስፖርት ችግር መንግሥት ብቻውን ሊፈታው አይችልም በመሆኑም መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል በሌሎች አገራት ግን ብዙኀን ትራንስፖርት አቅራቢዎችን ለማበረታት ታሪፈ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ ማቆሚያ ቦታዎችን በማቅረብ እንዲሁም የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የግል ብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅቶች ለብቻቸው እንዲሰሩ በማድረግ ድጋፍ ይደረጋል። በእኛም አገር መሰል ድጋፎች መኖር አለባቸው ሲሉ ይገልጻሉ።

በተጨማሪም መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን በተግባር ማገዝ ከቻለ የግል ብዙኀን ትራንስፖርት አቅራቢዎች የትራንስፖርት ችግሩን ለመቅረፍ የራሳቸውን አስተዋጽዖ ማበርከት ይችላሉ ብለዋል።

በዘርፉ አማካሪ የሆኑት ዓለምገና በበኩላቸው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በአንድ አካባቢ በተቀላቀለ መልኩ መኖር አለባቸው ይላሉ። እነዚህ ተቋማት አሁን ባለው ሁኔታ ወስን ናቸው የሚሉት ዓለምገና፣ ለአብነትም መርካቶ ገበያን በማንሳት በመርካቶ ደረጃ የሚደርስ ሌላ ገበያ በከተማዋ እስካሁን የለም። እነዚህን መሰል ተቋማትን በከተማዋ በተለያዩ ስፍራዎች ማስፋት ቢቻል ሰዎች አገልግሎትን ለማግኘትም ይሁን ለሥራ ወደ ተመሳሳይ ቦታ እንዳይጓዙ በማድረግ የትራፊክ እንቅስቃሴው የተረጋጋ እንዲሆን ያርገዋል የሚል ሐሳብ ያነሳሉ።

ሌላው እና በትኩረት ሊሠራበት የሚገባው ያሉት በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ማጎልበት እና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት መቆጣጠር ነው። ይህም ኢኮኖሚያዊ ሀብትን በፍትሐዊነት እንዲከፋፈል ከማድረጉም በላይ በከተማዋ ያለውን ሥራ አጥነት እና መሰል ማኅበራዊ ችግሮች በመቅረፍ ከተማዋን የተረጋጋች እና ለኑሮ የተመቻች ያደርጋታል ሲሉ አብራርተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here